ኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋቿን በሞት እንዳትቀጣ ተመድ አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, X
ኢራን፤ መሀንዲስ እና የሴቶች መብት ተሟጋች የሆነችውን ዘሐራ ታራቢንን በሞት እንዳትቀጣ የተባበሩት መንግሥታት አሳሰበ።
ተመድ ከ400 ታዋቂ ሴቶች ጋር በመጣመር ለኢራን ባቀረበው ጥሪ የ67 ዓመቷ የመብት ተሟጋች በሞት እንዳትቀጣ ጠይቋል።
ዘሐራ ሚያዝያ ላይ ነበር የታሰረችው። በኢራን መንግሥት እገዳ ከተጣለበት 'ዘ ፒፕልስ ሙጃሂንደን ኦርጋናይዜሽን' ጋር በማበር እንደተከሰሰች ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።
ራሻት የሚገኝ አብዮታዊ ፍርድ ቤት "በመሣሪያ በታገዘ አመጽ" የወንጀል ድርጊት ያለፈው ኅዳር ላይ ፈርዶባታል።
በቪድዮ የተከናወነው የፍርድ ሒደት ከ10 ደቂቃ ላነሰ ጊዜ የቆየ ነበር።
ቤተሰቦቿ እንደተናገሩት ፍርድ የተላለፈባት እጅግ ውስን በሆነ እና ተዓማኒነት በሚጎድለው ማስረጃ ነው።
በማስረጃነት ከቀረቡ መካከል 'ሴቶች፣ እምቢተኛነት፣ ነጻነት' የሚል ጽሑፍ ያለበት የልብስ ቅዳጅ እና ያልተላከ የድምጽ መልዕክት ይጠቀሳሉ።
የኢራን ባለሥልጣናት እስካሁን ስለ ፍርድ ሒደቱ አስተያየት አልሰጡም።
በመሣሪያ ከታገዘ አመጽ፣ ከስለላ እንዲሁም 'የፈጣሪ ጠላት' ከመሆን እና 'ከምድራዊ ሙሰኛነት' ጋር በተያያዘ ቢያንስ 51 ሰዎች ሞት እንደሚፈረድባቸው ተመድ ገልጿል።
በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል የኢራን የሰብአዊ መብት አያያዝ ልዩ መርማሪዎች ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በኢራን በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት፣ የዘፈቀደ ግድያ እንዲሁም መድልዎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።
በተጨማሪም የዘሐራ ጉዳይ "ዓለም አቀፍ ሕግ በተደጋጋሚ እንደሚጣስ ማሳያ ነው" ይላል መግለጫው።
ዘሐራ ያለ ፖሊስ ማዘዣ ከቤቷ ከተወሰደች በኋላ ብቻዋን ታስራ ለአንድ ወር ምርመራ ተደርጎባታል።
መንግሥትን 'በመሣሪያ ታግዛ' ለመገዳደር እንደሞከረች እና የተቃዋሚዎች ተባባሪ እንደሆነች በግድ እንድታምን መደረጓም ተገልጿል።
በመረጠችው ጠበቃ እንዳትወከል ስለታገደች ፍርድ ቤቱ ጠበቃ እንደመደበላት እና የፍርድ ሒደቷ ግራ ቀኙን ለማድመጥ በማያስችል ሁኔታ አጭር እንደነበርም ልዩ መርማሪዎቹ ተናግረዋል።
"ሕጋዊ አሠራር ተጥሷል፤ መብቷ ተገፏል፤ ጠበቃ የማቆም መብቷም አልተከበረም። የፍርድ ሒደቱ በጣም አጭር ነው። በመሣሪያ ከታገዘ አመጽ ጋር በተያያዘ ለቀረበባት ክስ የቀረበው ማስረጃ ለብይኑ በቂ ግብዓት አይመስልም" ሲሉም በመግለጫው አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ ሕግ የሞት ቅጣትን ለከፉ ወንጀሎች ብቻ እንደሚፈቅድ በመጥቀስ የመብት ተሟጋቿን በሞት መቅጣት ግን "ሆነ ብሎ መግደል" እንደሆነ አክለዋል።
"ዘሐራን በዚህ ሁኔታ በሞት መቅጣት የዘፈቀደ ግድያ ነው። ለፆታ እኩልነት ንቅናቄ የሚያደርጉ ሴቶችን መቅጣት በመሣሪያ በታገዘ አመጽ ከስሶ መቅጣት የፆታ መድልዎ ነው" ይላል መግለጫው።
የኖቤል ተሸላሚዎች፣ የቀድሞ የስዊዘርላንድ እና ኢኳዶር ፕሬዝዳንቶች፣ የቀድሞ የፔሩ፣ ፊንላንድ፣ ፖላንድ እና ዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨመሮ ከ400 በላይ ታዋቂ ሴቶች የመብት ተሟጋቿ ነጻ እንድትወጣ የሚጠይቅ ይፋዊ ደብዳቤ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
"ኢራን ሴቶችን በሞት በመቅጣት በዓለም ቀዳሚዋ አገር ናት። የሴቶችን እኩልነት የሚጠይቅ መፈክር ማሳየት በሞት የሚያስቀጣባት አገር ሆናለች" ሲሉም በደብዳቤው ገልጸዋል።
እአአ በ1988 በኢራን ከተፈጸመው ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ ለተጎጂዎች ፍትሕ እየጠየቀ ያለው ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ተቋም ዘሐራ ነጻ እንድትወጣ ጠይቋል።
ሌላዋ ሞት የተፈረደባት ኢራናዊት የኩርድ መብት ተሟጋች እና የማኅበራዊ አገልግሎት ባለሙያ ፓኪሻን አዚዚ ናት። ከዘሐራ ጋር ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባታል።
የተመድ ልዩ መርማሪዎች ቡድን ፓኪሻን "ብቸኛ ትኩረቷ የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራ ነው። በኢራቅ እና ሶርያ ተፈናቃዮችን ትረዳለች" ብሏል።
'ኢራን ሂውማን ራይትስ' ባወጣው አሐዝ መሠረት፤ እአአ በ2025፣ በ11 ወራት ውስጥ ቢያንስ 41 ሴቶችን ጨምሮ 1,426 ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ወስናለች። ቁጥሩ ከአምና ጋር ሲነጻጸር 70% ጨምሯል።
በሞት ከተቀጡ መካከል ግማሽ የሚሆኑት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ሲሆን፤ 53 የሚሆኑት ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር የሚገናኝ ክስ ቀርቦባቸዋል።















