ኢራን ሂጃብ ያልለበሱ ሯጮች የተሳተፉበትን ማራቶን አዘጋጆች አሰረች

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock
የኢራን የፍትሕ አካላት እንዳሉት ሁለት የማራቶን አዘጋጆች ሂጃብ ያልለበሱ ሴቶች በሩጫ እንዲሳተፉ በመፍቀዳቸው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው አርብ ዕለት በውድድሩ ላይ የተሳተፉ እና ሂጃብ ያልበሱ ሴቶች ምሥሎች በበይነ መረብ ላይ ከታዩ በኋላ ነው።
ሁለት ሺህ ሴቶች እና ሦስት ሺህ ወንዶች በኢራን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ በምትገኘው ኪሽ ደሴት በተካሄደው ማራቶን በተናጥል ተሳትፈዋል።
ከሴቶች ተወዳዳሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ቀይ ቲሸርት ያደረጉ ሲሆን፤ ሂጃብ ወይም ሌላ የራስ መሸፈኛ እንዳልለበሱ ግልጽ ነው።
ይህም የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል።
በኢራን ውስጥ ለውጥን የሚደግፉ ብዙ ሰዎች የኢራን ሴቶች የአገሪቱ ባለሥልጣናት አለባበሳቸው ላይ የጣሏቸውን ገደቦች አሻፈረን ማለታቸውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው በይነ መረብ ላይ የታዩትን ምሥሎች በጋለ ስሜት አድንቀዋል።
የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለወቅቱ ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸው ምላሽ ሰጥተዋል።
የፍትሕ አካላት በአዘጋጆቹ ላይ እርምጃ ለመውሰድ አፍታም አልወሰደባቸውም።
አንዳንድ ሴት ተወዳዳሪዎች በሂጃብ ላይ ያሉትን ሕጎች መጣሳቸው ብቻ ሳይሆን ከጅምሩ ማራቶኑ መካሄዱም ከአገሪቱ መንፈሳዊ የእስልምና አመራር ውግዘት ገጥሞት ነበር።
ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ብዙ የኢራናውያን ሴቶች የስፖርት ልብስ ለብሰው ከወንድ ተሳታፊዎች ተለይተውም ቢሆን እንኳን እንዲህ ባለ ሰፊ የሕዝብ ዝግጅት ላይ መሳተፋቸው እንደ ጥፋት ይቆጠር ነበር።
በኪሽ የሚገኘው ዐቃቤ ሕግ ውድድሩ የሚካሄድበት መንገድ በራሱ "የሕዝብ ጨዋነትን መጣስ" እንደሆነ ተናግሯል።
የሂጃብ ጉዳይ ኢራን ወዴት ልትሄድ እንደምትችል በሚደረገው ክርክር ዋና ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል።
ያለ ሂጃብ በአደባባይ በሚታዩ ሴቶች ላይ የሚወሰደው የመንግሥት እርምጃ የተለያየ ነው። አንዳንድ ጊዜ ሕጎቹ የሚላሉ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ የከፋ ይሆናል።
ማህሳ አማኒ የተባለች ኢራናዊት ወጣት ከሦስት ዓመታት በፊት የአለባበስ ሕጉን ጥሳለች በሚል ከታሰረች በኋላ በእስር ቤት ውስጥ መሞቷን ተከትሎ ኢራንን ለወራት ያናወጠው ሕዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ተቃውሞዎቹ በኃይል እና በጅምላ እስራት ከተገቱ ወዲህ፣ አንዳንድ ኢራናውያን ሴቶች ሕጎቹን መጣሳቸውን ቀጥለዋል።
ይህም በቅርብ ጊዜ በባለሥልጣናት ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል።
የፍትሕ ኃላፊው ሂጃብ ለብሰው በማይሄዱ ሴቶች ላይ አዲስ ዘመቻ እንደሚደረግ አስጠንቅቀዋል።
ጎላምሆሴን ሞህሴኒ ኢጄይ እንዳሉት የስለላ ኤጀንሲዎች "የሥነ ምግባር ብልሹነት የሚያበረታቱ እና ሂጃብ አለመልበስን የሚያበረታቱ የተደራጁ አዝማሚያዎችን" ለይተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዝዘዋል።
በኢራን መሪዎች እና በብዙ ዜጎቿ በተለይም በወጣቱ ትውልድ መካከል የሴቶች አለባበስ ላይ ያለው ክልከላ እና ይሁንታ ማለቂያ የለሌው ፍጥጫ መንስኤ ነው።















