እስራኤል ኢራንን ካጠቃች በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

እስራኤል ኢራንን ማጥቃቷን ካሳወቀች በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል።

እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ከተሰማ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከጥር ወር ወዲህ ከፍተኛ ነው የተባለውን ከ10 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለው ግጭት በነዳጅ ከበለፀገው አካባቢ የሚመጣውን አቅርቦት ሊያስተጓጉል ይችላል ሲሉ አገራት ሰግተዋል።

የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከመኪና ቤንዚን ጀምሮ እስከ የምግብ ዋጋ ድረስ ሁሉንም ነገር ይነካል።

በአውሮፓ የነዳጅ ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ሲሆን ሐሙስ ምሽት ላይ በ5 በመቶ ብቻ ከፍ ብሎ ነበር።

በለንደን የአንድ በርሜል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 72.80 ዶላር የነበረ ሲሆን በአሜሪካ የኒውዮርክ ገበያ (ኒሜክስ) ደግሞ 73.20 ዶላር ተሽጦ ነበር።

ምንም እንኳን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ10 በመቶ ያነሰ ነው።

በተጨማሪም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 መጀመሪያ ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመችበት ወቅት ከታየው ጭማሪ በታች ነው።

በወቅቱ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሚል ከ100 ዶላር በላይ ከፍ ብሎ ነበር።

አርብ ዕለት የአክሲዮን ዋጋ በመላው እስያ እና አውሮፓ ቀንሷል።

እንደ ወርቅ እና የስዊስ ፍራንክ ያሉ "ደህንነታቸው የተጠበቀ" የሚባሉት ንብረቶች ትርፍ አግኝተዋል።

አንዳንድ ባለሀብቶች ዓለም ባልተረጋጋችበት ወቅት እነዚህን ንብረቶች ይበልጥ አስተማማኝ መዋዕለ ንዋይ አድርገው ይመለከቷቸዋል።

የወርቅ ዋጋ ለሁለት ተከታታይ ወራት ያህል ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ኢራን ወደ 100 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ አገሪቱ ማስወንጨፏን አስታውቋል።

ተንታኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የነዳጅ ነጋዴዎች በመጪዎቹ ቀናት ግጭቱ ምን ያህል እየተባባሰ እንደሚሄድ ያጠናሉ።

የቫንዳ ኢንሳይትስ ባልደረባ ቫንዳና ሃሪ "ባለፈው ዓመት በሚያዝያ እና በጥቅምት ወር እንዳየነው እስራኤል እና ኢራን በቀጥታ ሲጋጩ በፍጥነት ሊቀዛቀዝ የሚችል ቢሆንም አደገኛ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም "ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦትን ወደሚያውክ ወደ ትልቅ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

የካፒታል ኢኮኖሚክስ ተንታኞች እንደተናገሩት የኢራን የነዳጅ ምርት እና የውጪ ንግድ ተቋማት ዒላማ ከተደረጉ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሚል ከ80 እስከ100 ዶላር ሊደርስ ይችላል።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው የዋጋ ጭማሪ ሌሎች ነዳጅ አምራቾች ምርታቸውን እንዲጨምሩ እንደሚያበረታታ፣ በመጨረሻም የዋጋ ንረትን እና ግሽበትን የሚገድብ መሆኑንም አክለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ተቆጣጣሪ አካል የሆነው አርኤሲ ቃል አቀባይ ሮድ ዴኒስ የቅርብ ጊዜ የነዳጅ ጭማሪ በነዳጅ ዋጋ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ እንደሚፈጥር ለመናገር ጊዜው በጣም ገና ነው ብለዋል።

"በጨዋታው ላይ ሁለት ቁልፍ ነገሮች አሉ፤በሚቀጥሉት ቀናት ከፍ ያለ የጅምላ ነዳጅ ዋጋ የሚታይ ከሆነ በወሳኝነት ቸርቻሪዎች ያንን ለመከተል ይወስናሉ" ብለዋል።

በጣም እጅግ የከፋው ሁኔታ በሆርሙዝ የባህር ዳርቻ የሚገኙ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ወይም መርከቦች ላይ ጥቃት የሚፈፀም ከሆነ ኢራን በቀን በሚሊዮኖች የሚቆጠር በርሜል ነዳጅ አቅርቦትን ልታስተጓጉል ትችላለች።

የባህር ዳርቻው ከዓለም በጣም አስፈላጊ ከሆኑ የንግድ መርከብ መንቀሳቀሻ አንዱ ነው።የዓለም ነዳጅ አንድ አምስተኛው የሚያልፈው በዚህ በኩል ነው።

በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ዋና የነዳጅ እና ጋዝ አምራቾች እና ደንበኞቻቸው በአካባቢው ነዳጅ ስለሚያጓጉዙ በማንኛውም ጊዜ፣ ወደ ሆርሙዝ የባህር ዳርቻ ብዙ ደርዘን የጫኑ የነዳጅ ታንከሮች ይገኛሉ።

በሰሜን ኢራን በደቡብ በኩል በኦማን እና በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የሚዋሰነው የሆርሙዝ ባህር ባህረ ሰላጤ ከአረብ ባህር ጋር ያገናኛል።

በኤምኤስቲ ፋይናንሺያል የኢነርጂ ምርምር ኃላፊ ሳውል ካቮኒክ "አሁን የምናየው ነገር በጣም የመጀመሪያ የሆነ የአደጋ ምላሽ ነው። ነገር ግን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ፣ ገበያው ይህ ወደየት ሊያመራ እንደሚችል ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል" ብለዋል።