ፓኪስታን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ስደተኞችን አባረረች

አፍጋኒስታናውያን ስደተኞች በድንበር አካባቢ ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አፍጋኒስታናውያን ስደተኛ ቤተሰቦች በቶርክሃም ድንበር ማቋረጫ አካባቢ

ፓኪስታን በዚህ ወር ብቻ ከ19,500 በላይ አፍጋኒስታናውያንን ከአገሯ አስወጣች።

በዚህ ወር ከፓኪስታን ከወጡት መካከል ከ80,000 በላይ የሚሆኑት ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም. ድረስ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ ቀደም ብለው መሄዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ፓኪስታን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን እና በጊዜያዊነት የመቆየት ፈቃድ የነበራቸውን አፍጋኒስታናውያንን ከዚህ በላይ እንዲቆዩ ማድረግ እንደማትችል በመግለጽ በፍጥነት አገሯን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛለች።

በየቀኑ ከ700 እስከ 800 የሚደርሱ ቤተሰቦች ከአገር እንዲወጡ እየተደረጉ መሆኑን የታሊባን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ወራት እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ፓኪስታንን ለቅቀው እንዲወጡ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዳሜ ዕለት የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳቅ ዳር ከታሊባን ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ወደ ካቡል አምርተው ነበር።

የአፍጋኒስታን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ ዜጎቻቸው ከፓኪስታን እንዲወጡ መደረጋቸው "በእጅጉ እንዳሳሰባቸው" ተናግረዋል።

በድንበር አካባቢ ከሚገኝ የፓኪስታን ግዛት እንዲወጡ የተደረጉ አፍጋኒስታናውያን ቤተሰቦቻቸው ግጭትን ሸሽተው ወደ ፓኪስታን ከተሰደዱ በኋላ የተወለዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2021 ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ 700,000 የሚጠጉ ሰዎችን ጨምሮ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ አፍጋኒስታናውያን ወደ ፓኪስታን ተሰድደው ይኖሩ እንደነበር የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።

በአፍጋኒስታን ባለው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ስደተኞችን ስትቀበል የቆየችው ፓኪስታን፣ በአገሪቱ ያለው ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን እና በሕዝብ አገልግሎት ላይ ጫና መፍጠሩን ተናግራለች።

ከሰሞኑ በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ጨምሯል።

ለግጭቱ ፓኪስታን በአፍጋኒስታን የሚገኙ ታጣቂዎች ተጠያቂ ናቸው ብትልም ታሊባን ግን አስተባብሏል።

የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ በካቡል በተካሄደው ስብሰባ ሁለቱ ወገኖች "የጋራ ጉዳዮችን ላይ ተወያይተዋል" ብለዋል።

ፓኪስታን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው አፍጋኒስታናውያን አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደቡን ለተከታታዮቹ አስር ቀናት፣ እስከ ሚያዝያ 22 2017 ዓ.ም. ድረስ አራዝማለች።

በቶርክሃም ድንበር አካባቢ የተባረሩ አፍጋኒስታናውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት አገራቸውን ከዓመታት በፊት ለቅቀው መውጣታቸውን ገልጸው እዚያ ኖረው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

በፓኪስታን ተወልዶ ያደገው ሳይድ ራህማን "ሕይወቴን ሙሉ በፓኪስታን ነው የኖርኩት" ብሏል። " እዚያ ነው ያገባሁት አሁን ምን ማድረግ አለብኝ?" ሲል ይጠይቃል።

የሦስት ሴት ልጆች አባት የሆነው ሳሌህ ሕይወት በታሊባን አገዛዝ ስር ምን ይመስላል የሚለው አሳስቦታል።

ሴት ልጆቹ ትምህርታቸውን በፓኪስታን እየተከታተሉ እንደነበሩ ገልጾ በአፍጋኒስታን ግን ከ12 ዓመት በላይ የሆናቸው ልጃገረዶች እንዳይማሩ መከልከላቸውን ጠቅሷል።

"ልጆቼ እንዲማሩ እፈልጋለሁ፤የትምህርት ጊዜያቸው እንዲባክን አልፈልግም" ብሏል።

"ማንኛውም ሰው የመማር መብት አለው።"

ሌላ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አፍጋኒስታናዊ በበኩላቸው "ልጆቻችን አፍጋኒስታንን አይተው አያውቁም። እኔ እንኳን ብሆን ምን እንደሚመስል ተረስቶኛል። ለመደላደል እና ስራ ለማግኘት አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድብን ይችላል፤ ምንም ረዳት እንደሌለን ነው የተሰማን።"