'የወደፊቱን እተነብያለሁ' በማለት 46 ሚሊዮን ዶላር ያጭበረበረችው ሴት እና ልጇ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, NSW Police
በአውስትራሊያ 'የሰዎችን እጣ ፈንታ እተነብያለሁ' በሚል 46 ሚሊዮን ዶላር ያጭበረበረችው የ53 ዓመት ሴት በቁጥጥር ሥር ዋለች።
የ25 ዓመት ልጇም ጤና እና ብልጽግናን ያጎናጽፋል በሚባለው የቻይና ባህላዊ ክንውን (Feng Shui) 'የተካንኩ ነኝ' ብላ በማጭበርበሯ ታስራለች።
እናት እና ልጅ በዋነኛነት በአውስትራሊያ የሚኖሩ ቬትናማውያንን እንዳታለሉ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ እንዳለው እናት እና ልጅ "በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀስ የምዝበራ ቡድን" አባላት ናቸው። በማጭበርበር እንዲሁም ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባትም ተጠርጥረዋል።
እናትየዋ "ለወደፊት ቢሊየነር ስትሆኑ ታይቶኛል" በማለት ሰዎች ከባንክ ገንዘብ ተበድረው ግማሹን እንዲሰጧት አድርጋለች ተብሏል።
እናት እና ልጅ ፍርድ ቤት ቀርበው፤ ልጅቷ በዋስ እንድትለቀቅ ሲወሰን እናትየዋ ግን የዋስትና ጥያቄዋ ውድቅ ተደርጓል።
የወንጀል ቡድንን መምራት እና በማጭበርበር ሃብት ማካበትን ጨምሮ 39 ክሶች ቀርበውባታል።
ልጅቷ ከወንጀል የተገኘ ጥቅም ተካፋይ መሆን እና በወንጀል ቡድን መሳተፍን ጨምሮ በሰባት የወንጀል ድርጊቶት ተከስሳለች።
እናት እና ልጅ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ቅንጡ ቤታቸው ሲሆን፤ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ዘመነኛ ቦርሳዎች፣ 6,500 ዶላር የሚያወጣ 40 ግራም ወርቅ እና 6,600 የአውስትራሊያ ዶላር የሚያወጣ የቁማር መጫወቻ ቺፖች ተገኝተዋል።
ፖሊስ እንዳለው እናትየዋ በምትኖርበት አካባቢ 'እጣ ፈንታ አዋቂ' በሚል የተከበረች ስትሆን፤ ብዙዎች ስለሚያምኗት የገጠማቸውን የገንዘብ ቀውስ ይነግሯት ነበር።
እሷም በቅርቡ "ቢሊየነር ትሆናላችሁ" በማለት ከባንክ ብድር እንዲወስዱ ታበረታታለች።
ከግለሰቧ ጋር በተያያዘ ፖሊስ 15 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር የሚያወጣ ንብረት ላይ ዕገዳ ጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, NSW Police
የአውስትራሊያ ፖሊስ አምና በከፈተው ምርመራ፤ በሐሰተኛ ሰነድ ቅንጡ መኪና ለመግዛት ብድር በመውሰድ ገንዘብ የሚመዘብር የወንጀል ቡድን ላይ መድረስ ችሏል።
መርማሪ ፖሊስ ጎርዶን አርቢጃ "ከመኪና ግዢ ጋር የተያያዘ ማጭበርበር ላይ የተከፈተው ምርመራ ውስብስብ የሆነ የወንጀል ቡድን እንቅስቃሴ ላይ እንድንደርስ አግዞናል። በሙያዬ ካየኋቸው የወንጀል ድርጊቶች በጣም የረቀቀው ነው" ብለዋል።
የወንጀል ቡድኑ ለቤት ግዢ ከሚሰጥ ብድር ጋር በተያያዘ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማትን እንዳጭበረበረ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
የወንጀል ቡድኑ መሪ በሲድኒ 18 ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር በሚያወጣ ቤት ውስጥ እንደሚኖር ተገልጿል። ከእናት እና ልጅ በተጨማሪ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ጠበቆች፣ አካውንታትቶች እና ቤት አልሚዎችን ጨምሮ ሌሎችም አባሪዎች ላይ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ የአውስትራሊያ ፖሊስ አስታውቋል።















