ሳልሠራ ያገኘሁት ነው በሚል በውርስ ያገኘችውን 25 ሚሊዮን ዩሮ በስጦታ ልታከፋፍል የወሰነችው ኦስትሪያዊት

የኦስትሪያ እና ጀርመን ጥምር ዜግነት ያላት አንዲት ግለሰብ ከአያቷ የወረሰችውን አብዛኛውን ሐብት እንዴት በስጦታ መስጠት እንዳለባት ለመወሰን ቡድን በማቋቋም ላይ ትገኛለች።

የ31 ዓመቷ ማርሊን ኤንገልሆርን መኖሪያዋ በቪዬና ሲሆን 50 ኦስትሪያውያን ያቀፈ ቡድን በማቋቋም በውርስ ያገኘችውን 25 ሚሊዮን ዩሮ እንዴት መከፋፈል እንዳለበት ለመወሰን ትፈልጋለች።

“ምንም ሳልሠራ ሐብትና ሥልጣኔ ወርሻለሁ” ብላለች።

"መንግስትም ከሐብቱ ላይ ታክስ ለመቁረጥ እንኳን አይፈልግም።"

ኦስትሪያ በውርስ ላይ የሚጣል ታክስን በ2008 አቋርጣለች። ይህም የውርስ ታክስ ወይም የሞት ቀረጥ ከማይጥሉ ጥቂት የአውሮፓ አገሮች አንዷ አድርጓታል።

ይህም ፍትሐዊ አለመሆኑን ኤንገልሆርን ታምናለች።

ግለሰቧ የፍሪድሪክ ኤንገልሆርን ቤተሰብ አባል ናት። ፍሬደሪክ የጀርመኑ ቢኤኤስኤፍ የኬሚካል እና ፋርማሲዩቲካል ኩባንያ መስራች ሲሆኑ ሴት አያቷ እአአ በ 2022 ህይወታቸው ሲያልፍ በሚሊዮኖችን የሚቆጠር ገንዘብ ወርሳለች።

ፎርብስ መጽሔት የትራወድል ኤንገልሆርን-ቬቻይቶን ሐብት 4.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ገምቷል። አያቷ ከመሞታቸው በፊት ነው ኦስትራዊቷ 90 በመቶ የሚሆነውን ውርስዋን መለገስ እንደምትፈልግ የተናገረችው።

ረቡዕ ዕለት በዘፈቀደ የተመረጡ የኦስትሪያ ዜጎች ግብዣ እየደረሳቸው ነው።

ጉድ ካወንስል ፎር ሪዲስትሪቡውሽን ለተባለው ቡድን መሥራት የሚፈልጉ በበይነ መረብ ወይም በስልክ መመዝገብ ይችላሉ። በመጀመሪያው ዙር ከተመለመሉት ከ 10 ሺህ ኦስትሪያውያን መካከል 50 ሰዎች ይመረጣሉ። ሊያቋርጡ የሚችሉ ካሉም በሚል 15 ተተኪ አባላትም ይመረጣሉ።

"ፖለቲከኞች ሥራቸውን ካልሠሩ እና ካላከፋፈሉ፤ ሐብቴን ራሴ ማከፋፈል አለብኝ" ስትል በመግለጫዋ አስረድታለች።

"ብዙ ሰዎች ሥራ ሠርተው ከሚያገኙት እያንዳንዱ ዩሮ ግብር ይከፍላሉ። ይህን እንደ ፖለቲካ ውድቀት ነው የማየው። ፖለቲካው ካልተሳካ ዜጎቹ ራሳቸው ሊቋቋሙት ይገባል።"

ሐሳቡን የሚደግፈው የፎርሳይት ኢንስቲትዩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስቶፍ ሆፊንገር በበኩላቸው የውርስ ገንዘቡን መልሶ የሚያከፋፍለው ቡድን 50 ሰዎች ሲኖሩት “ከሁሉም የዕድሜ ምድቦች፣ ከክልሎች እና ከሌሎችም ዘርፎች” የተውጣጡ ናቸው።

ቡድኑ "የህብረተሰቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ መፍትሔዎችን በጋራ ለማዘጋጀት ሐሳባቸውን እንዲያበረክቱ" ይጠየቃል ብለዋል።

በዚህ ዓመት ከመጋቢት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ በሳልዝበርግ ከምሑራን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በሚደረጉ ተከታታይ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ።

የጉዞ ወጪዎች የሚሸፈኑ ሲሆን እና ተሳታፊዎች ለሚገኙበት ለእያንዳንዱ ቅዳሜና እሁድ 1 ሺህ 200 ዩሮ ያገኛሉ።

ማርሊን ኤንገልሆርን ውይይታቸው "የዲሞክራሲዊ አገልግሎት" እንደሚሆን ስልምታምን ለዚያም በትክክል ማካካሻ ሊደረግላቸው ይገባል ብላለች ።

"ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የለኝም። ንብረቶቼን በእነዚህ 50 ሰዎች እጅ ከማስቀመጥ ባለፈ በእነሱ ላይ እተማመናለሁ" ስትል ተናግራለች።

በገንዘቡ ምን እንደሚደረግ "በስፋት የሚያስማማ" ውሳኔ ማምጣት ካልቻሉ ገንዘቡ ለኤንገልሆርን ይመለሳል።

ከውርስዋ ምን ያህሉን እንደምትሰጥ በትክክል ግልጽ አይደለም። እአአ በ 2021 ምንም ሳትሠራ ያገኘችው እና ከቤተሰቡ በመወለዷ የደረሳት “የልደት ሎተሪ” መሆኑን በመጥቀስ ቢያንስ 90 በመቶውን ለማስረከብ እንደምትፈልግ ገልጻ ነበር።

የተወሰነ ገንዘብ ለራሷ ለማስቀረት ያሰበች ቢሆንም ምንያህል እንደሆነ አልተገለጸም።

ኦስትሪያ የውርስ ታክስን ከሰረዘች ከ16 ዓመታት ቢሆነውም አሁንም ድረስ አከራካሪነቱ ቀጥሏል። ሶሻል ዲሞክራትስ የተሰኘው ተቃዋሚ ፓርቲ ታክሱ እንዲመለስ ይፈልጋል።

የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ መሪ የሆኑት አንድሪያስ ባቤር ለኦአርኤፍ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት መጨረሻ ከሚካሄደው የኦስትሪያ አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ጥምር መንግስት ለመመስረት ዋናው የድርድር ቅድመ ሁኔታ እንዲሆን ይፈልጋሉ።