በኤርትራ የካቶሊክ ምዕመናን ከቤተክርስቲያን መታፈሳቸው ተገለጸ

መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስትያን በፀጥታ ኃእሎች የተያዙ ምዕመናን

የፎቶው ባለመብት, Social Media

የኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች ከአሥመራ በስተደቡብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አክሩር መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመግባት፣ አገልጋዮች እና ጸሎት ላይ የነበሩ ወጣቶችን አፍሰው መውሰዳቸው ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ወታደሮቹ ቤተ ክርስቲትያኑ ውስጥ ያገኙዋቸውን ዲያቆናት እና መዘምራንን ጨምሮ ይዘው መውሰዳቸውን ተገልጿል።

ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በደቡባዊ ዞን፣ የኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች ከአገሪቱ ሠራዊት ከድተዋል እንዲሁም እድሜያቸው ለብሔራዊ አገልግሎት ደርሶ ወደ ሳዋ አልሄዱም ያሉዋቸው ወጣቶችን እያፈሱ እየወሰዱ መቆየታቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ከሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉትን ለመያዝ የተሰማሩት ወታደሮች፣ ልጆቻቸው ያልተገኙት ቤተሰቦችን ከቤታቸው እንዲወጡ በማድረግ፣ ቤቶቹን በራሳቸው ቁልፍ በቆልፈው ወላጆችን አንዲንገላቱ አድርገዋል ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል።

የኤርትራ ሠራዊት በሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት እየተሳተፈ ነው የሚል ክስ እየቀረበ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ወጣቶች እየታፈሱና ቤተሰቦቻቸው እየተንገላቱ እንደሚገኙ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ምንጮች ገልጸዋል።

ፍጹም የተባለ የአካባቢው ተወላጅ የሥርዓቱ ወታደሮች፣ ልጆቻቸው ከድተዋል ያሏቸውን ቤተሰቦች እንሳሳቶቻቸው ለግጦሽ እንዳይወጡ በመከልከል “በረት ውስጥ በረሃብ እንዲሰቃዩ” እያደረጓቸው ነው ብሏል።

መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስትያን

የፎቶው ባለመብት, Social Media

በቤተሰቦቻቸው እና በእንስሶቻቸው ላይ የሚደርሰው መንገላታት ያላስቻላቸው በርካታ የሚፈለጉ ወጣቶች እና የብሔራዊ አገልግሎት አባላት በፍላጎት እጃቸው ለመንግሥት እየሰጡ እንደሚገኙም ምንጮች ያስረዳሉ።

አሁን በኤርትራ ሠራዊት እየተፈለጉ ካሉ አብዛኞቹ ከ10 ዓመት በላይ በሠራዊቱ ያገለገሉ እና መፍትሄ በማጣታቸው ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ ከሠራዊቱ የሸሹ እንደሆኑ ፍጹም ለቢቢሲ ገልጿል።

በተጨማሪም ለዓመታት አገልግለው ለመቋቋም እና ኑሮ ለመምራት ዕድል ያላገኙት፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ለማገዝ ከገደብ የለሹ ወታደራዊ ብሔራዊ አገልግሎት የሸሹ ኤርትራውያን በጦርነት የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸውም ይገልጻል።

ምንም እንኳ የኤርትራ ሠራዊት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ዳግም ባገረሸው እና እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ላይ እየተሳተፈ ነው የሚል ክስ ቢቀርብበትም መንግሥት ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም።

እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶት በኤርትራ ገደብ የለሽ ወታደራዊ አግልግሎት ለወጣቶች ፍልሰት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋና ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል።

የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ከምዕራባውያን እና በሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚሰነዘርበት ትችት ከእውነት የራቀ እና ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው በማለት ያስተባብላል።