የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፆታ መቀየርና የማሕፀን ኪራይን በተመለከተ ያላትን አቋም እንደማትቀይር ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቫቲካን ፆታ መቀየርን፣ የማሕፀን ኪራይ፣ ፅንስ ማቋረጥ እና በከፋ ህመም ያሉ በሽተኞችን በፈቃዳቸው መግደልን በተለመከተ ያላትን አቋም ይፋ አድርጋለች።
“ዲግኒታስ ኢንፊኒታ” የተሰኘ ርዕስ ባለው ፅሑፍ ነው ይሀን ይፋ ያደረገችው።
ፅሑፉ ሌሎች እንደ ድኅነት፣ ስደት እና ሕገ-ወጥ የሰው ልጅ ዝውውር ያሉ ማሕበራዊ ጉዳዮችንም አንስቶ የሰው ልጅ ክብርን የሚገረስሱ ናቸው ይላል።
መግለጫውን በፊርማቸው ያጸደቁት ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ናቸው።
ሊቀ-ጳጳሱ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አቋም የላላ ነው የሚል ትችት ከወግ አጥባቂ ካቶሊኮች ሲደርስባቸው ይሰማል።
ፍራንሲስ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያንን ከባህላዊው ትምህርት እያራቋት ናቸው የሚል ነው የወግ አጥባቂ ካቶሊኮች ትችት።
ነገር ግን ነፃ ሐሳብ የሚያራምዱ ካቶሊኮች ደግሞ ጳጳሱ ቤተ-ክርስቲያኗ ከዘመኑ ጋር እንድትራመድ ገና ብዙ መሥራት አለባቸው ይላሉ።
በ2023 ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች [ትራንስጀንደር] በካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን መጠመቅ ይችላሉ ማለታቸው ይታወሳል። አልፎም ቄሶች የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንዲባርኩ መፍቀዳቸው አይዘነጋም።
ምንም እንኳ ቫቲካን አሁንም ጋብቻን በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ነው ብትልም ፍራንሲስ ግን እንደሁኔታው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንም ጋብቻቸው ቡራኬ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሊቀ-ጳጳሱ የቫቲካን ጠንካራው የሚባለው የዶግማውን ቢሮ ዘመኑ የሚጠይቃቸውን “አዳዲስ ጥያቄዎች” እንዲመረምር አዘው ነበር።
ይህን ቢሮ የፍራንሲስ የቅርብ ሰው የሆኑት ካርዲናል ቪክተር ማኑዌል ፈርናንዴዝ ናቸው የሚመሩት።
ካርዲናል ፈርናንዴዝ በ1990ዎቹ ስለ ፆታ በጥልቅ የሚተነትን መፅሐፍ ማሳተማቸውን ተከትሎ በርካታ ወቀሳ ደርሶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ እና በቤተ-ክርስቲያኗ ሴቶች ያላቸውን ሚና በተለመከተ ሊቀ-ጳጳስ ያላቸው አቋም ለዘብተኛ እንደሆነ እና ወደፊት ለውጦች ሊመጡ እንደሚችሉ ተገምቷል።
በሌሎች ጉዳዮች በተለይ ደግሞ በሁሉት አከራካሪ ርዕሶች ላይ ግን ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የማሕፀን ኪራይን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ድርጊቱ “አስነዋሪ” ማለታቸው፤ እንዲሁም የፆታ ሚና በባዮሎጂ ሊቀየር የሚችል ነው የሚለውን ሐሳብ “የማይረባ ባዮሎጂ” ሲሉ ገልጠውት ነበር።
አሁን ያሳተሙት ዲግኒታስ ኢንፊኒታ ፅንስ ማቋረጥን “ለሰው ልጅ የሞራል ልዕልና ከፍተኛ አደጋ ያለው” የሚል ሲሆን የማሕፀን ኪራይን ደግሞ ለሴቷ እና ለሚወለደው ልጅ “ውርደትን” የሚያመጣ ነው ብለዋል።
አዲሱ መመሪያ ሰዎች ሲወለዱ ያላቸው ፆታ ስጦታቸው እንደሆነ፤ ይህን ለመቀየር መሞከር “ፈጣሪን ለመሆን እንደ መሞከር” እንደሆነ ይጠቅሳል።
ድኅነት የደቆሳቸውን ሰዎች፣ ስደተኞች እና ሴቶች መበዝበዝን ደግሞ የሰው ልጅ ክብርን የሚያቆሽሹ ተግባራት ናቸው ይላል።
የ87 ዓመቱ ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ 2013 ነው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ሆነው የተሾሙት። ባለፈው ወር በታተመው የሕይወት ታሪካቸውን የሚያትት መፅሐፍ ከመንበራቸው የመውረድ ዓላማ እንደሌላቸውና በሕይወት እስካሉ ድረስ ቤተ-ክርስቲያኗን እንደሚመሩ አሳውቀዋል።












