የተቋረጠው የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የምግብ እርዳታ

በአፍሪካ ቀንድ ለአራት አስርት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ተከስቷል። በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲሁም ግጭቶች አጋጥመዋል።

የሁለቱ ድምር ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አስቸኳይ እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የጦርነት ማዕከል በነበረችው ትግራይ ክልል ውስጥ ካሉ ነዋሪዎች ከ90 በመቶ በላይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ይላሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የእርዳታ ድርጅቶች እጃቸውን ሲዘረጉ ቆይተዋል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የምግብ እርዳታ ከሚሰጡት አገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት። ይህንንም በእራሷ የተራድኦ ድርጅት እና በተባበሩት መንግሥታት በኩል ታከናውናለች።

ነገር ግን እነዚህ የረድኤት ድርጅቶች የምግብ የእርዳታ እጃቸውን ሰብስበዋል።

ሐሙስ ሰኔ 01/2015 ዓ.ም የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ከተረጂዎች አፍ እየተነጠቀ ለሌላ ጥቅም ውሏል በሚል እንዲቋረጥ መወሰኑን አስታወቀ።

“ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅረብ የነበረበት የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ በመዋሉ” ከዚህ ውሳኔ እንደደረሰ ዩኤስኤአይዲ ገልጿል።

ውሳኔው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት የተወሰደ መሆኑን የተራድኦ ድርጅቱ ገልጿል።

አርብ ሰኔ 02/2015 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ በመዋሉ ለአገሪቱ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡን አስታወቀ።

“እርዳታው ላልተገባ ዓላማ መዋሉ ፍጹም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲንዲ ማኬይን ተናግረዋል።

ቅዳሜ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኤስኤአይዲ የተወሰደውን የእርዳታ አቅርቦትን የማቋረጥ ውሳኔ “ፖለቲካዊ” ነው ሲል ተቃወመ።

የኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ እርምጃው “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህም ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” ብሎ መንግሥታቸው እንደሚያምን አመልክተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ማቋረጡንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዩኤስኤአይዲ እየተስተዋለ ያለውን የምግብ እርዳታ ላልተገባ ዓላማ መዋልን እልባት ለማግኘት ቁርጠኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ሁለቱ መንግሥታት እርዳታዎችን ላልተገባ ዓላማ ያዋሉ ወንጀለኞች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ምርመራ እያደረጉ ነው። ሁለቱ መንግሥታት በኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ በተቀላጠፈ መንገድ የሚዳረስበት እና እርዳታ ላልተገባ ዓላማ ከመዋል በሚታደግ መልኩ የሚሰራጭበትን ሥርዓት ለመዘርጋት በትብብር ለመሥራት ቃል ገብተዋል” ብሏል የጋራ መግለጫው።

በተመሳሳይ የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ ተጠቅሟል በሚል ስሙ የተነሳው የመከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሠራዊቱ የእርዳታ ምግብን እንደማይጠቀም በመግለጽ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎታል።

የሰብአዊ እርዳታ ተቋሙ ‘ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል’ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ደግሞ በኢትዮጵያ “የእርዳታ አቅርቦት በከፍተኛ መጠንና በተቀናጀ ሁኔታ ለሌላ አላማ መዋሉ” መታወቁን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግሥት “ይህ አይነቱ ድርጊትን እንደማይታገስ” በግልጽ ማሳየት አለበት ብሏል።

የተከሰተው ምንድን ነው?

ዋሽንግተን ፖስት ሾልከው እጁ እንደገቡ ከጠቀሳቸው መረጃዎች በመነሳት የምግብ እርዳታው ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ በማዋሉ ተግባር የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ተሳትፈዋል ሲል ዘግቧል።

የተዘረፈው የምግብ እርዳታ በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ግን ግልጽ አልተደረገም።

ባለሥልጣናት እርዳታውን ከተረጂዎች አፍ በመንጠቅ ለወታደሮች እና ለቀድሞ ተዋጊዎች ሰጥተዋል። አለፍ ሲልም ወደ ሌላ አገር ለሚልኩ የዱቄት ፋብሪካዎች በግልጽ መሸጣቸውንም የዩኤስኤይድ ምርመራ ማረጋገጡን ዘግቧል።

መርማሪ ቡድኑ በኢትዮጵያ ዘጠኝ ክልሎች የሚገኙ 63 የዱቄት ፋብሪካዎችን በመጎብኘት፣ በሰባቱ ክልሎች ከፍተኛ መጠን ያለው የእርዳታ ምግብ ላልተገባ ዓላማ መዋሉን አመልክቷል።

ከአሜሪካ፣ ከዩክሬን፣ ከጃፓን እና ከፈረንሣይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የተለገሰው የእርዳታ ምግብ ተዘርፏል ሲልም ዘገባው ጠቅሷል። ሁሉም የእርዳታ እህል የላኩ ለጋሾች ሥርጭቱን እንዲያጤኑም ጥሪ ቀርቧል።

ዋሽንግተን ፖስት ስለጉዳዩ ያውቃል ካለው የእርዳታ ሠራተኛ አገኘሁት እንዳለው መረጃ ከሆነ፣ ኃላፊነት የተጣለባቸው የአካባቢ ባለሥልጠናት የተረጂዎችን ዝርዝር ሲያዘጋጁ የተቸገሩ አባወራዎችን ቁጥር በማናር እና ለተራቡ ቤተሰቦች እንዳይደርስ ያደረጉ ይመስላል ብሏል።

ስለጉዳዩ የሚያውቁ አንድ ዲፕሎማት ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ እህል ወታደሮችን እና የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎችን ለመመገብ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በረሃብ እየተሰቃዩ ባሉበት ወቅት ከእርዳታ ስንዴ የተዘጋጀ ዱቄት ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ እየተላከ ነው ያሉት ዲፕሎማቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም “ቸልተኛ ወይም ተባባሪ ነው" ብለዋል።

አስከፊ ድርቅ በገጠመው የሶማሌ ክልል የሚገኙ የዱቄት ፋብሪካ ኃላፊዎች ለምርመራ ቡድኑ እንደገለፁት የዩኤስኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም አርማ በተለጠፈበት ከረጢት ስንዴ በብዛት ይገዙ እንደነበር ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

የስንዴ ከረጢቶቹ ያልተከፈቱ መሆናቸው ካገኙት ድጋፍ የተወሰነውን ከሸጡ እርዳታ ጠባቂዎች የተገዙ እንዳልሆኑ ያሳያል ብለዋል ዲፕሎማቱ።

ትግራይ ክልል እና ፌደራል መንግሥቱ ምን አሉ?

የትግራይ ክልል ጉዳዩን ለማጣራት በሚያዝያ ወር ያቋቋመውን ኮሚቴ የሚመሩት የትግራይ ክልል ሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ ኪዳኑ ናቸው።

ኃላፊው ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ምን ያህል እርዳታ እንደገባ፣ ማን እንዳከፋፈለው እና በምን መልኩ እንደተዳረሰ ጥናት መሠራቱን እና ሕዝቡም በተለያየ መንገድ ጥቆማ የሰጠበት መሆኑን ገልጸዋል።

የእርዳታ አከፋፋዮች ብቃት፣ ታማኝነት እና እርዳታው ወደ ሕዝቡ የተላለፈበት መንገድ መታየቱን ጠቅሰዋል።

ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ “አነሰም በዛም የእርዳታ አቅርቦት መጥፋት እንዳለ ማረጋገጥ ችለናል። በእርግጥ ይህ እንደመነሻ የደረስንበት እንጂ ሌላም ሊኖር እንደሚችል ግምት ውስጥ መግባት አለበት” ብለዋል።

“በሁሉም ወገን የተፈጸሙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በውጊያው ጊዜ ፌደራል መንግሥት ሲያስተዳድር በነበረት ጊዜ በጊዜያዊ አስተዳዳሪነት የተሹሙ አካላት የፈፀሟቸው ስርቆቶች እና ማጭበርበሮች አሉ።

“የሻዕቢያ ኃይል የዘረፈው የእርዳታ እህልም አለ። እርዳታ እንዲያከፋፍሉ በሚል በሕዝብ ይሁን በአስተዳደር የተወከሉ የፈፀሙት ስርቆት አለ። እርዳታ አቅራቢዎች ለበጎ ሥራቸው ማመስገን ቢገባም በእነሱ በኩልም ስርቆት ተፈፅሟል” ብለዋል።

የእርዳታው እህል ገበያ ላይ የታየው ከሠላም ስምምነቱ በፊት በእርዳታ ድርጅቶቹ የሚሠሩ ሠራተኞች በጥሬ ገንዘብ ምክንያት ደመወዝ ማግኘት ስላልቻሉ በምትኩ የሚሰጣቸውም የእርዳታ እህል በመሸጣቸው፤ ከአማራ፣ ከአፋር እና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ወደ ትግራይ የሚመጡ የሸቀጦች በእርዳታ ድርጅቶች ማሸጊያ ከረጢቶች የሚገቡ በመሆናቸው እና በትግራይ ውስጥም የእርዳታ እህሎቹ ተሰርቀው ለገበያ ስለሚቀርቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

እናቶች እና ህጻናት በምግብ እጥረት ሕይወታቸውን እየከፈሉ ወደ ስርቆት የሚገባ ሰው መኖሩን መስማት እጅግ የሚያሳምም ነው። ይንን አለመታገል የሞት ሞት ነው ብለዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች 186 ገደማ ሰዎች ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ቢውሉም ሕግ ፊት ቀረቡት ሰባት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሁሉም ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

የመርማሪ ኮሚቴው መሪ የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲቋረጥ የተደረገበት ውሳኔን “የሞት ፍርድ የመፍረድ ያህል ነው” በማለት፣ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር እርዳታው ዳግም እንደሚጀመር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በበኩሉ የእርዳታ አቅርቦት እንዲቋረጥ መደረጉ ሚሊዮኖችን ለችግር የሚዳርግ እና ለቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ “እንደማይቀበለው” በመግለጽ ውሳኔው መለስ ተብሎ እንዲጤን ጠይቋል።

እንዲሁም በዚህ የእርዳታ አቅርቦትን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዲውል በማድረግ በኩል የተሳተፉ አካላት በምርመራ በማስረጃ ተረጋግጦባቸው ሲገኝ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

መንግሥት በጉዳዩ ላይ ስላደረገው ማጣራት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ስለጉዳዩ ለማወቅ ቢቢሲ ያደረገው ሙከራም አልተሳካም።

በጉዳዩ ዙሪያ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የዩኤስኤአይዲ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር እርዳታው መቋረጡ መጥፎ መሆኑን ጠቅሰው ለተረጂዎች የተሰጠ እርዳታ ገበያ ላይ እየዋለ ትርፍ እየተሰበሰበበት ነው ብለዋል።

“ምርመራ እየተካሄደ ነው። እርዳታውን እንደገና ለማስጀመር ፍላጎት አለን። ለዚህ ደግሞ እርዳታው ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች እየደረሰ መሆኑን መተማመን አለብን።

“ለዚህም እንደ ዩኤስኤአይዲ ባሉ ለጋሾች እና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ በጣም ፈጣን ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም

በኋላ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊያስቀጥል እንደሚችል ጠቁሟል።

ተረጂዎች በምን መልኩ እንደሚመረጡ የሚያስችለው ቁጥጥር ማደግ ከቻለ በሚቀጥለው ወር የተወሰኑ የምግብ እርዳታዎችን ማቅረብ ሊጀምር እንደሚችል አንድ ከፍተኛ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለሥልጣንን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የፖሊሲ ልማት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ቫለሪ ጓርኒየር “ተረጂዎችን በመምረጥ ሂደት እኛ እንደ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ እንዲሁም አጋር የሆኑት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች የበለጠ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረን እንፈልጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም መርማሪዎች በድርጅቱ የክትትል ሥርዓቶች ላይ ያሉ ድክመቶችን በተለይም በትግራይ ክልል ለይተው ማወቃቸውንም ተናግረዋል።