አይኤምኤፍ የብድር ስምምነት ላይ ሳይደረስ በኢትዮጵያ ለሳምንታት የዘለቀ ቆይታውን አጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የብድር ስምምነት ላይ ሳይደርስ በኢትዮጵያ ለሳምንታት የዘለቀውን ቆይታውን አጠናቀቀ።
የድርጅቱ ተወካዮች አዲስ አበባ መጥተው በብድር ጉዳይ ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ዕቅዷን ለመተግበር የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ ከተቋሙ መጠየቋን ተከትሎ ነው።
አይኤምኤፍ የጉብኝቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በድርጅቱ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አልቫሮ ፒሪስ የተመራ ቡድን ከመጋቢት 10 አስከ 24/2016 ዓ.ም. ለሁለት ሳምንታት ያደረገውን ቆይታ ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በመግለጫው ፒሪስ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ አይኤምኤፍ የአገሪቱን የምጣኔ ሃብት ፕሮግራሞች መደገፍ በሚችልበት ሁኔታ አዎንታዊ ንግግሮች ማድረጋቸውን እና ውይይቱ በቀጣይ ሳምንታት በዋሺንግተን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአይኤምኤፍ ጉብኝት መጠናቀቅን አስመልክቶ ሮይተርስ ባወጣው ዘገባ አይኤምኤፍ የብድር ስምምነት ሳይደርስ የኢትዮጵያ ቆይታውን ማጠናቀቁ አገሪቱ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎቿ የሚጠበቅባትን እንዳትወጣ እክል ይሆናባታል ብሏል።
የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አብዱልመናን መሐመድ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ብድር የማታገኝ ከሆነ ለአገሪቱ መንግሥት ትልቅ ራስ ምታት ይሆናል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ ለመክፈል የአገር ውስጥ የገቢ ምንጭ ያስፈልጋታል። የውጪ ዕዳ ለመክፈል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል። ይሄ በአገሪቱ በጀት እና የውጭ ምንዛሬ ላይ ትልቅ ጫና ይኖረዋል” ብለዋል።
አይኤምኤፍ ብድር የሚሰጠው ወይም የብድር ሽግሽግ የሚያደርገው የሚያስቀምጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑን ዶ/ር አብዱልመናን ያስረዳሉ።
“ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ብድር ስትቀበል ተቀምጠው ከነበሩት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሪፎርም ማድረግ፣ የገንዘብ ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የውጪ ምንዛሬ ተመኑን እና የበጀት ጉድለትን ማስተካከል ይገኙበታል።”
እንደ ዶ/ር አብዱልመናን ከሆነ አይኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ብድር ለመስጠት ወይም የብድር ሽግሽግ ለማድረግ በቀዳሚነት ከሚያስቀምጣቸው ጉዳዮች መካከል የውጭ ምንዛሬ ዋጋን ማስተካከል ቀዳሚው እንደሚሆን ይገልጻሉ።
“ትልቁ ፈተና የሆነው የውጭ ምንዛሬ ጉዳይን ማስተካከል ነው። በባንኮች እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፍቷል። መንግሥት ይህን ላስተካክለ ብሎ ቢነሳ ሊመጣ የሚችለው የኢኮኖሚ ቀውስ ያስፈራው ይመስለኛል። የዋጋ ግሽበት በአንዴ ሊመጣ ይችላል” በማለት መንግሥት ያለበትን አጣብቂኝ ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም ቻይናን የማይጨምረው ገንዘብ አበዳሪ አገራት ስብሰብ የሆነው 'ፓሪስ ክለብ' ኢትዮጵያ እስከ መጋቢት 22/2016 ዓ.ም. ድረስ ከአይኤምኤፍ ብድር የማታገኝ ከሆነ እስከ 2025 መክፈል ያለባትን ብድር ለማገድ የተደረሰውን ስምምነት ውድቅ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በዚህኛው ንግግር ከአይኤምኤፍ ጋር ከስምምነት መድረስ ሳትችል መቅረቷን ተከትሎ የፓሪስ ክለብ አባል አገራት የብድር መክፈያ ቀነ-ገደብ ያራዝሙ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ኢትዮጵያ እአአ 2022 ማብቂያ ላይ ከአይኤምኤፍ ጋር የነበራት የብድር ስምምነት ካበቃ ወዲህ ከገንዘብ ተቋሙ ታገኝ የነበረው የፋይናንስ ድጋፍ ተቋርጦ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ኅዳር 2016 ላይ መክፈል ይጠበቅባት የነበረውን 1 ቢሊዮን ዶላር ዮሮቦንድ በጊዜው መክፈል ሳትችል ቀርታ ብድር በወቅቱ መከፍል ያልቻሉ የአፍሪካ አገራት ዝርዝር ውስጥ ተካታለች።
ለሁለት ዓመታት ከዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ገና እያገገመች ያለችው ኢትዮጵያ፤ ምጣኔ ሃብቷ በከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና እየጨመረ በመጣ የውጭ ብድር ክፍያ እየተፈተነ ይገኛል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የአገሪቱን መንግሥት አሃዝ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ኢትዮጵያ ወደ 28.2 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ብድር ያለባት ሲሆን፣ ከዚህ መካከል 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልገው ቦንድ ኅዳር 2017 ዓ.ም. መከፈል አለበት።












