ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ በኢትዮጵያ ተጥሷል ያለችው የመርሆች ስምምነት ምንድነው?
ኢትዮጵያ አራተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ማካሄዷን ተከትሎ ግብጽ የኢትዮጵያ ተግባር የመርሆች ስምምነትን የጣሰ ነው ብላለች።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ጷጉሜ 5/2015 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ ሙሌት ያከናወነችው ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2015 (መጋቢት 14፣ 2007 ዓ/ም) ላይ የተፈራረሙት መርሆዎች ስምምነትን በሚጥስ ሁኔታ ነው ብላለች።
ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር በተፈራረምኩት የመርሆች ስምምነት መሠረት ግድቡ በውሃ የሚሞላው እና ኦፕሬሽን የሚካሄደው አስገዳጅ ስምምነት ሲደረስ ብቻ ነው ትላለች።
ከዚህ ቀደም ግብጽም ሆነች ሱዳን በተለይም የሕዳሴ ግድብ ሙሌትም ጋር ተያይዞ በሚያወጧቸው የተቃውሞ መግለጫዎች ሦስቱ አገራት የደረሱትን የመርሆችን ስምምነት በመጥቀስም ይሟገታሉ።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ድንበር ተሻገሪ የሆነው የአባይ (ናይል) ወንዝ በአገራቱ ላይ የሚኖረው ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታን ከግምት በማስገባት ከስምንት ዓመታት ገደማ በፊት መጋቢት 14/2007 ዓ.ም በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ በ10 መርሆች ላይ ከስምምነት ደርሰው ነበር።
የትብብር መርህ
ሦስቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነት፣ ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ እና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ የላይኛው እና የታችኛው የተፋሰስ አገራት ፍላጎትን መሠረት በማድረግ ለመተባበር ተስማምተዋል።
የልማት፣ ቀጠናዊ ትስስር እና ዘላቂነት መርህ
ሦስቱ አገራት በሱዳን መዲና በደረሱት የመርሆች ስምምነት ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓላማ ምጣኔ ሃብታዊ እድገትን የሚደግፍ፣ ድንበር ተሻጋሪ ትብብርን እና ትስስርን የሚያጠናክር ዘላቂ እና ከብክለት ነጻ የሆነ አስተማማኝ ኃይል ማመንጨት ስለመሆኑ ተስማምተዋል።
ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም
በዚህ መርህ መሠረት ሦስቱ አገራት የውሃ ድርሻቸውን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ከስምምነት ደርሰዋል።
አገራቱ በድንበራቸው ውስጥ የሚገኘውን የውሃ ሃብት የሚጠቀሙት ሥነ-መልዕክዓ ምድር፣ የአየር ሁኔታ፣ ሥነ-ምህዳራዊ እና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በውሃ ሃብት ላይ ሕይወቱን የመሰረት ሕዝብ ቁጥር እና የተፋሰሱ አባል አገር የውሃ አጠቃቀም በሌላኛው አገር ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እና ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት ሦስቱ አገራት የውሃ ድርሻቸውን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም መስማማታቸውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል።
ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስ መርህ
ሦስቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሠረት የትኛውም አገር የናይል ወንዝን ሲጠቀም በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አለማስከተሉን ማረጋገጥ አለበት።
ይሁን እንጂ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ሲረጋገጥ፤ ወንዙን በመጠቀሙ ጉዳት ያስከተለው አገር ጉዳት ከደረሰበት አገር ጋር በመወያየት ችግሩን መቅረፍ አለበት፤ አስፈላጊ ከሆነም በካሳ ጉዳይ ሊነጋገሩ ይችላሉ።
የግደቡ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን
የመርሆች ስምምነቱ አንቀጽ 5 ስለ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት እና አሰራርን በተመለከተ ስለሚደረግ ትብብር ያትታል።
ሦስቱ አገራት የግድቡን ዲዛይን እንዲሁም ግድቡ ለሦስቱ ተፋሰስ አገራት ሊያስገኘው ስለሚችለው እና ሊያስከትለው ስለችሚለው ጉዳት ጥናት እንዲያደርግ የተሰየመው የዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ በግደቡ የመጀመሪያ አሞላል ላይ በመመሪያዎች እና ደንቦች ለመገዛት ተስማምተዋል።
የመተማመን፣ የመረጃ ልውውጥ መርሆች
ሦስቱ አገራት በካርቱም ፊርማቸውን ያኖሩበት የመርሆች ስምምነት፤ ለግድቡ ግንባታ፣ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽን በተመለከተ መተማመን እንዲኖራቸው የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ በመርህ ደረጃ ከስምምነት ደርሰዋል።
ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴው ለሚያደርገው ጥናት መረጃዎችን ለመስጠት ተስማምተዋል።
የታችኛው የተፋሰስ አገራት ከሕዳሴ ግድብ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲገዙ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።
የግድቡ ደኅንነት፤ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርሆች
የግድቡ ደህንነት በተመለከተ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታው ወቅት የግድቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል ሪፖርት መተግበር ይጠበቅባታል።
ሦስቱ አገራት በቅን ልቦና ሆነው የናይል ወንዝን ለመጠበቅ እና የወንዙ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሉዓላዊነትን፣ የግዛት አንድነትን እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ ለመተባበር ተስማምተዋል።
አለመግባባቶችን በስላም የመፍታት መርህ
ሦስቱ አገራት በመካከላቸው በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ አለመግባባቶች ውስጥ ቢገቡ በመርህ ደረጃ አለመግባባቱን በሰላም ለመፍታት ከስምምነት ደርሰዋል።
ግጭት እና አለመስማማት መፍታትን በተመለከተ፤ የዚህ ስምምነት አተረጓጎም ወይም አፈጻጸም ተከትሎ የሚከሰት አለመግባባት በመልካም መርህ ላይ ተመስርቶ በውይይት ወይም በድርድር የሚፈታ ይሆናል ይላል የሦስቱ አገራት መሪዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት ስምምነት።
ይሁን እንጂ አለመግባባቱን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ካልተቻለ ጉዳዩን ወደ አገራቱ ርዕሰ ብሔሮች ሊወስዱት ይችላሉ።