ማንቸስተር ሲቲ በሃላንድ እና ፎደን ታግዞ በኦልድ ትራፈርድ ዩናይትድን ረታ

ማንቸስተር ሲቲ በማንቸስተር ደርቢ ዩናይትድን በቀላሉ በመርታት በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለውን ልዩነት አስፍቷል።

ኧርሊንግ ሃላንድ በሁለቱም አጋማሽ አንድ አንድ ግቦችን በማስቆጠር እንዲሁም አንድ ለጎል የሚሆን ኳስ በማመቻቸት ደምቆ አምሽቷል።

የፔፕ ጉዋርዲዮላ ቡድን ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ በኳስ ቁጥጥር ከተቀናቃኛቸው ልቀው ተገኝተዋል።

የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊት ባለፈው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን እንግሊዛዊው የቀድሞ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሰር ቦቢ ቻርልተንን ዘክረዋል።

ነገር ግን ኤሪክ ቴን ሃግ እና ተጫዋቾቻቸው የሰንበቱን ፍልሚያ መዘከር የሚሹት አይደለም።

በ26ኛው ደቂቃ ሃላንድ ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎል በመቀየር ሲቲ እንዲመራ አስችሏል።

ራሰመስ ሆይለንድ የሲቲውን አማካይ ሮድሪ ጎትቷል በሚል የተነሳውን ቅሬታ ተከትሎ ቪኤአር በድጋሚ ምስል ከተመለከተው በኋላ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ከሃላንድ የተሰነዘረውን የግንባር ኳስ በግሩም ሁኔታ ቢመልስም ከእረፍት በኋላ ሃላንድ ከበርናንዶ ሲልቫ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

የሲቲው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ከስኮት ማክቶሚናይ የተመታውን ኳስ በማዳን ቡድኑ ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አስችሏል።

ጨዋታው ሊገባደድ 10 ደቂቃዎች ገደማ ሲቀሩት ሃላንድ ለቡድን አጋሩ አመቻችቶ የሰጣትን ኳስ ፊል ፎደን ወደ ግብ በመቀየር ሲቲ ዩናይትድ ላይ ያለውን የበላይነት አጠናክሯል።

ምንም እንኳ ማንቸስተር ሲቲ በያዝነው የውድድር ዓመት እንደቀደመው ጊዜ አቋማቸውን ባያሳዩም የከተማ ተቀናቃኛቸውን መርታት ግን አልከበዳቸውም።

ሃላንድ ለጎል ያለው ጥማት ኃያል ሲሆን፣ የዩናይትዱ በረኛ አንድሬ ኦናና ሁለት ጊዜ ለግብ የቀረቡ ኳሶችን አውጥቶበታል።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን አጨዋወቱ ቅርፅ አልባ ሆኖ ነው ያመሸው። በተቃራኒው ሲቲ የተመጠነ፤ የተረጋጋ እና ልቡ ሙሉነት የታከለበት ኳስ አሳይቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የዩናይትድ ደጋፊዎች ጨዋታው ከመገባደዱ በፊት ስታድየሙን ለቀው የወጡ ሲሆን፣ ይህም ክለቡ ያለበት ቀውስ ማሳያ ነውም ተብሏል።

ዩናይትድ በጨዋታው የተወሰኑ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም የኤሪክ ቴን ሃግ ተጫዋቾች ጎል መፍጠር አልቻሉም። ወጣቱ ሆይለንድ ፍፁም ቅጣት ቢያሰጥም በደጋፊዎች ዘንድ እየተወደደ መጥቷል።

ቀያይ ሰይጣኖቹ ባለፈው የውድድር ዘመን በሜዳቸው ሲቲን በመርታት ወደፊት እየገሰገሱ እንደሆነ የሚጠቁም ፍንጭ ቢሰጡም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን ወደኋላ የሚሄዱ መስለው ቀርበዋል።