የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ፡ ናይጄሪያ ከአይቮሪ ኮስት - ዋንጫውን ማን ያነሳል?

የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ - ናይጄሪያ ከአይቮሪ ኮስት

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

ክብረ-ወሰን የሰበሩ ጎሎች፣ አስደናጋጭ ክስተቶች፣ ድራማ. . . የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ እሑድ የካቲት 3/2016 ዓ.ም. ናይጄሪያ ከአይቮሪ ኮስት በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።

ዘ ሱፐር ኢግልስ በተሰኘ ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ናይጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫን በአቢጃን ለማንሳት አልመዋል።

አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ደግሞ ከ2015 (እአአ) በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአህጉሪቱን ግዙፉን ዋንጫ አቅፋ ለመሳም ቆርጣ ተነስታለች።

ሁለቱ ቡድኖች አንድ ምድብ ውስጥ ነበሩ። በመጀመሪያው ጨዋታ ናይጄሪያ 1- 0 ማሸነፏ ይታወሳል።

እነሆ ከ24 ቀናት በኋላ ድጋሚ ተገናኝተዋል።

ዝሆኖቹ ከ2006 (እአአ) በኋላ ውድድሩን አዘጋጅተው ለፍፃሜ የደረሱ የመጀመሪያው ብሔራዊ ቡድን ሆነዋል። ለመጨረሻ ጊዜ ይህን ያደረገችው ግብፅ ናት።

ለፍፃሜ ከደረሱ ስድስት የውድድሩ አዘጋጆች አምስቱ ዋንጫውን ሲያነሱ በ2000 ዋንጫውን አዘጋጅታ ለፍፃሜው ደርሳ ድል ያልቀናት ናይጄሪያ ናት።

በዚህ ውድድር ናይጄሪያ ምንም ሽንፈት ሳትቀምስ ነው ለፍጻሜው ጨዋታ የበቃችው። ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በብሔራዊ ቡድኖች ሰንጠረዥ ከአህጉሩ ስድስተኛ ከዓለም 42ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

አይቮሪ ኮስት ደግሞ በአፍሪካ ስምንተኛ፤ በዓለም 49ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ምድቧን በ7 ነጥብ በመምራት፤ ቀጥሎ ደግሞ በጥሎ ማለፉ ካሜሩን፣ አንጎላን እና ደቡብ አፍሪካን በመርታት ለፍፃሜው የበቃችው ናይጄሪያ ከ2013 (እአአ) በኋላ ድጋሚ ዋንጫውን ለማንሳት ትፋለማለች።

አይቮሪ ኮስት ደግሞ በናይጄሪያ ከቀመሰችው ሽንፈት በኋላ በኢኳቶሪያል ጊኒ 4 - 0 መሸነፏ አይዘነጋም። ይህ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪኳ እንዲሁም በሜዳዋ ትልቁ ሽንፈት ነው።

ዝሆኖቹ ከምድባቸው ያለፉት ምርጥ ሦስተኛ ሆነው ነው። በጥሎ ማለፉ ድራማዊ በሆነ ክስተት ሴኔጋልን፣ ማሊን እና ዲሞክራቲከe ኮንጎን በመርታት ለፍፃሜው በቅተዋል።

በዋና ከተማዋ አቢጃን የሚገኘው 60 ሺህ ተመልካች የሚይዘው ትልቁ ስታድየም ፍፃሜውን እንዲያስተናግድ ተመርጧል።

ሉክማን እና ኦሲምሄን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሉክማን እና ኦሲምሄን

ምንም እንኳ ናይጄሪያ በማይደክማቸው የአይቮሪ ኮስት ደጋፊዎች ፊት ብትጫወትም ይህ የሚበግራት አትመስልም።

በአውሮፓውያኑ 2022 የናይጄሪያ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የስፖርቲንግ ሊዝበን እና የፖርቶ አሠልጣኝ ሆዜ ፔሴይሮ ከናይጄሪያውያን ከፍተኛ ትችት ሲሰነዝርባቸው ነበር።

ነገር ግን ዘ ሱፐር ኢግልስን ይዘው ለፍፃሜው በቅተዋል። ናይጄሪ ዋንጫውን ካነሳች ከአውሮፓውያኑ 1980፣ 1994 እና 2013 በኋላ አራተኛው ክብሯ ይሆናል።

በቀድሞው የዋትፈርድ ተጫዋች ዊሊያም ትሩስት-ኤኮንግ የሚመራው የናይጄሪያ ተከላካይ መስመር አድናቆት ተችሮታል።

ናይጄሪያ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች 2 ግቦችን ብቻ ነው ያስተናገደችው። በተቃራኒ ቡድን መረብ ላይ ደግሞ 7 ግቦች አስቆጥራለች።

እርግጥ ነው የ2023 የአፍሪካ ምርጡ ተጫዋች የተባለው የናፖሊው ኮከብ አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠሩ ብዙዎችን አስገርሟል።

ቢሆንም አንዳች ድካም ሳይሰማው ለቡድኑ በሚሠራው ሥራ ከበርካታ ተንታኞች አድናቆትን አትርፎለታል።

“እሱ ኮከብ ተጫዋች ነኝ ብሎ አይቆምም። ለቡድኑ ነው የሚታገለው” ይላሉ አሠልጣኝ ፔሴይሮ።

የጣሊያኑ አታላንታ አጥቂ አዴሞላ ሉክማን ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል፤ አምበሉ ትሩስት-ኤኮንግ ደግሞ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች በስሙ ተመዝግበዋል።

ኒኮላስ ፔፔ ከአሠልጣን ፋየ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኒኮላስ ፔፔ ከአሠልጣን ፋየ ጋር

የአይቮሪ ኮስቱ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ኤሜርሴ ፋየ “ሊሰጥም የነበረ መርከብ በማዳኑ” ከናይጄሪያው አቻው ውዳሴ ተችሮታል።

አሠልጣኝ ዦን-ሉዊ ጋሴት ከምድብ ጨዋታዎች በኋላ ከኃላፊነታቸው ሲነሱ የቀድሞው የአይቮሪ ኮስት ተጫዋች ፋየ ቦታውን ተረከበ።

ከዚህ በኋላ ነው አይቮሪ ኮስት በአስደናቂ ሁኔታ ሴኔጋል እና ማሊ በጥሎ ማለፉ ረትታ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ በግማሽ ፍፃሜው ዲሞክራቲክ ኮንጎን በማሸነፍ ለፍፃሜው የበቃቸው።

የጋሴት ምክትል የነበረው ፋየ የፈረንሳዩ ክለብ ኒስ ታዳጊ ክለብ እና የክሌሞን ተጠባባቂ ቡድን አሠልጣኝ ሆኖ ከማገልገል ያለፈ ልምድ የለውም።

“ቡድኑን ላለፉት ሁለት ዓመታት በማወቄ ዕድለኛ ነኝ” የሚለው ፋየ “እኔ ብዙ አድናቆት አይገባኝም” በማለት የሚጎርፍለትን አድናቆት በትህትና ይመልሳል።

በ2006 የአፍሪካ ዋንጫ አንድም ደቂቃ ሳያርፍ አገሩ በፍፃሜው እስክትረታ ድረስ ያገለገለው ፋየ በህመም ምክንያት በ28 ዓመቱ ነው ከእግር ኳስ ተጫዋችነት የተሰናበተው።

አሁን አይቮሪ ኮስት ሦስተኛ የአፍሪካ ዋንጫዋን እንድታነሳ ለማድረግ አቅዷል።

ያለፉት አራት የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜዎች 90 ደቂቃ ተሻግረው፤ ተጨማሪ 30 ደቂቃ አልፈው፤ በፍፁም ቅጣት ምት ነው የተጠናቀቁት።

በግማሽ ፍፃሜው ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ሴባስቲያን አለር ከጉዳት የተመለሰ ሲሆን፣ አገሩን ለድል ሊያበቃ እንደሚችል ብዙዎች ያምናሉ።

ዋንጫውን ማን ያነሳዋል የሚለውን ለመገመት ቢያዳግትም የፍፃሜው ጨዋታ ውጥረት እና ፍትጊያ የተሞላበት እንደሚሆን እሙን ነው።