“በዘረኝነት ጥቃት ተፈትኖ ወደ ባለሃብትነት ያደረሰኝ የሕይወት ጉዞ”

ሳንሚ አዲጎኬ

የፎቶው ባለመብት, A&O STUDIOS

ሳንሚ አዲጎኬ ሥራ ሲጀምር በቤቶች ግንባታ እና ሽያጭ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል ከንግዱ ዓለም ጋር ግንኙነት አልነበረውም።

አሁን ላይ ግን ጥቂት ጥቁር ሥራ አስፈጻሚዎች ባሉበት በዚህ ዘርፍ ከዜሮ ተነስቶ የራሱን ድርጅት በማቋቋም ስኬታማ መሆን ችሏል።

አዲጎኬ ከወላጆቹ ጋር ከናይጄሪያ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሄደው በአውሮፓውያኑ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር።

ያኔ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ታዳጊ ነበር።

ለታዳጊው አዲጎኬ ሕይወት በዩኬ ቀላል አልነበረም። ገና በልጅነቱ ዘረኝነትን ለመጋፈጥ ተገዷል።

ወደ ሥራው ዓለም ከተቀላቀለ በኋላ ሥራ የጀመረው ፈጣን ምግቦችን በሚያቀርበው በደቡባዊ ለንደን በሚገኘው ማክዶናልድስ ውስጥ ነበር።

አዲጎኬ አንዳንድ ሰዎች የሥራ ቦታው ድረስ ሄደው የዘረኝነት ስድቦችን ይሰነዝሩበት እንደነበር ያስታውሳል።

ባስ ሲል ደግሞ “አንተ እንድታስተናግደን አንፈልግም” ይሉኝ ነበር ይላል።

የያኔው ታዳጊው አዲጎኬ እነዚህን ሁሉ የዘረኝነት ጥቃቶች ችሎ ከመኖር ውጪ ምንም ምርጫ አልነበረውም።

ማክዶናልድስ እንደዚህ ዓይነት ደንበኞችን የሚታገስ ባይሆንም የሚከተለው የክርስትና እምነቱ ጥቃቶቹን ለመቋቋም ጥንካሬ እንደሰጠው ይናገራል።

“ፈጣሪ ሁሉንም ሰው ይወዳል፤ እናንተ ግን ይህንን የዘነጋችሁ ናችሁ እላለሁ” ይላል።

በዚህ ሁኔታ በማክዶናልድስ የሥራ እድገቶችን አግኝቶ በአስተዳደር ቦታ ላይ መድረስ ችሏል።

አዲጎኬ እንደሚለው ሕይወቱን በሚያስደንቅ መልኩ የቀየረው እና አሁን ወዳለበት ስኬት ያንደረደረው አንድ የሥራ ባልደረባው የሰጠው መጽሐፍ ነበር።

መጽሐፉ በሮበርት ቲ ኪዮሳኪ የተጻፈው ‘ሪች ዳድ ፑር ዳድ’ የሚለው ነበር። መጽሐፉ ከማኅበረሰቡ ለመቅደም እንደ ሪል ስቴት (መኖሪያ ቤቶች) ግንባታን በመሳሰሉ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን ያበረታታል። ይህም ለአዲጎኬ ተነሳሽነትን ፈጥሮለታል።

ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በዩኬ የንብረት ገበያ ላይ ገንዘቡን ማፍሰስ ጀመረ። ቤቶቹ ገና ሳይገነቡ የመኖሪያ አፓርታማዎችን መግዛት እና መሸጥ ጀመረ።

ምንም እንኳን እንደ አውሮፓውያኑ በ2008 ላይ የገንዘብ ቀውስ አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ በ2023 የራሱን ‘ሮሆቦት ፕሮፐርቲ ግሩፕ’ ለማቋቋም ያስቻለውን ጥሩ ገንዘብ ሠራ።

የቤቶች ግንባታ እና ሽያጭ ንግዱ ግን ለእርሱ ቀላል አልነበረም።

አዲጎኬ ድርጅቱ እድሳት ያደረገለት አዳራሽ ውስጥ ቆሞ
የምስሉ መግለጫ, የአዲጎኬ ቡድን በመጀመሪያ ሥራው በደቡብ ለንደን ካምቤርዌል ውስጥ የሚገኘውን አዳራሽ አድሷል።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የባሜ (BAME ) የቤቶች ግንባታ እና ሽያጭ ኩባንያ መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት ፕሪያ አጋርዋል ሻህ ወደዚህ ንግድ ለመግባት ከሰዎች ጋር ግንኙነት ከሌለ ከባድ ነው ይላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ገንዘብ ያላቸውን ሰዎች ማወቅ እና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት መፍጠር ወሳኝ ነው።

በመሆኑም ከማንም ጋር ግንኙነት ያልነበረው አዲጎኬ፣ ሊረዱት ከሚችሉት ሰዎች ጋር ለመገናኘት አድራሻዎችን ለመፈለግ ወሰነ። በዚህም በለንደን የሚኖሩ አብዛኞቹ ጥቁር የሆኑ የእምነት ማኅበረሰቦችን አገኘ።

አዲጎኬ ናይጄሪያ እያለ ገና ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ይሄድ ነበር። ወደ ለንደን ከሄደ በኋላም ተመሳሳይ የእምነት ተቋምን ተቀላቅሏል።

በዩኬ ላለፉት አስርት ዓመታት ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቀንሰዋል። በዚህም ምክንያት በኢንግላንድ ያለ ቤተክርስቲያን ቀስ በቀስ ንብረቶቹን ሸጧል።

ደቡብ ለንደን ግን እንደ አዲጎኬ ባሉ ስደተኞች ምክንያት ይህንን ውሳኔ ተቃውማለች።

በደቡብ ለንደን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እሑድ እሑድ የሚያመልኩባቸው እና ጥቁሮች በብዛት የሚገለገሉባቸው ከ250 በላይ አብያተ ክርስቲያናት አሉ።

አድጎኬ ንግዱን ማሳደግ የጀመረውም ያረጁ የመዝናኛ ቦታዎችን በማደስ እና ወደ አምልኮ ቦታ በመለወጥ ነበር።

በመጀመሪያ የሠራቸው ፕሮጀክቶቹም በደቡብ ለንደን ካምብረዌል የሚገኝ የቢንጎ አዳራሽ እድሳት እና ውልዊች ማጂስትሬትስ ፍርድ ቤትን ወደ ሃይማኖት መገልገያ ቦታ መቀየርን የሚያካትቱ ነበሩ።

ከዚያም የተለያዩ ሕንጻዎችን በማደስ እና ያረጁ መጠጥ ቤቶችን እና ፖሊስ ጣቢያዎችን ወደ ጥሩ የሥራ ቦታነት፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽነት እና የፕሮግራም [ኤቨንት] ማዘጋጃ ስፍራነት በመለወጥ ሥራውን አሰፋ።

አሁን ላይ በአዲጎኬ የተመሠረተው የሮሆቦት ግሩፕ ከ20 በላይ ትላልቅ የእድሳት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ድርጅቱም ከ35 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሚያወጣ ሃብት ያለው ሲሆን፣ ከ20 በላይ ሠራተኞች አሉት።

አዲጎኬ በዚህ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ይናገራል። ምክንያቱም ለበርካታ ዓመታት የዩኬ የንብረት ልማት ዘርፍ ለብዝሃነት እና ችሎታን ለማሳደግ በር እንደማይከፍት ተገንዝቧል።

ወደ የጋራ መኖሪያ ቤት የተለወጠው በሰሜን ለንደን በካምደን የሚገኘው መጠጥ ቤት

የፎቶው ባለመብት, REHOBOTH

የምስሉ መግለጫ, የአዲጎኬ ድርጅት በሰሜን ለንደን በካምደን የሚገኘውን መጠጥ ቤት ወደ የጋራ መኖሪያ ቤት እና ፕሮግራሞች ማሰናጃነት እንዲቀየር ረድቷል።

ባለፈው ዓመት ‘በአክሽን ሰስቴኔብሊቲይ ኮንሰልታንሲ’ የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየው አካባቢን ከመገንባት ጋር በተገናኘ በተሰማሩ ድርጅቶች ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚመጡ ሰዎች 13. 6 በመቶ የሚሆነው የሠራተኛ ኃይል ይሸፍናሉ።

ይህ የሮያል ተቋም እንደ አውሮፓውያኑ 2016 ባወጣው የዳሰሳ ጥናት ከተገለጸው 1.2 በመቶ የተሻለ ቢሆንም፣ አሁንም አሃዙ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ካስቀመጠው መመዘኛ 18.5 በመቶ በታች ነው።

አጋርዋል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥቁሮች እና በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውክልና ሁኔታ እየተሻሻለ ነው ይላሉ። ሆኖም ዘርፉ አዲስ ተሰጥኦን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ አይደለም የሚሉት አጋርተዋል፣ ብዝሃነት በሥራ አስፈጻሚነት ደረጃ በሚያስገርም ሁኔታ መቀነሱን ተናግረዋል።

በቤቶች ግንባታ እና ሽያጭ ገበያ ላይ መረጃ እና ትንተና የሚሰጠው ኢስቴት ጋዜት መጽሔት በ2021 ለሠራው የዳሰሳ ጥናት አነስተኛ ቁጥር ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ባቀረበው መጠይቅ 84 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ዘረኝነት በሥራ ላይ ትልቁ ፈተና እንደሆነ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል 75 በመቶዎቹ ራሳቸው ላይ እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

የቤቶች ግንባታ እና ሽያጭ ንግድ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚናገሩት አጋርዋል፣ ብዙ ገንዘብ አውጥቶ ንብረት ለመግዛት ሰዎችን ማመን ይጠይቃል።

“ስለዚህ የምንመሠርተው ግንኙነት አድሏዊ ይሆናል፤ በመሆኑም ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ከሆኑ ሰዎች ጋር መሥራት እንፈልጋለን” ብለዋል።

ለዚህም ነው አነስተኛ ቁጥር ካላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የመጡ እና በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ እንደ አዲጎኬ ያሉ ሰዎች የራሳቸውን ድርጅት የመሠረቱት ይላሉ።

አዲጎኬ አሁን ላይ ለደረሰበት ስኬት ከሚያውቀው ነገር መነሳቱ እንደረዳው ይናገራል።

“ለውጥ ሒደት ነው” የሚለው አዲጎኬ፣ ልጆቹ በእርሱ ላይ የደረሰው ዘረኝነት እንደማይገጥማቸው እምነት አለው።

ከእርሱ ታሪክ ብዙ እንደሚማሩም ተስፋ አድርጓል።