ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ፖሊስ 600 ሺህ ዩሮ የሚያወጣ ሻምፓኝ ሰርቀው ያመለጡ ሌቦችን አሳዶ ደረሰባቸው
የፈረንሳይ ሌቦች 600 ሺህ ዩሮ የሚያወጣ ሁለት የጭነት መኪና ሻምፓኝ ሰርቀው ቢያመልጡም ፖሊስ አሳዶ ደርሶባቸዋል።
ገንዘቡ በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ስሌት ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።
ክስተቱ የተፈፀመው ዕለተ ቅዳሜ ሪምዝ በተሰኘው የፈረንሳይ የሻምፓኝ መናኸሪያ ነው።
ሁለቱ ሻምፖኝ የጫኑ መኪናዎች መሰረቃቸውን የሰማው ፖሊስ ሌቦችን አሳዶ ሊደርስባቸው ችሏል።
የፖሊስ መኮንኖች ሌቦችን ሊደርስባቸው የቻለው የጭነት መኪናዎቹ የት እንዳሉ የሚጠቁም ቴክኖሎጂ ስለተገጠመባቸው ነው።
ከሪምዝ ከተማ ወደ ፓሪስ በሚያቀናው ሰፊ ጎዳና ላይ ነው ፖሊስና ሌባ ሲሯሯጡ የታዩት።
ሁለት የጭነት መኪና ሻምፓኝ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቢገባም ሌቦች ለጊዜው አምልጠዋል።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት መኪናዎቹ ከሻምፓኝ አምራቹ ኩባንያ የተሰረቁት ከአርብ ምሽት እስከ ቅዳሜ ንጋት ባለው ጊዜ ነው።
ለ ፓሪዚያን ጋዜጣ እንደዘገበው ከተሰረቁት ጠርሙሶች መካከል ሞየ እና ሻንዶን የተሰኙ እጅግ ታዋቂ የሻምፓኝ ዓይነቶች ይገኙበታል።
ሁለቱ የጭነት መኪናዎች 600 ሺህ ዩሮ የዋጋ ተመን ያላቸው የሻምፓኝ ጠርሙሶች እንደያዙ ተተምኗል።
ሌቦቹ የጭነት መኪናዎቹን እያበረሩ ወደ ፓሪስ ሊደርሱ 20 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው ነው ፖሊስ የደረሰባቸው።
ሁለት የፖሊስ መኪናዎች ሌቦች እያሳደዱ ሳለ ሌቦች በፍጥነት አቅጣጫ በመቀየር ሊሸውዷቸው ሲሞክሩ ታይተዋል።
ከሁለት የጭነት መኪናዎች አንዱ በፖሊስ ሲከበብ ሲያሽከረክር የነበረው ሌባ ዘሎ አምልጦ በሌላ መኪና ከሥፍራው ተሰውሯል።
ሁለተኛው የጭነት መኪና ደግሞ ከፍጥነት መንገዱ መውጫ ላይ ሲቃረብ ሾፌሩ ወርዶ መኪናውን ጥሎ ፈርጥጧል።
ፖሊስ የሌቦቹን ማንነት ለማግኘት ምርመራ ከፍቷል።
የሻምፓኝ ጠርሙሶቹ ከአነስተኛ መንገራገጭ ውጭ ምንም ዓይነት አደጋ ሳይደርስባቸው ለኩባንያው ተመልሰዋል።