ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ሩቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይሰጡ ቀሩ

የፎቶው ባለመብት, William Samoei Ruto/FB
ለይፋዊ ጉብኝት ኬንያ ናይሮቢ የሚገኙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጋራ ይሰጡታል የተባለው ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይካሄድ ቀረ።
አስከ ሐሙስ ድረስ በናይሮቢ የሚቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሁለቱ አገራት ግንኙነት እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
ትናንት ማክሰኞ የካቲት 19/2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ኬንያ ናይሮቢ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት (ስቴት ሐውስ) አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ዐቢይ፤ በአገሪቱ የክብር ዘቦች ታጅበው ወደ ስቴት ሐውስ የገቡ ሲሆን፣ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶላቸዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስቴት ሐውስ በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አቀባበል ከተደርገላቸው የሁለቱ አገራት መሪዎች በጋራ ለጋዜጠኞች መግለጫ ለመስጠት ዕቅድ ይዘው ነበር።
ይሁንና ሁለቱ መሪዎች ወደ ውስጥ ከገቡ ከደቂቃዎች በኋላ “በዕቅድ ለውጥ ምክንያት” ጋዜጣዊ መግለጫው እንደማይኖር በቦታው ተገኝተው ሲጠባበቁ ለነበሩት ዘጋቢዎች ተነግሯል። የዕቅድ ለውጡ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ግን አልተገለጸም።

የፎቶው ባለመብት, @WilliamsRuto
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ፕሬዝዳንት ሩቶ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያ እያደረጉት ያለው መንግሥታዊ ጉብኝት፤ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ነው።
ትናንት ኬንያ ሲደርሱ ከፕሬዝዳንት ሩቶ ሞቅ ያለ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ የሚያርፉበት ሆቴል ከመሄዳቸው በፊት በ“ሳሚር ቢዝነስ ፓርክ” የሚገኘውን የአይሲቲ መሠረተ ልማትን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ የካቲት 18/2016 ዓ.ም. በተጀመረው እና እስከ አርብ ድረስ በሚቆየው ስድስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ በነገው ዕለት እንደሚገኙ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ጉብኝታቸው ላይ በደኅንነት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ላይ ከፕሬዝዳንት ሩቶ ጋር እንደሚወያዩ የኬንያው ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል።
የሁለቱ መሪዎች ንግግር በተለይ ኢትዮጵያ የላሙ ወደብን በምትጠቀምበት መንገድ ላይ እንደሚያተኩር ዘገባው አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኬንያ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት ሐሙስ ዕለት ሲያጠናቅቁ፣ ለሦስት ቀናት ጉብኝት የኬንያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ታንዛኒያ እንደሚያቀኑ ተነግሯል።
በታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን ግብዣ ወደ ዳሬ ሰላም የሚሄዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነቶች ላይ እንደሚነጋገሩ የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ሁለቱ መሪዎች በአየር ትራንስፖርት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ በግብርና እና በሌሎችም መስኮች ላይ በመወያየት ያላቸውን የቀደመ ግንኙነት የሚያጠናክር ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።












