ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ካናዳ ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት መወሰኗ ለንግድ ስምምነቱ አደጋ ነው አሉ
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና ለመስጠት ማቀዳቸውን ካስታወቁ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ ጋር የንግድ ስምምነት ለማድረግ "በጣም ከባድ ይሆናል" አሉ።
የትራምፕ የንግድ ማስፈራርያ የተሰማው ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት የሌላቸው አገራት ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ለመጣል አንድ ቀን ሲቀረው ነው።
ካናዳ እና አሜሪካ ዛሬ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ከዓርብ ጀምሮ ለአሜሪካ በምትሸጣቸው አብዛኛዎቹ ዕቃዎች ላይ የ35 በመቶ ታሪፍ ይጣልባታል።
ካናዳ ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና ለመስጠት ማቀዷን ያስታወቀችው የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግሥታት ውሳኔን ተከትላ ነው።
በጋዛ ውስጥ ያለው ረሃብ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ሰባት ተጨማሪ ሰዎች በምግብ እጥረት መሞታቸውን አስታውቋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ "እውነተኛ ረሃብ" እንዳለ ተናግረው፣ "ነገሮችን ለማስተካከል" ከእስራኤል ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።
የዩናይትድ ስቴትስ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ዛሬ በእስራኤል ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ካናዳ ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ ይፋ ካደረገች ከ12 ሰዓታት በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።
"ዋው! ካናዳ ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ አስታውቃለች።ያ ከእነሱ ጋር የንግድ ስምምነት ለማድረግ በጣም ከባድ ያደርግብናል። ኦ ካናዳ !!!"
ከአሜሪካ ጋር የንግድ ሥምምነት ላይ ያልደረሱ አገራት ላይ የሚጣለው ከፍተኛ ታሪፍ ተግባራዊ ሊሆን የቀረው ጥቂት ሰዓታት ብቻ ናቸው።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል። እነዚህ አገራት ለአሜሪካ በሚሸጧቸው ዕቃዎች የተለየ ዋጋ ይኖራቸዋል።
ነገር ግን ሌሎች አገሮች፣ ቻይና እና ሜክሲኮን ጨምሮ፣ እስካሁን ከስምምነት መድረስ አልቻሉም።
ትራምፕ እአአ ከነሐሴ 1 በፊት ስምምነቶች ላይ መደረስ እንዳለበት ይፋ ካደረጉ ቆይተዋል።
ያ ካልሆነ ግን አገራቱ ወደ አሜሪካ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ይጣላል።
በጋዛ ባለው አስከፊ ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ዓለም አቀፍ ቁጣ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፕሬዚዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ዛሬ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር እንደሚገናኙ ተነግሯል።
የዩናይትድ ስቴትስ ልዑክ የጋዛ ነዋሪዎች በከፍተኛ ረሃብ እየተሰቃዩ ባለበት ወቅት ነው በመካከለኛው ምሥራቅ የደረሱት።
ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጦት በጋዛ በየቀኑ በርካታ ሰዎችን መግደሉን ቀጥሏል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ዊትኮፍ በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈውን አወዛጋቢውን የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን የእርዳታ ጣቢያዎችን ይጎበኛሉ።
ባለፈው ሳምንት የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ድርድር ከተቋረጠ በኋላ በሐማስ ላይ ከፍተኛ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ የዛቱትን የእስራኤል ባለስልጣናትም አግኝተው ያነጋግራሉ።
በጋዛ፣ የእስራኤል ጦር አንዳንድ አዳዲስ እርምጃዎች ቢወሰድም፣ የተባበሩት መንግሥታት አሁንም እርዳታ ለመስጠት አዳጋች ሆኖበታል።
አብዛኞቹ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ተስፋ በቆረጡ እና በተራቡ ሰዎች ተዘርፈዋል።
በትናንትናው ዕለት በአካባቢው የሚገኝ አንድ ሆስፒታል ቢያንስ 48 ሰዎች በስተሰሜን በሚገኝ የደንበር ማቋረጫ ላይ ምግብ በመጠባበቅ ላይ እያሉ ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል ብሏል።
የሞቱት እና የቆሰሉ ሰዎች በጋሪ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ እና ሌሎች ደግሞ ዱቄት ተሸክመው ሲሄዱ የሚያሳዩ ምስሎች ወጥተዋል።
የእስራኤል ጦር ወታደሮቹ የተኮሱት "የማስጠንቀቂያ ተኩስ" እንጂ "በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ቀጥታ አይደለም" ያለ ሲሆን፣ "መከላከያ ሠራዊቱ በተተኮሰው ጥይት ስለደረሰው ጉዳት ምንም መረጃ የለውም" ብሏል።
ጦሩ አክሎም "ታማኝ ባልሆኑ ምንጮች ይፋ የሆነው መረጃ" ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳን ለፍልስጤም በአገርነት እውቅና እሰጣለሁ ማለቷን "ለሐማስ ሽልማት ነው" ሲል ተችቶታታል።
በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።
ከነዚህም መካከል ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ኅብረት አባላት አገራት ይገኙበታል።