ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትኛው የወር አበባ መጠበቂያ ምርት ይስማማዎታል?
አብዛኛቹ ሴቶች የወር አበባን በሚመለከት የመጀመሪያ ያገኙት ትምህርት አጭር እና የተገደበ ነው።
በአመዛኞቹም ታምፖን ወይም ሞዴስ መጠቀም የሚለው ምርጫ ላይ ብቻ የተገደበ ነው።
ከእነዚህ ከተለመዱ ምርጫዎች ባሻገር አሁን ሰፊ የምርት አማራጮች አሉ። ይህም ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ እና የሚታጠቡ ምርቶችን፣ አነስተኛ ኩባያዎችን እና ሱሪዎችን ያካትታል።
ነገር ግን የትኛው ምርት ተስማሚ ነው የሚለውን ለመምረጥ ምርጫዎች ሊበዙ ይችላሉ። እነዚህ ምርቶች እንዴት እንደሚሰሩ እና እርጥበት የማያሳልፉ እንደሆነ ለማወቅ ማውጣት ማውረዱ አይቀርም።
በሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ የማህፀን ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ታምፐስት ሴቶች የሚስማማቸውን ምርጫ እንዲያገኙ እነዚህ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች እንዴት እንደሚሰሩ እና ጥቅም እና ጉዳታቸውን ይገልፃሉ።
የወር አበባ ካፕ (ኩባያ)
የወር አበባ ካፕ (ኩባያዎች) አነስተኛ እና ተጣጣፊ ሲሆኑ የሕክምና ቁሳቁሶች ከሚሰሩበት ሲልኮን ምርት ይሰራሉ።
ማህፀን ውስጥ ተጣጥፈው የሚገቡ ሲሆን፤ የወር አበባን ከመምጠት ይልቅ የማጠራቀም ሥራ ይሰራሉ።
ዶ/ር ታምፐስት የደም ፍሰት መጠን ወይም ልጆች መውለድን መሠረት በማድረግ የተለያዩ ዓይነት ኩባያዎች እንዳሉ ይናገራሉ።
ኩባያዎችን ሲጠቀሙ ንፅህናን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚገልፁት ሐኪሟ ኩባያዎችን ወደ ማህፀን ከማስገባት በፊት እጅን መታጠብ እና ኩባያዎችን ከተጠቀሙ በኋላ ደግሞ ማፅዳት አለባቸው ይላሉ።
ጥቅም
- አካባቢ በጣም ተስማሚ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርት
- ከታምፖን በሦስት እጥፍ የወር አበባ መያዝ ይችላል
- 12 ሰዓታት ጥቅም ላይ መዋል ይችላል
- ለዓመታት ጥቅም ላይ መዋል ይችላል፤ እስከ 10 ዓመት አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን አማካኙ የመጠቀሚያ ጊዜ ግን ከሁለት እስከ አራት ዓመት ነው።
- ወጪው ተመጣጣኝ
ጉዳት
- ወደ ማህፀን ለማስገባት እና ለማስወጣት ልምምድ ይጠይቃል
- የሚመችን ኩባያ ለማግኘት ጊዜ ሊወስድ ይችላል
- በተለይ በሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ለመቀየር ምቾት ሊነሳ ይችላል
- በየወሩ እንደ ሕክምና ቁሳቁስ ጀርም ለመግደል መፀዳት አለበት
- አንድ ጊዜ ምርቱን ለመግዛት ከ20 እስከ 25 ፓውንድ ያስወጣል
የወር አበባ የውስጥ ሱሪ
የወር አበባ የውስጥ ሱሪዎች እንደ ውስጥ ሱሪ (ፓንት) ተደርበው የሚጠለቁ እና የወር አበባን መምጠጥ እንዲችሉ ተደራራቢ ጨርቆች የተሰፉላቸው ናቸው። እንደ መደበኛ ሱሪዎች ታጥበው ከደረቁ በኋላ ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
ለሌሊት ወይም የወር አበባ ፍሳሽ ቀለል በሚልባቸው ቀናት በጣም የተለመዱ ናቸው።
የወር አበባ ከመጠበቂያ ምርቶች አልፎ ይፈስሳል ወይም ልብስ ይነካል የሚለው ጭንቀት የተለመደ መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር ታምፐስት፤ የወር አበባ ሱሪዎች ለአብዛኞቹ ሴቶች አስተማማኝ እና ፍሳሽን ለመከላከል ተደራራቢ ንጣፎች እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጥቅም
- ማንኛውንም የውስጥ ሱሪ ይመስላሉ
- ሳይቀየሩ ከስድስት እስከ ስምንት ሰዓት መቆየት ይችላሉ
- ዳግም ጥቅም ላይ የሚውሉ እና ለአካባቢ ምቹ ናቸው፤ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት መቆየት ይችላሉ
- ለተጨማሪ ጥንቃቄ ከሌሎች ምርቶች ጋር ጥቅም ላይ መዋል ይችላሉ
ጉዳት
- ዋጋው ውድ ሊሆን ይችላል፤ ዋጋው ከ10 እስከ 50 ፓውንድ ድረስ ሊያስወጣ ይችላል
- ከአንድ አገልግሎት በኋላ መታጠብ እና መድረቅ አለበት
- ከፍተኛ ፈሳሽ ላለባቸው ሴቶች ፍሳሹን ለመምጠጥ በቂ ላይሆን ይችላል
- በጉዞ ወቅት ማጠቢያ ካልተገኘ ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ
- ቤት ካልሆኑ የተጠቀሙትን ይዞ ለመዋል ልትገደዱ ትችላላችሁ
የሚታጠቡ ፓዶች/ሞዴሶች
የሚታጠቡ ፓዶች ከአንድ ጥቅም በኋላ እንደሚወገዱ ከሚደረጉ ፓዶች ተመሳሳይ ናቸው። ነገር ግን በአብዛኛው ከጥጥ ወይንም ከቀርቅሃ የሚሰሩ እና በውስጥ ሱሪ በቁልፍ የሚታሰሩ ናቸው።
ከአንድ ጥቅም በኋላ ከማስወገድ ይልቅ ታጥበው እና ደርቀው ለዳግም አገልግሎት ይውላሉ።
ጥቅም
- ከፕላስቲክ ፓዶች ይልቅ ለስላሳ እና ምቹ ናቸው
- ለአካባቢ ተስማሚ እና ዘላቂ አማራጭ ለሚፈልጉ ሴቶች ተመራጭ ናቸው
- መጠናቸው እና የመምጠጥ አቅማቸው በርካታ አማራጮች አሏቸው
- ዋጋቸው ከጊዜ በኋላ የማይጎዳ ነው
- ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ድረስ መጠቀም ይቻላል
ጉዳት
- በእያንዳንዱ ጥቅም መታጠብ አለባቸው
- የቆዳ ኢንፌክሽን አደጋ እንዳይደቅኑ በደንብ መድረቅ አለባቸው
- በአንድ ጥቅም ከሚወገዱ ፓዶች በላይ ወፍራም ናቸው
- ከቤት ውጭ ከሆናችሁ የተጠቀማችሁትን ፓድ መያዝ ይኖርባችኋል
ለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ ፓዶች
ለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ ፓዶች ወይም ሞዴስ በጣም የተለመደ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርት ሲሆን፤ በውስጥ ሱሪ የሚለጠፍ እና ከአገልግሎት በኋላ ተጠቅልሎ የሚወገድ ምርት ነው።
ዶ/ር ታምፐስት ሞዴስን ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት መቀየር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩ ሲሆን አንድ ሞዴስ ከስምንት ሰዓት በላይ መጠቀም የቆዳ መቆጣት ሊያስከትል ይችላል ይላሉ።
ጥቅም
- ለመጠቀም ቀላል ነው
- በተለያዩ መጠኖች ይገኛል፤ ከስስ ሞዴሶች ጀምሮ በጣም ከባድ ፈሳሽ መሸከም እስከሚችሉ ሞዴሶች ገበያ ላይ ማግኘት ይቻላል
- ለሌሊት ሽፋን የተመቹ ናቸው
- የወር አበባ ለጀመሩ ታዳጊዎች የተሻለ ምቾት መስጠት ይችላል
ጉዳት
- ወፍራም እና ተንሸራታች ሊሆኑ ይችላሉ
- ዋናን ጨምሮ ለውሃ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተስማሚ አይደሉም
- አካባቢን ይጎዳሉ፤ አንድ እሽግ ሜዴል ከአምስት የፕላስቲክ ከረጢት (ዘንቢል) ጋር እንደሚስተካከል ዶ/ር ታምፐስት ይናገራሉ።
- ከጊዜ በኋላ ዳግም አገልግሎት ላይ ከሚውሉ ምርቶች አንፃር ውድ ይሆናሉ፤ ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ለወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች አምስት ሺህ ፓውንድ ገደማ ያወጣሉ።
ታምፖን
ታምፖን እንደ ሞዴስ በጣም የተለመዱ ምርቶች ሲሆኑ ማህፀን ውስጥ ገብተው የወር አበባን የሚመጡ ናቸው።
ዶ/ር ታምፐስት አወጋገዳቸው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ።
በየቀኑ 2.5 ሚሊዮን ታምፖኖች በቆሻሻ ቅርጫቶች ከመወገድ ይልቅ በመፀዳጃ ቤት ይጣላሉ።
ጥቅም
- በኪስ ለመያዝ አነስተኛ ናቸው
- ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ዋና ምቹ ናቸው
- የወር አበባን የመምጠት አቅማቸው ትልቅ ነው
ጉዳት
- ወደ ማህፀን ማስገባት ለአንዳንድ ሴቶች ምቾት ሊነሳ ይችላል
- ረጅም ሰዓት ከተደረጉ የጤና ስጋት ሊኖራቸው ይችላል
- አካባቢን ይበክላሉ
- ዳግም ጥቅም ላይ ከሚውሉ ምርቶች ጋር ሲነፃፀሩ ዋጋቸው ውድ ነው