በኢራን ለአራተኛ ቀን እየተካሄደ ባለው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የደህንነት አባል መገደሉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ

በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ ቪዲዮ ተቃዋሚዎች በፋሳ ከተማ የሚገኘውን የዋና አስተዳዳሪውን ቢሮ በር ሲሰብሩ አሳይቷል

የፎቶው ባለመብት, telegram

የምስሉ መግለጫ, በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ ቪዲዮ ተቃዋሚዎች በፋሳ ከተማ የሚገኘውን የዋና አስተዳዳሪውን ቢሮ በር ሲሰብሩ አሳይቷል

የኢራን የደህንነት ኃይሎች አባል የሆነ አንድ ግለሰብ በአገሪቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውደቁን ተከትሎ ለአራተኛ ቀን በቀጠለው ሕዝባዊ አመጽ ላይ መገደሉን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ከኢራን የፍትህ አካላት ጋር ግንኙነት ያለው ሚዛን የዜና ወኪል የክልሉን ዋና ዳኛ ሰኢድ ሻህቫሪን በመጥቀስ እንደዘገበው አሚር ሄሳም ኮዳያሪ የተባለ የደህንነት አባል ሐሙስ ዕለት በምዕራባዊ ሎሬስታን ግዛት በምትገኘው ኩዳሽት ከተማ ተገድሏል።

በርካታ የጸጥታ ኃይሎች አባላትም ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።

በኢራን፤ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውደቅን ተከትሎ በተቀሰቀሰው እና አራተኛ ቀኑን በያዘው ተቃውሞ ሰልፍ የወጡ የደቡባዊ ፋርስ ግዛት ነዋሪዎች የአካባቢውን አስተዳደር ሕንጻ ሰብረው ለመግባት ሞከረዋል።

በፋሳ ከተማ በነበረው ግጭት ደግሞ ሶስት የፖሊስ መኮንኖች መቁሰላቸውን እና አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በምዕራባዊ የሀሜዳን እና የሎሬስታን ግዛቶችም ተመሳሳይ ግጭቶች እንደተከሰቱ ተገልጿል።

በዋና ከተማዋ ቴህራን የሚገኙ ባለሥልጣናት፣ እየተባባሰ የመጣውን ተቃውሞ ለማረጋጋት በሚመስል መልኩ ረቡዕ ዕለት ባንኮች ዝግ ሆኖ የሚውሉበት የበዓል ቀን እንደሆነ አውጀው ነበር።

በማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ የተሰራጨ እና ትክክለኛነቱ በቢቢሲ የተረጋገጠ አንድ ቪዲዮ ላይ በፋሳ ከተማ የተሰበሰቡ ሰዎች የአካባቢውን ዋና አስተዳዳሪ ቢሮ በር ሲሰብሩ አሳይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሌላ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ደግሞ የጽጥታ ኃይሎች ሰብረው እየገቡ ያሉ ሰዎች ላይ ተኩስ ሲከፍቱ ይታያል። ከተዘጉ መደብሮች ፊት ለፊት አስለቃሽ ጭስ ወደ ሰማይ ሲጎን ተቀርጿል።

የኢራን መንግሥት በድንገት ባወጀው የሕዝብ በዓል ምክንያት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የመንግሥት ተቋማት ተዘግተው ውለዋል።

የአገሪቱ መንግሥት የእረፍት ቀኑ ለመታወጁ በምክንያትነት ያቀረበው 'በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የተነሳ ኃይል ለመቆጠብ' የሚል ቢሆንም በርካታ ኢራናውያን ግን ተቃውሞውን ለመግታት የተደረገ ሙከራ አድርገው ተመልክተውታል።

እሁድ ዕለት በዋና ከተማዋ ቴህራን ተቃውሞ የተጀመረው በተቆጡ ነጋዴዎች ነው። ነጋዴዎቹ የኢራን ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር አንፃር በድጋሚ በከፍተኛ ሁኔታ መውደቁን ተከትሎ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ተቃውሞው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያሳተፈ እና ወደ በርካታ ከተሞች የተስፋፋ ሆኗል። ሕዝቡ በሃይማኖታዊ መሪዎቹ ላይ ቁጣውን ማሰማት ጀምሯል።

ይህ ተቃውሞ በአውሮፓውያኑ 2022 ማህሳ አሚኒ የተባለች ወጣት ሴት "ሂጃብ በአግባቡ አልለበሽም" በሚል በአገሪቱ የሞራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ሕይወቷ ባለፈበት ወቅት ከተቀሰቀሰው አመፅ ወዲህ የታየ የመጀመሪያው ሰፊ ተቃውሞ ነው። ይሁን እንጂ ይሄኛው ተቃውሚ በመጠኑ ከቀደመው ጋር የሚስተካከል አይደለም።

ሁኔታው እንዳይባባስ ለመከላከል ተቃውሞው በተጀመረባቸው የቴህራን አካባቢዎች የጸጥታ አካላት ጥብቅ ጥበቃ እያደረጉ እንደሆነ ተዘግቧል።

የኢራን ፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን መንግሥታቸው የተቃዋሚዎችን "ተገቢ ጥያቄዎች" እንደሚያዳምጥ ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ መሐመድ ሞቫህዲ አዛድ ግን አለመረጋጋት ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ "ቁርጠኛ ምላሽ" እንደሚሰጠው አስጠንቅቀዋል።