አሜሪካ ከ50 በላይ የኢራን ዜጎች የያዘውን ሁለተኛ ቡድን ማባረሯን ባለሥልጣናት ተናገሩ

የኢራን ሰንደቅ ዓላማ በተሰቀለበት አካባቢ የምትራመድ ሴት

የፎቶው ባለመብት, ABEDIN TAHERKENAREH/EPA/Shutterstock

አሜሪካ ሁለተኛውን የኢራን ዜጎች ቡድን ወደ አገራቸው ማባረሯን በቴህራን የሚገኙ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ይህ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር የኢሚግሬሽን ሕጉን ለማስፈፀም የሚያደርገው ጥረት በቀጠለበት ወቅት ነው።

ከ50 በላይ ኢራናውያንን ያሳፈረ አውሮፕላን እሁድ ዕለት ከአሪዞና ሜሳ ተነስቶ በካይሮ እና ኩዌት በኩል ተጉዞ ኢራን መግባቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።

የቴህራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ዜጎች ወደ ኢራን መመለሳቸውን አረጋግጠዋል።

የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ግን ለደኅንነት ሲሉ በረራው መደረጉን ሊያረጋግጡ አሊያም ሊያስተባብሉ አልቻሉም።

ብዙም ባልተለመደው የኢራን እና የአሜሪካ ትብብር ወደ አገራቸው እንዲባረሩ የተደረገው የመጀመሪያ የኢራናውያን ዜጎች ቡድን በረራ የተካሄደው መስከረም መጨረሻ ላይ ነበር።

በርካታ ኢራናውያን ስደትን መርጠው አሜሪካ የገቡት በአገራቸው እስርን በመፍራት እንደሆነ ይናገራሉ።

ለስደተኞች ድጋፍ የሚያደርገው 'ቦርደርላንድ ካምፓኒየን ኦፍ ሆፕ' አባል የሆኑት አባ ጆሴፍ ባች እንዳሉት እንዲባረሩ ከተደረጉት ስደተኞች መካከል እምነታቸውን ወደ ክርስትና የለወጡ እንደሚገኙበት በአሪዞና ማቆያ ጣቢያ ከሚገኝ ሰው ተነግሯቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በማቆያ ጠቢያው የሚገኙት የተወሰኑ እስረኞችም የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን እንደሆኑ ራሳቸውን ለይተው እንደነበርም አባ ጆሴፍ አክለዋል።

እምነታቸውን ወደ ክርስትና የለወጡ እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ማኅበረሰብ አባላት በኢራን ከባድ የሕግ እና የማኅበራዊ ጫና የገጠማቸው ቡድኖች ናቸው።

አባ ጆሴፍ እንዳሉት ከአገር እንዲባረሩ መደረጋቸው " ከክርስትና እምነት ያፈነገጠ፤ አስፈሪ ነው። ያሳስበኛል፤ ጥሩ አይደለም። ይህንን የሞት በረራ ብዬ ነው የምጠራው" ብለዋል።

የኢራን ባለሥልጣናት ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረገበትን መንገድ አመቻችተዋል።

አንድ የኢራን ቆንስላ ባለሥልጣን በአሜሪካ በውጭ ዜጎች ላይ በተለይም በኢራናውያን ላይ እየተፈፀመ ባለው ፀረ ስደተኞች እና አግላይ ፖሊሲን ተከትሎ ስደተኞቹ ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል ማለታቸውን ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ሚዛን የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሆኖም ሁሉም ወደ አገራቸው እንዲባረሩ የተደረጉ ኢራናውያን የመመለስ ፍላጎት እንዳልነበራቸው አንድ እስረኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወደ አገራቸው በሚባረሩ ኢራንያውያን ዝርዝር ውስጥ የሚገኝ አንድ ግለሰብም እርሱ እና የሕይወት አጋሩ የሜክሲኮን ድንበር በእግራቸው አቋርጠው ወደ አሜሪካ የገቡት እየተገባደደ ባለው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።

በአሪዞና ማቆያ ጣቢያ ሆኖ የተናገረው ግለሰቡ ወደ ኢራን የሚመለስ ከሆነ ለሕይወቱ እንደሚሰጋ ተናግሯል።

አሁን ላይ ኢራናውያኑ ወደ አገራቸው የተባረሩት በተለይ ሰኔ ወር ላይ አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ማብለያ ጣቢያዎች ላይ የቦምብ ድብደባ በመፈፀሟ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነት ይበልጥ እየተባባሰ በመጣበት ወቅት ነው።

የስደተኞቹ መባረርም የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የድንበር ደኅንነትን እና ሕገ ወጥ ስደትን ለመቀነስ በሚል የፖለቲካ አጀንዳቸው ዋና ትኩረት ያደረገበትን ጠንካራ የአሜሪካ መንግሥት የኢሚግሬሽን አቋም የሚያሳይ ነው።