የሜክሲኮ ባሕር ኃይል ጀልባ ከብሩክሊን ድልድይ ጋር ተጋጭታ ሁለት ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ግዙፍ የሜክሲኮ ባሕር ኃይል ጀልባ ከኒው ዮርክ ከተማ ብሩክሊን ድልድይ ጋር ተጋጭታ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና 19 መቁሰላቸውን የከተማዋ ከንቲባ ተናገሩ።
ኤሪክ አዳምስ ቅዳሜ ምሽት አደጋው መድረሱን ገልፀው፣ ጀልባዋ ከመጋጨቷ በፊት የኃይል መቋረጥ አጋጥሟት ነበር ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት 277 ሰዎች በጀልባዋ እንደነበሩ ተናግረዋል።
አደጋው በደረሰበት ወቅት የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጀልባዋ በድልድዩ ስር በምታልፍበት ወቅት ረዣዥም ማማዎቿ ከድልድዩ ጋር መጋጨታቸውን እና መሰበራቸውን ያሳያሉ።
የተሰበረው ማማ በጀልባዋ ላይ ወድቆ አደጋውን አድርሷል።
አደጋው የደረሰው የተወሰኑ የጀልባዋ ሠራተኞች ግጭቱ በደረሰበት ወቅት ማማው ላይ ተንጠላጥለው ስለነበረ መሆኑን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ በኤክስ ገጻቸው ላይ "በወቅቱ 277 ሰዎች በጀልባዋ ላይ ተሳፍረው የነበረ ሲሆን 19 ጉዳት ሲደርስባቸው ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። እንዲሁም ሁለት ሰዎች በደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል" ብለዋል።
ከንቲባው ብሩክሊን ድልድይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳላጋጠመው አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት አንድም ሰው ባሕሩ ውስጥ አለመግባቱን አረጋግጠዋል።
የሜክሲኮ ባሕር ኃይል 22 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር።
ጀልባዋ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን የአደጋው መንስዔ ምን እንደሆነ ምርመራ ይደረጋል ብሏል።
የኒው ዮርክ የባሕር ዳርቻ ጠባቂ የጀልባዋ ሁለት ማማዎች መሰበራቸውን ገልጾ፣ የጀልባዋ ሠራተኞች ሁሉ መኖራቸው ተረጋግጧል ያለ ሲሆን የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን አስታውቀዋል።
የኒው ዮርክ ፖሊስ ኃላፊ በበኩላቸው አደጋው የደረሰው "በመካኒክ ብልሽት" መሆኑን ገልፀው፣ የኃይል መቋረጥ በማጋጠሙ የጀልባዋ አንድ ማማ ከድልድዩ ጋር መጋጨቱን አስታውቀዋል።
በአካባቢው የተሰበሰቡ ሰዎች የጀልባዋ ማማ ከድልድዩ ጋር ሲጋጭ እና አቅጣጫዋን ስትቀይር ተመልክተዋል።
የኒውዮርክ ፖሊስ ነዋሪዎች ብሩክሊን ድልድይ፣ በማንሃተን ሳውዝ ስትሪት ሲፖርት እና ብሩክሊን ዱምቦ አካባቢ እንዲርቁ ማስጠንቀቅያ ሰጥቷል።
"ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና ብዛት ያላቸው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መኪኖች በአካቢው ላይ ሊገኙ ይችላሉ" ሲል የከተማዋ ፖሊስ በኤክስ ገፁ ላይ ጽፏል።
ጀልባዋ በኋላ ላይ ከአደጋ ስፍራው እንድትነሳ ተደርጓል።
91 ሜትር የምትረዝመው እና 12 ሜትር የምትሰፋዋ ጀልባ ለመጀመርያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለችው እአአ በ1982 መሆኑን የሜክሲኮ ባሕር ኃይል መረጃ ያሳያል።
በየዓመቱ ከባሕር ኃይል ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ተማሪዎችን ይዛ በባሕር ላይ ቀዘፋ ታካሂዳለች።
በዚህ ዓመትም ከአካፕሉኮ የባሕር ወደብ እአአ በሚያዝያ 6፣ 277 ሰዎችን አሳፍራ መነሳቷን የባሕር ኃይሉ አስታውቋል።
የመጨረሻ መዳረሻው አይስላንድ እንደነበር ተገልጿል።












