ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የታይም መጽሄት የአመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው ተባሉ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታይም መጽሔት ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው አድርጎ ለሁለተኛ ጊዜ ሰየማቸው።

ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2016 በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በመጽሔቱ የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ተደርገው የነበረ መሆናቸው ይታወሳል።

ትራምፕ ይህንን ስያሜ ያገኙት ታሪካዊ እና አስደናቂ በተባለ ሁኔታ ወደ ስልጣን በመመለሳቸው እና በትውልዱ የፖለቲካ ለውጥ በማምጣት የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሁኔታ በመቀየራቸው መሆኑን የታይም መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሳም ጃኮብስ ለአንባቢዎች በጻፉት ጽሁፍ አስፍረዋል።

ዋና አዘጋጁ ትራምፕ አሜሪካ በአለም ያላትን ሚና በመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉም በዚሁ ጽሁፍ ላይ አትተዋል።

ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በኒውዮርክ በነበረው የአክሲዮን ልውውጥ የመክፈቻ ዝግጅት ላይ ከበርካታ የቤተሰቦቻቸው አባላት እና ዩኤስኤ በሚሉ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው ድላቸውን አክብረዋል።

ትራምፕ ከታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወደ ስልጣን ሲመለሱ ያቀዷቸውን ጉዳዮች አጋርተዋል።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ከሶስት ዓመታት በፊት በአሜሪካ የካፒቶል አመጽ እና ነውጥ በማነሳሳት የተከሰሱ ግለሰቦችን ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ይቅርታ አደርግላቸዋለሁ ብለው የነበረ ቢሆንም ከታይም ጋር በነበራቸው ቆይታ ጉዳያቸውን በተናጠል አያለሁ ሲሉ አሻሽለዋል።

በአክሲዮኑ ልውውጥ የመክፈቻ ወቅት ማንም ሰው አይቶት በማያውቅ ሁኔታ አገራቸው በምጣኔ ኃብት እንደሚያሳድጉ እና ቀረጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሱ ቃል ገብተዋል።

ታይም በአውሮፓውያኑ 1927 የጀመረው "የዓመቱ ሰው" ምርጫ ጉልህ በዓመት ውስጥ አስተዋጽኦ ወይም ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ሰዎችን ወይም እንቅስቃሴዎችን ዕውቅና ይሰጣል።

ከዚህ ቀደም የታይም መጽሄትን የአመቱ ሰው ካሸነፉት መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቿ ግሬታ ቱንበርግ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ይገኙበታል።

የታይም መጽሔት አዘጋጆች በመጨረሻ ሽልማቱን ማን እንደሚያሸንፍ ይወስናሉ።

መጽሔቱ በዚህ ዓመት አስር ሰዎችን እነሱም ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ፣ የዌልስ ልዕልት፣ የቴስላ ዋና አስፈጻሚ ኤሎን ማስክን በአሸናፊነት እጩ ዝርዝር ውስጥ አካቶ ነበር።