ኤርትራ በድጋሚ ከኢጋድ ለመውጣት የወሰነችበት ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ይሆን?

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በ2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የተደረገላቸውን አቀባበል ያሳያል። ኢሳያስ በፈገግታ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁን ሰላም ሲሉ ይታያል። ከአጠገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና አምባሳደር ፍጹም አረጋ ቆመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega/X

የምስሉ መግለጫ, የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት በኢትዮጵያዊው ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከሚመራው ኢጋድ ራሱን ያገለለው አገሪቱን በድጋሚ የተቋሙ አባል ባደረገ በሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ነው

በሐምሌ 1998 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በእስላማዊ ታጣቂዎች የበላይነት የተወሰደበትን የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን ለመደገፍ ወደ ሞቃዲሾ ዘመተ። ከዘጠኝ ወራት በኋላ በሚያዝያ 1999 ዓ.ም. ኤርትራ ቀጣናዊው ተቋም ከሆነው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) መውጣቷን አስታወቀች።

ኤርትራ ውሳኔዋን ባሳወቀችበት ደብዳቤ፤ ተቋሙ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የፈጸመችውን "ወረራ" በዝምታ መደገፉን በመጥቀስ ከስሳለች። ኤርትራ በዚህ ምክንያት ከ16 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከቀጣናዊው ተቋም አባልነት ውጪ ሆና አሳልፋለች።

እነሆ አሁን ደግሞ ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ኤርትራ ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ ደርሳለች። የኤርትራ መንግሥት አርብ ታኅሣሥ 3/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ኢጋድ "ሕጋዊ ግዴታዎቹን ባለመወጣቱ" ከአባልነት መውጣቱን አስታውቋል።

ኤርትራ በመግለጫዋ ላይ ኢትዮጵያን ባትጠቅስም፤ በአዲስ አበባ እና አሥመራ መካከል ተፈጠረው መካረር ለዚህ ውሳኔዋ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በኢጋድ ላይ ጥናት ያደረጉት የሰላም እና ደኅንነት ተመራማሪው ዶ/ር ቃለአብ ታደሰ ይናገራሉ።

መቀመጫውን በጂቡቲ ያደረገው ኢጋድ በ1978 ዓ.ም. የተቋቋመው በቀጣናው በተደጋጋሚ በሚከሰቱት ድርቅ እና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎችን የመከላከል ሥራ ለማከናወን ነበር። ኢጋድ አሁን ያለበትን ተቋማዊ ቅርጽ የያዘው በ1991 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ከተደረገው ጠቅላላ ጉባኤው በኋላ ነው።

ከኢጋድ የትኩረት መስኮች መካከል፤ በቀጣናው አገራት በሚታዩ የሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ቀጣናዊ ውህደት ይገኙበታል።

ኢጋድ ቀጣናዊ ተቋም ሆኖ እንዲቋቋም ያደረጉት የመጀመሪያዎቹ አባል አገራት ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ ናቸው። ኤርትራ ተቋሙን የተቀላቀለችው አገር ሆና ከተመሠረተች በኋላ በ1985 ዓ.ም. ነው። ከ15 ዓመታት በፊት አገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን ደግሞ ኋላ ላይ ስምንተኛዋ አባል አገር ሆናለች።

ኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢጋድን ለቅቃ የመውጣት ውሳኔ ላይ ያደረሳት ጉዳይ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ካደረገችው ጣልቃ ገብነት ጋር የተያያዘ ነው።

የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት (Islamic Courts Union) የተባለው የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን ሰኔ 1998 ዓ.ም. ባደረገው ፈጣን ወታደራዊ ዘመቻ የሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾን ተቆጣጥሮ ነበር።

ይህ የታጣቂ ቡድኑ እንቅስቃሴ በወቅቱ አገሪቱን ሲመራ የነበረው የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ሸሽቶ መቀመጫውን ባይዶዋ ከተማ ላይ እንዲያደርግ አስገድዶታል።

ቡድኑ ለኢትዮጵያ ያለውን ጠላትነት በይፋ ከመግለጹ ጋር ተያይዞ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር መንግሥቱን ወደ ሥልጣኑ ለመመለስ ወታደሮቹን ወደ ሶማሊያ አስገብቷል።

አወዛጋቢው ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ ከሶማሊያውያንም ተቃውሞ ተነስቶበት ነበር። አሁንም ድረስ የዚህ እርምጃ ውጤት አካራካሪ ነው።

በጉዞ ላይ ባለ ከባድ ተሽካርካሪ ጀርባ ላይ ላይ ቁጭ ብለው እና ቆመው የተጫኑ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ በመግባት በእስላማዊ ታጣቂዎች የበላይነት ተወስዶበት የነበረውን የወቅቱን የሽግግር መንግሥት ወደ ሞቃዲሾ መልሷል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሆነው ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ከገቡ ከአምስት ወራት በኋላ የሽግግር መንግሥቱ ወደ ሞቃዲሾ መመለስ ችሏል።

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ዘመቻ ለተከፈተበት እስላማዊ ታጣቂ ቡድን "በጦር መሳሪያ እና በወታደራዊ ምክር" ድጋፍ ያደርግ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ያቋቋመው በኤርትራ የሰብአዊ መብቶች አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርት ያመለክታል።

ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች መፍረስ በኋላ ለተቋቋመው እና ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ላለው "አልሸባብ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች" ድጋፍ ማድረጓን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንደተገኙም የመንግሥታቱ ድርጅት የማዕቀብ ተገዢነት ክትትል ቡድን አስታውቆ ነበር።

ኤርትራ ግን ወደ ሶማሊያ "ምን ዓይነት የጦር መሳሪያ አለመላኳን" በመግለጽ የቀረበባትን ውንጀላ ተቃውማለች። ክሶቹንም "ግልጽ ፈጠራዎች እና ፍጹም ውሸቶች" በማለት ገልጻቸዋል።

ኤርትራ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ መግባቱን አጥብቃ በመቃወም ብቻ አላበቃችም። የኢትዮጵያን እርምጃ እንደደገፈ በመጥቀስ ከምትከስሰው ኢጋድም መወጥታለች።

የአገሪቱ መንግሥት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ "ኤርትራ፤ በኢጋድ ጥላ ሥር የሚደረገውን ወረራ እና የበላይነትን ለመደገፍ እንዲሁም ከፍትሕ እና ከእውነት ውጪ በሶማሊያ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው የጭካኔ ድርጊት አካል ለመሆን ፍቃደኛ አይደለችም" ብሏል።

ቀጥሎ ደግሞ በ2002 ዓ.ም. ኤርትራ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት አሥመራ እና ባለሥልጣናቷ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

እነዚህ ሁኔታዎች የተቀየሩት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የአዲስ አበባ እና የአሥመራ ግንኙነት ሲሻሻል ነው።

ከዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት ስምንት ወራት በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ለዘጠኝ ዓመታት በኤርትራ ላይ ጥሎት የቆየው የመሳሪያ ማዕቀብ፣ የሀብት እገዳ እና የባለሥልጣናት የጉዞ ክልከላን አንስቷል።

የሰላም እና ደኅንነት ተመራማሪው ዶ/ር ቃለአብ እንደሚናገሩት፤ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የተነሳው የኢትዮጵያ መንግሥት "ባደረገው ጉትጎታ" ነው።

የዐቢይ መንግሥት "ኤርትራ ከዚህ በኋላ በቀጣናው የሚገባትን ቦታ አግኝታለች፣ ቀጣናው ላይ ለሰላም እና ትብብር ሚናዋን ልትጫወት ነው" በሚል ማዕቀቡ እንዲነሳ ድጋፍ መስጠቱን ያስረዳሉ።

የኢጋድ አገራት ባንዲራን ከያዘ ትልቅ ቢልቦርድ ፊት ለፊት የኢጋድ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፥ ጅቡቲ አገራት መሪዎች ጨምሮ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዑስማን ሳልህ፣ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ በአንድ መስመር ተደርድረው ለፎቶ ቆመዋል

የፎቶው ባለመብት, IGAD Secretariat/X

የምስሉ መግለጫ, ኤርትራ ከ16 ዓመታት በላይ ከዘለቀ እቀባ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የ2015 ዓ.ም. የኢጋድ ጉባኤ ላይ የተወከለችው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዑስማን ሳልህ (ከግራ ሁለተኛ) ነበር

በሰኔ 2015 ዓ.ም. ደግሞ ኤርትራ ለ16 ዓመታት ራሷን ያገለለችበትን የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅትን መልሳ በመቀላቀል በወቅቱ በጂቡቲ በተደረገው መደበኛ ጉባኤ ላይ ተሳትፋለች።

ይህ የአሥመራ ውሳኔ ግን ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በላይ ሊጸና አልቻለም፤ አሁን በድጋሚ ከአባልነት መልቀቋን አስታውቃለች።

ኤርትራ ይህንን ውሳኔዋን ይፋ ባደረገችበት መግለጫ ላይ ተቋሙ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ "ዒላማ የተደረጉ አባል አገራት፤ በተለይም ኤርትራ ላይ" ለሚፈጸሙ እርምጃዎች "መገልገያ በመሆን ጎጂ ሚና" መጫወቱን በመጥቀስ ከስሳለች።

በተጨማሪም ከ20 ዓመት ገደማ በፊት ከአባልነት የወጣችው በእነዚሁ "አግባብነት የሌላቸው ድርጊቶች" ምክንያት እንደሆነም አስታውሳለች።

በ2015 ዓ.ም. ወደ አባልነቷ የተመለሰችው ተቋሙ "የኤርትራን የሪፎርም ጥያቄ ይቀበላል እና የቀደመ ታሪኩን ያቃናል በሚል ተስፋ" እንደነበረ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። "በሚያሳዝን ሁኔታ፤ ኢጋድ በሕግ ከተጣለበት ግዴታ ማፈንገጥ ቀጥሏል፤ በዚህም ጠቃሚነቱን እና ሕጋዊ መብቱን ሽርሽሯል" ብላለች።

ተቋሙ ለአባል አገራቱ "ምንም ጉልህ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ የሌለው" እንዲሁም "በቀጣናው መረጋጋት ለማምጣት" ያልቻለ እንደሆነ በማንሳትም ወቅሳለች። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ከአባልነት ለመውጣት "እንደተገደደችም" አስታውቃለች።

የኤርትራን ውሳኔ ተከትሎ ኢጋድ ከሰዓታት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ በውሳኔው "ማዘኑን" ገልጿል። ይሁን እንጂ ኤርትራ ወደ አባልነቷ ከተመለሰችበት ከሰኔ 2015 ዓ.ም. አንስቶ "በኢጋድ ስብሰባዎች፣ ፕሮግራሞች ወይም እንቅስቃሴዎች ላይ አለመሳተፏን" ገልጿል።

"በዚህ ጊዜ ውስጥ ጽህፈት ቤቱ ራሱን ለገንቢ ግንኙነት ክፍት እና ዝግጁ በማድረግ ትዕግስት እና መልካም ፈቃደኝነትን ሲያሳይ ነበር" ብሏል።

አክሎም ኤርትራ ከአባልነት ለመውጣት የወሰነችው "በተቋማዊ ወይም ፖሊሲ ሪፎርም ላይ ተጨባጭ የሆነ የዕቅድ ሰነድ ሳታቀርብ ወይም ግንኙነት [ሳታደርግ]" እንደሆነ ጠቅሷል።

በኢጋድ ላይ ጥናት ያደረጉት ዶ/ር ቃለአብ በኢጋድ የተነሳውን ሀሳብ ይጋሩታል። ኢጋድ ከአሥመራ ፍላጎት አንጻር "ምን እንዳልሠራ መናገር የሚችለው የኤርትራ መንግሥት" መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር ቃለአብ፤ በመግለጫው ላይ ይህንን በተመለከተ በዝርዝር የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩን ይጠቁማሉ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ድምጽ ማጉያዎች የተደረደሩት አንትሮስ ፊት ቆመው ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/X

የምስሉ መግለጫ, የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት እንደ ኢጋድ ባሉ "የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ" እንዳለው ተመራማሪው ይናገራሉ

ይሁን እንጂ "ኤርትራ ከመጀመሪያውም እንደ ቁም ነገር ቆጥራ ከልቧ ከኢጋድ ጋር ግንኙነት አላት ለማለት ይከብዳል። አንድኛ ኢጋድም በአሥመራ ጽህፈት ቤት የለውም። ኢጋድ በየአባል አገራቱ 'ሄድ ኦፍ ሚሽን' የሚባል ቢሮ አለው። ኤርትራ [ከኢጋድ ጋር] እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት የላትም" ይላሉ። ኤርትራ በኢጋድ ያላት ተሳትፎ ቀድሞውንም "ጠንካራ ያልነበረ" መሆኑንም ያክላሉ።

"ኤርትራ ያን ያህል ኢጋድ ላይ ከልቧ ገብታበት 'ኢጋድ ዓላማ እንደዚህ ነው፣ አብሬ በቀጣናው ልማት፣ ሰላም እና ፀጥታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ቀጣናዊ ውህደት ላይ እሠራለሁ' የሚል ሥራ ሠርተው አያውቁም" በማለት የአሥመራ ተሳትፎ መሠረት የያዘ እንዳልነበረ ይገልጻሉ።

ከዚህ አውድ በመነሳት፤ የአሁኑ የኤርትራ ውሳኔ "ኢጋድ ላይ ሲሪየስ እና ስትራቴጂክ ፍላጎት ኖሯት ያደረገችው አይደለም" የሚል ምልከታ እንዳላቸው የሰላም እና ደኅንነት ተመራማሪው አንስተዋል።

"የኢጋድ እና የኤርትራ ጉዳይ ሁሌም ከኢትዮጵያ ጋር የተገናኘ ነው" የሚል አቋም ያላቸው ዶ/ር ቃለአብ፤ የአሁኑ ውሳኔም ከአዲስ አበባ ጋር የተገናኘ እንደሚሆን ያነሳሉ።

ኤርትራ፤ በቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ከሚመራው ኢጋድ የመውጣት ውሳኔዋን ይፋ ያደረገችው ከአዲስ አበባ ጋር የገባችበት ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።

ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ካስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መፈረም ወዲህ የሻከረው የአዲስ አበባ እና የአሥመራ ግንኙነት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን ከገለጸበት 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ውጥረት ውስጥ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ከ30 ዓመት በፊት የተፈጸመ ስህተት" በማለት የሚገልጹት የኢትዮጵያን የባሕር በር አልባነት "የኅልውና" ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። ይህንን "ስህተት ለማረም" እንደሚሠሩም በይፋ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት ከህወሓት አመራሮች ጋር ያለው ግንኙነት አዲስ አበባ ላይ ስጋት ፈጥሯል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ በላኩት ደብዳቤ፤ ኤርትራ እና ህወሓት "ጽምዶ" በሚል ጥምረት መሥርተው "ጦርነት ለመክፈት" እየሠሩ ነው የሚል ክስ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ውስጥ ላይ አውራ እና አመልካች ጣቶቻቸው ገጣመው እና ቀሪዎቹ ጣቶቻቸውን አጥፈው ሲናገሩ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister - Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት በቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ "መመለስ" ያለበት "የኅልውና ጥያቄ" እንደሆነ ደጋግሞ በአጽንኦት ማንሳቱን ተከትሎ የአዲስ አበባ እና የአሥመራ ውጥረት ይበልጥ ተካርሯል

ኤርትራ በበኩሏ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ፍላጎት እና የተሰነዘሩት ውንጀላዎች "የጦር መስበቅ" እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ትገልጻለች። የአዲስ አበባ የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ አገሪቱን ሉዐላዊነት የሚዳፈር እንደሆነም ታነሳለች።

ዶ/ር ቃለአብ የኤርትራ ከኢጋድ መውጣት ውሳኔ የዚህ ውጥረት አንድ ነጸብራቅ ነው የሚል እምነት አላቸው። "አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ኤርትራ የገቡበት ፍጥጫ ተመልሶ ኤርትራ ሁሌ የምታነሳውን 'ወጥቻለሁ' የሚል መግለጫ እንዲወጣ አድርጓል" ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።

ኤርትራ፤ "የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ" እንዳላት ያነሱት ተመራማሪው፤ የአሁኑ ውሳኔዋም ይህንን የከረመ ስጋት የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አመልክተዋል።

የሆነው ሆኖ እንደ ኢጋድ ያሉ ቀጣናዊ ተቋማት አባል የአገራቱ መውጣት እንዲሁም ጠንካራ አለመሆን ተጽዕኖው "በሚገባው ልክ እንዳይሆን" እንደሚያደርግ አንስተዋል።

"አንድ ቀጣናዊ ድርጅት ጥንካሬው የሚለካው በአባል አገራቱ ነው" የሚሉት ዶ/ር ቃለአብ፤ የኢጋድ አባል አገራት በአብዛኛው "ለረጅም ጊዜ በብጥብጥ ላይ ያሉ" ወይም እንደ ኤርትራ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን "የሚገፉ" መሆናቸው የተቋሙን ተጽዕኖ እንደገደበው ገልጸዋል።

"ከጥቂት ጊዜያት በፊትም ሱዳን 'ከኢጋድ ወጥቻለሁ' ብላ ነበር። በአባል አገራቱ ሁሌ በብጥብጥ እና ደካማ ማዕከላዊ መንግሥት በመኖር ድርጅቱን ደካማ ያደርገዋል። እንጂ ኢጋድ እንደ ድርጅት ከሌሎቹ የምዕራብም ሆነ የደቡብ [አፍሪካ ቀጣናዊ ድርጅቶች] በተለየ ጠንካራም ደካማም የሚያደርገው ነገር የለም። በቀጣናው ያለው የአገራቱ ሁኔታ ነው እንደዚህ ያደረገው" በማለት ያብራራሉ።