የቀድሞ የአሜሪካ የጦር መኮንን በፍቅር ጓደኛ መፈለጊያ ድረ ገጽ ላይ ሚስጥር አሳልፎ በመስጠት ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የቀድሞ የጦር አባል የነበሩት ኮሎኔል የአገሪቱን ሚስጥር በአንድ የውጭ የፍቅር ጓደኛ መፈለጊያ ድረ ገጽ ላይ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለአንዲት ግለሰብ አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የ63 ዓመቱ ዴቪድ ፍራንክሊን ስላተር እስከ ፈረንጆቹ 2022 ድረስ በሥራ ላይ የነበሩ ሲሆን የአሜሪካ የኒውክሌር መሣሪያ ተቆጣጣሪው ስትራትኮም ተቀጣሪ ነበሩ።
ኮሎኔሉ ፈጽመውታል በተባለው ወንጀል ተጠርጥረው ባለፈው ቅዳሜ የታሰሩ ሲሆን ዛሬ [ማክሰኞ] ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ባለስልጣናት እንዳሉት ኮሎኔሉ በሕገ ወጥ መንገድ “የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል” መረጃ ሲያሾልኩ ቆይተዋል።
ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነው የኮሎኔሉ ክስ እንደሚያስረዳው የጦር መኮንኑ በስራቸው ምክንያት ያገኙትን ወታደራዊ ዕውቀት አንዲት ዩክሬን ውስጥ ለምትገኝ ሴት አሳልፈው ሰጥተዋል። መረጃውም በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ዝርዝር ትንታኔዎችን የያዘ ነው ተብሏል።
ኮሎኔሉ የአሜሪካ ብሔራዊ የመከላከያ ምስጢራዊ መረጃዎችን በተመለከተ በተደጋጋሚ በመልዕክቶች ሲጠየቁ እንደነበርም ዓቃቤ ህግ ገልጿል።
ኮሎኔሉ በተለያየ ጊዜ በድረ ገጹ የተለዋወጧቸው መልዕክቶች ለክሱ ማጠናከሪያነት ተይዘዋል። ከእነዚህም መካከል “የእኔ ጣፋጭ ዴቭ ለሰጠኸኝ ወሳኝ መረጃ አመሰግናለሁ። ምስጢራዊ ሰላዬ ነህ” የሚለው ይገኝበታል።
መልዕክቱ ግን ኮሎኔሉ የሚያወሯትን ግለሰብም ሆነ የድረ ገጹን ስም በይፋ አልጠቀሰም።
የኮሎኔሉ ጉዳይ በኤፍቢአይ እና በአየር ኃይል ልዩ መርማሪ ቡድን ሲጠና ቆይቷል።
“አንዳንድ ኃላፊነቶች ግለሰቦች ከፍተኛ መረጃዎችን እንዲያገኙ ያስችሏቸዋል” ያሉት የነብራስካ ዳኛ ሱዛን ሌህር፣ “በዴቪድ ላይ የሚደረገው ምርመራ ይህንን ኃላፊነታቸውን ስለመጣስ አለመጣሳቸው የሚመለከት ይሆናል” ብለዋል።
ኮሎኔል ዴቪድ በማሴር ወንጀል እና የአገሪቱን ወታደራዊ ሚስጥር ያለ ያለ ፍቃድ አሳልፎ በመስጠት ነው የተከሰሱት።
በተከሰሱበት ድርጊት ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊያስቀጣቸው ይችላል።
የኮሎኔል ዴቪድ ክስ ይፋ የተደረገው በማሳቹሴት ኤየር ናሽናል ጋርድ የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ የመከላከያ መረጃዎችን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በማግኘት እና አሳልፎ በመስጠት ጥፋተኛ መሆኑን ማመኑን ይፋ በተደረገ በሰዓታት ልዩነት ነው።
በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ጃክ ቴክሴራ እስከ 16 ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል።












