ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ ከተገለበጠ የጭነት መኪና የተዘረፈ መርዛማ ኬሚካል ስጋት ፈጠረ
በኬንያ መዲና ናይሮቢ አቅራቢያ ከተገለበጠ የጭነት መኪና የተዘረፈው በጣም መርዛማ ኬሚካል ስጋት እንደፈጠረ ባለስልጣናቱ ተናገሩ።
የተዘረፉትን መርዛማ ኬሚካል እሽጎችም ለማግኘት የኬንያ ባለስልጣናት እርዳታ ጠይቀዋል።
መርዛማ ኬሚካሉ ሶዲየም ሲያናይድ የተሰኘ ሲሆን በትንሽ መጠን ቢዋጥ ወይም በትንፋሽ መልኩ ቢወሰድ ሊገድል እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
ለአካባቢም ጠንቅ እንደሆነ የገለጹት ባለሙያዎች አደገኛነቱንም እያስረዱ ይገኛሉ።
በኬንያ የመኪና አደጋን ተከትሎ ከባድ መኪናዎች መዘረፍ የተለመደ ተግባር ነው።
ቅዳሜ ረፋድ ላይ ይህ አደገኛ ኬሚካሎችን ጭኖ የነበረው የጭነት መኪና ሲገለበጥም በርካቶች በስፍራው የተገኙ ሲሆን ኮንቴነሮችንም ዘርፈው ወስደዋል።
አደጋው የደረሰበት እና የተጨናነቀው የናይሮቢ- ናኩሩ አውራ ጎዳናን አካበቢ ነዋሪዎች እንዲያስወግዱ መንግሥት አሳስቧል።
የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ ዜጎቹ ሌላ አቅጣጫ እንዲከተሉ መክሯል።
አደጋው የደረው ከናይሮቢ በ33 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲሆን የጭነት መኪናው ለምን እንደተገለበጠ ግልጽ አይደለም።
ባለስልጣናቱ ስለ አሽከርካሪው ሁኔታ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
የአገሪቱ የብሔራዊ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ማህበረሰቡ የተዘረፉትን ጭነቶች ካዩ በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መጠቆም እንዳለባቸው አሳስቧል።
ኤጀንሲው በተጨማሪ እነዚህን ነጭ ቀለም ያላቸው ትናንሽ መርዛማ ኬሚካሎች እንዳይነኩም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኬሚካሉን ያለ ደህንነት ጓንት መንካት አደገኛ መሆኑን ገልጿል።
“ሶዲየም ሳይናይድ በኦክስጅን አጠቃቀም ላይ ጣልቃ በመግባት በትንፋሸ መልክ እንኳን በብዛት ከተወሰደ በአጣዳፊ ሁኔታ ሞትን ያስከትላል። ምልክቶቹ ራስ ምታት፣ የትንፋሸ መቆራረጥ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ማንቀጥቀጥ ናቸው” ብሏል።
ኬሚካሉ በመሬት ውስጥ እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃን ሊበክል እንደሚችል እና በከባቢው ለረጅም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችልም ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል።
ሶዲየም ሳያናይድ ተባዮችን ለማጥፋት፣ ኬሚካል ወርቅ እና ብር ከድንጋይ ፈልፍሎ ለማውጣት እንዲሁም በኬሚካል ማምረቻዎች ላይ ጥቅም እንደሚውል የአሜሪካ የስራ ደህንነት እና የጤና ተቋም አስታውቋል።
የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አንዳንድ ሰዎች የኬሚካል እሽጎችን ቢወስዱም ሌሎች ጄሪካን ይዘው የመጡ ደግሞ ንጥረ ነገሩ ምንም እንደማይጠቅማቸው በመረዳታቸው ዝም ብለው መመለሳቸው ተዘግቧል።