ትራምፕ ቀረጥን በሚቃወም ማስታወቂያ ምክንያት በካናዳ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ጣሉ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ወደ ማሌዥያ እያቀኑ ሳለ በካናዳ ላይ ስለጣሉት ተጨማሪ ቀረጥ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ አጋርተዋል

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ቀረጥን ከሚቃወም ማስታወቂያ ጋር በተያያዘ ከካናዳ ወደ አገሪቱ በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ቀረጥ ጣሉ።

ይህ የሆነው የካናዳዋ ግዛት ኦንታሪዮ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሪጋን የታዩበት 'ፀረ ቀረጥ ማስታወቂያ' ማስተላለፏን ተከትሎ ነው።

በኦንታሪዮ መንግሥት ድጋፍ የተደረገለት ማስታወቂያው፣ሪፐብሊካን እና የአሜሪካ ወግ አጥባቂ መሪ የሆኑትን የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሪጋን "ቀረጥ እያንዳንዱን አሜሪካዊ ይጎዳል" የሚለውን ንግግር ያጣቀሰ ነው።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ ማስታወቂያውን 'ማጭበርበር' ያሉት ሲሆን፣ የካናዳ ባለሥልጣናት ከዓለም የቤዝቦል ሻምፒዮን አስቀድሞ ማስታወቂያውን ከአየር ላይ ባለማውረዳቸው ወቅሰዋል።

"እውነታውን በተሳሳተ መልኩ በማቅረባቸው እና በጥላቻ ድርጊት ምክንያት አሁን ከሚከፍሉት በተጨማሪ በካናዳ ላይ 10 በመቶ ቀረጥ ጨምሬያለሁ" ብለዋል - ትራምፕ።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ከካናዳ ጋር እያደረጉ የነበረውን የንግድ ንግግር ካቋረጡ በኋላ የኦንታሪዮ አስተዳዳሪ ማስታወቂያውን እንደሚያወርዱ ተናግረዋል።

የኦንታሪዮ ገዢ ዶግ ፎርድ አርብ ዕለት እንደተናገሩት ግዛታቸው በአሜሪካ የሚያካሂደውን የፀረ ቀረጥ ማስታወቂያ ዘመቻዎች እንደሚያቆሙ ገልጸዋል።

ፎርድ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒይ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ እንደሆነ እና የንግድ ንግግሮች እንደገና እንዲቀጥሉ በማሰብ መሆኑን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ - ካናዳ የንግድ ሚኒስትር ዶሚኒክ ሊብላንክ፣ ከነበረው ላይ የተጨመረውን ቀረጥ አስመልክቶ ምላሽ ሲሰጡ "ባለፉት ሳምንታት ከአሜሪካ አቻዎቻችን ጋር በተደረገው ገንቢ የሆነ ውይይት ሂደት ለማጠናከር ዝግጁ ነን" ብለዋል።

የማስታወቂያ ቪዲዮው በአውሮፓውያኑ 1987 በብሔራዊ ራዲዮ የተላለፈ እና በውጭ ንግድ ላይ ካተኮረ የቀድሞው ፕሬዚደንት ንግግር የተቀነጨበ ነው።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱን አሻራ ለመጠበቅ የተቋቋመው ሮናልድ ሪጋን ፋውንዴሽንም፣ "የተመረጠ ድምጽን እና ቪዲዮን በመጠቀም የተዘጋጀ እንዲሁም የቀድሞው ፕሬዚደንት ያደረጉትን ንግግር የማይወክል ነው" ሲል ማስታወቂያውን ተችቶታል።

ጨምሮም የኦንታሪዮ መንግሥት ንግግሩን ለመጠቀም ፈቃድ አልጠየቀም ብሏል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋሩት ጽሑፋቸው ማስታወቂያው ቀደም ብሎ መውረድ ነበረበት ብለዋል።

"ማስታወቂያቸው ወዲያውኑ መውረድ ነበረበት፤ ነገር ግን ማጭበርበር መሆኑን እያወቁ በወርልድ ሲሪስ [የስፖርት ውድድር] ወቅት ባለፈው ምሽትም አስተላልፈውታል" ብለዋል ወደ ማሌዥያ እያቀኑ።

ካናዳ፣ ትራምፕ በዋና ዋና የንግድ አጋሮቻቸው ላይ ታሪፍ ካጣሉ በኋላ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ያልደረሰች የቡድን ሰባት አባል አገር ናት።

አሜሪካ ምንም እንኳን ቀደም ብሎ በነበረ የነፃ ንግድ ስምምነት ምክንያት አብዛኞቹ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ቢሆኑም በሁሉም የካናዳ ምርቶች ላይ 35 በመቶ ቀረጥ ጥላለች።

ከዚህም በተጨማሪ በብረታ ብረት ምርቶች ላይ የተጣለውን 50 በመቶ ቀረጥ እና በአውቶሞቢሎች ላይ የተጣለውን የ25 በመቶ ቀረጥ ጨምሮ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ የጣለችው ቀረጥ ከፍተኛ ነው።

ትራምፕ ወደ እስያ እያቀኑ በነበረበት ወቅት ባጋሩት በዚህ ጽሑፋቸውም በእነዚህ ቀረጦች ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ መጨመራቸውን ጠቁመዋል።

አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የካናዳ ምርት በአሜሪካ የሚሸጥ ሲሆን ኦንታሪዮ ግዛት ደግሞ የካናዳ አውቶሞቢሎች የሚመረቱባት ግዛት ናት።