ዶናልድ ትራምፕ ፆታቸውን የቀየሩ ወንዶች በሴቶች ስፖርት ላይ እንዳይወዳደሩ የሚያግድ ውሳኔ አሳለፉ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፆታቸውን ወደ ሴት የቀየሩ ሰዎች በሴቶች የስፖርት ዘርፎች እንዳይወዳደሩ የሚከለክለውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ፆታቸውን ከወንድ ወደ ሴት የቀየሩ ሰዎችን በሚመለከት መመሪያ፣ ደንብ እና ሕጋዊ ትርጓሚዎችን የሚሰጥ ሲሆን፣ የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን በማያስፈጽሙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ የሚያዝ ነው።

የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ በስፖርት ውድድሮች ላይ ፍትሐዊነትን የሚያመጣ መሆኑን ሪፐብሊካኖች ሲናገሩ፣ የፆታ ጉዳዮች እና የመብት ተከራካሪዎች በበኩላቸው አግላይ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በዋናነትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቪርስቲዎችን እና በየአካባቢው የሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮችን የሚመለከት ነው።

ዋናን፣ አትሌቲክስን እና የጎልፍ ስፖርቶችን ጨምሮ በርካታ የስፖርት አስተዳዳሪ አካላት በተፈጥሯዊ የወንድ የእድገት ሂደት ውስጥ ያለፉ እና ፆታቸውን የለወጡ ሰዎች በሴቶች ዘርፍ እንዳይወዳደሩ አግደዋል።

አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳሉት ይህ የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን መብት በፌደራል መንግሥቱ ሕግ ጥበቃ ይደረግለታል በማለት ያስተላላፉትን አቋም የሚቀለብስ ነው።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተለያዩ የስፖርት ውድድር አዘጋጅ አካላትን ወደ ዋይት ሐውስ በመጥራት ሴት ስፖርተኞች እና ወላጆቻቸው ያላቸውን ስጋት በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተነግሯል።

ትዕዛዙን በተመለከተ የተናገሩ አንድ ባለሥልጣን፣ በአሜሪካ ግዛት ውስጥ በሚካሄዱ የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ውድድሮች ላይ ፆታቸውን ወደ ሴት የቀየሩ ሰዎች ከሴቶች ጋር በአንድ ላይ እንዲወዳደሩ አሜሪካ አትፈቅድም ብለዋል።

ይህ ውሳኔም በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ የሚካሄደውን የ2028 የኢሊምፒክ ውድድርን ጭምር እንደሚመለከት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተለይም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ ለመምጣት ለሚፈልጉ ፆታቸውን ለቀየሩ አትሌቶች የመግቢያ ቪዛ እንደማይሰጡ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔውን በፊርማቸው ከማጽደቃቸው በፊት ትራምፕ ባደረጉት ንግግር "በሴቶች ስፖርት ላይ የተከፈተው ጦርነት አብቅቷል" በማለት በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ላይ "የእኔ አስተዳደር ወንዶች ከሴቶች ጋር እየተወዳደሩ ሴት አትሌቶችን ሲያሸንፉ ቆሞ አይመለከትም" ብለዋል።

ጨምረውም የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት "ሴት አትሌት ነን በማለት በማጭበርበር ወደ አሜሪካ የመግቢያ ቪዛ የሚጠይቁ ወንዶችን ማመልከቻ ውድቅ እንዲያደርግ" መመሪያ እንሚሰጡ አሳውቀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቋል።

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ዊሊያምስ ኢኒስቲቲዩት የተደረገ ጥናት እንሚያመለክተው ከ13 ዓመት በላይ ከሆኑ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ መካከል ፆታቸውን የቀየሩት ከአንድ በመቶ በታች ሲሆኑ፣ በስፖርት የሚሳተፉት ደግሞ በጣም ጥቂቶች ናቸው።