ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ለተለያዩ አገራት ሙያተኞች የሚሰጠውን የአሜሪካ ቪዛ እንደሚደግፉ ተናገሩ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተለያዩ ሙያተኞች ቪዛ በመስጠት ወደ አሜሪካ የሚወስደውን የስደተኞች ፕሮግራም በተመለከተ ድጋፋቸውን ለኤለን መስክ እና ቪቬክ ራማስዋሚ ሰጡ።
ኤች-1ቢ (H-1B) የተባለው ለሙያተኞች የአሜሪካ ቪዛ የሚሰጥበትን አሠራር "እወደዋለሁ" ሲሉ ትራምፕ ለኒው ዮርክ ፖስት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ይህንን የቪዛ ዓይነት ሲተቹ ነበር።
ቪቬክ እና ኤለን የመንግሥትን ወጪ እንዲቆጣጠሩ በትራምፕ ተሹመዋል።
ቪቬክ የአሜሪካ ተቋማትን የቅጥር አካሄድ ተችቷል። ለአሜሪካ ኢኮኖሚ መጠናከር የውጭ አገር ሠራተኞች የላቀ ሚና አላቸውም ብሏል።
"የላቀ ችሎታ ካላቸው ሰዎች ይልቅ ደካማ ሠራተኞችን መቅጠር በአሜሪካ ተቋማት እየተለመደ መጥቷል" ብሏል።
ስደተኛ ጠል የሆኑ የትራምፕ ደጋፊዎች በዚህ ተቆጥተዋል።
ቪቬክ ከንግግሩ በኋላ "ኤች-1ቢ አሠራር ተበላሽቷል። መተካት አለበት" ብሏል።
"እነዚህ ቪዛዎች ደስ ይሉኛል። ለዛ ነው አሠራሩ ያለን። ለኔ የሚሠሩ ብዙ ኤች-1ቢ ቪዛ ያላቸው ሰዎች አሉ። ጥሩ አሠራር ነው" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ይህንን የቪዛ ዓይነት ሲተቹ ቆይተዋል።
ሆኖም ግን ከዚህ ቀደም ጄዲ ቫንስ በኤች-1ቢ ቪዛ ወደ አሜሪካ የተጓዙ ሠራተኞችን የሚቀጥርና የሚያሠራ ተቋም ነበረው።
ቀኝ ዘመም የትራምፕ ደጋፊዎች በቪቬክ ንግግር ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የትራምፕ ደጋፊው ስቲቭ ባነን ይህንን የቪዛ ዓይነት እንደሚነቅፍ ዋር ሩም በተባለው ፖድካስቱ ላይ ተናግሯል።
የቪቬክ አስተያየት ግን በኤለን መስክ ድጋፍ አግኝቷል። የላቀ ችሎታ ያላቸው መኃንዲሶች ወደ አሜሪካ የሚጓዙበት ነው ሲልም ተደምጧል።
"አሜሪካ ድል እያደረገች እንድትቀጥል ትክክለኛ የአስተሳሰብ መዋቅር ያስፈልጋል" ሲል በኤክስ ገጹ ጽፏል።
ተቺዎች ግን ሐሳቡን ነቅፈዋል።
በኤለን ተቋም ውስጥ በኤች1-ቢ ቪዛ አሜሪካ የሄዱ ሠራተኞች ደመወዛቸው 200,000 ዶላርና ከዛ በታች መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም የአሜሪካውያንን የክፍያ መጠን እንደሚያጠብ ተከራክረዋል።
"በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ጥላቻ የተሞሉ ዘረኞች የፓርቲው ውድቀት ስለሚሆኑ መወገድ አለባቸው" ብሏል ኤለን።
የቀድሞ የትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ "የአሜሪካ ሠራተኞችም የሥራ ባህላችንም ምንም ችግር የለበትም። ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለአሜሪካውያን እንጂ ለውጭ አገር ዜጎች አይደለም" ስትል ሐሳቡን ተቃውማለች።
እንደ ቪቬክ ሁሉ ኒኪ ከሕንዳውያን ስደተኛ ቤተሰቦች ነው የተወለደችው።
ፀረ ሙስሊም የሆነችውና የሴራ ትንታኔ በማሰራጨት የምትታወቀው የትራምፕ ዋነኛ ደጋፊ ሎራ ሎመር በሚሊዮኖች የታየ ስደተኛ ሠራተኞችን ነቃፊ ጽሑፍ አጋርታለች።
ሕንዳውያን ስደተኞችን "ወራሪ" በማለት ትራምፕ ኃላፊነት የሰጧቸውን የሕንድ የዘር ግንድ
ያላቸውን ሰዎች ተቃውማለች።
ኤለን መስክ ጽሑፏ ላይ ገደብ እንዳስቀመጠ በመናገርም ተቃውሞ አሰምታለች።
በዓመት ውስጥ ኤች-1ቢ ቪዛ የሚሰጣቸው ሰዎች 65,000 ሲሆኑ ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ተጨማሪ 20,000 ሰዎች ይካተታሉ።
የስደተኞች አማካሪ ተቋም 'ባውንድለስ' በሠራው ጥናት መሠረት ይሄ ቪዛ ከሚሰጣቸው መካከል 73% ሕንዳውያን እና 12% ቻይናውያን ናቸው።
ትራምፕ ሥልጣን እንደያዙ ሰንድ አልባ ስደተኞችን እንደሚያባርሩ ተናግረዋል።
ትራምፕ በኤለን ጫና ሥር ናቸው በሚል የሚናፈሰውን ወሬ በወግ አጣባቂ ውይይት ላይ ውድቅ አድርገዋል።
"ትራምፕ ፕሬዝዳንትነቱን ለኤለን ሊሰጥ ነው የሚለው ውሸት። እሱ ፕሬዝዳንት አይሆንም" ብልዋል።