ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ደቡብ ኮሪያ ተማሪዎች በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ስልክ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ሕግ አወጣች
ደቡብ ኮሪያ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች የግል የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎችን መጠቀምን የሚከለክል ሕግ አወጣች።
ሕጉ ከሚቀጥለው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ የስልክ ሱስን ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል።
የሕግ አውጪዎች፣ ወላጆች እና መምህራን የሞባይል ስልክ አጠቃቀም የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ብቃት እየጎዳው መሆኑን፣ እንዲሁም በጥናት ሊያሳልፉ የሚችሉትን ጊዜ እንደሚሻማ በመግለጽ ይከራከራሉ።
አብዛኞቹ የደቡብ ኮሪያ ትምህርት ቤቶች አንዳንድ የስማርት ስልኮች እገዳን አስቀድመው ተግባራዊ አድርገዋል።
እንደ ፊንላንድ እና ፈረንሣይ ያሉ አገራት ታዳጊ ልጆች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስልኮችን እንዳይጠቀሙ በተወሰነ መልኩ እገዳ ጥለዋል።
ሌሎች እንደ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና ቻይና ያሉ አገራት ደግሞ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የስልክ አጠቃቀምን ገድበዋል።
ነገር ግን ደቡብ ኮሪያ ይህን መሰል እገዳ በሕግ በመደንገግ ረገድ ከጥቂት አገራት መካከል አንዷ ሆናለች።
በዋና ከተማዋ ሴዑል የ14 ዓመት ልጅ እናት የሆነችው ቾይ ኢዩን ያንግ በዚህ ዘመን ያሉ ልጆች "ስማርት ስልኮቻቸውን የሚያስቀምጡ አይመስሉም" ትላለች።
በስልካቸው ላይ ዓይናቸውን ተክለው የሚውሉት ልጆች ብቻ አይደሉም።
በ2024 የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ባደረገው ጥናት መሠረት ከ51 ሚሊዮን የአገሪቱ ሕዝብ ሩብ ያህሉ በስልኮቻቸው ላይ ጥገኛ ናቸው።
ነገር ግን ይህ ቁጥር ከ10 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ላይ ከእጥፍ በላይ ወይም 43 በመቶ ይሆናል። ባለፉት ዓመታትም ይህ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጥናቱ ጨምሮ አሳይቷል።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙት ታዳጊዎች መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቪዲዮዎችን በመመልከት የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቆጣጠር እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
ወላጆቻቸውም ይህ ልጆች እንዲያከናውኑ የሚጠበቁባቸውን ሌሎች ነገሮችን በአግባቡ እንዳይፈጽሙ እንቅፋት እየሆነባቸው ነው ብለው ይፈራሉ።
"ትምህርት ቤት ሲሄዱ መማር አለባቸው፤ ማጥናት፣ ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወት እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ አለባቸው። ነገር ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮር አልቻሉም" ስትል ቾይ ትናገራለች።
"ከጓደኞቻቸው ጋር ሲጨዋወቱ እንኳን በፍጥነት ወደ ስልካቸው ይመለሳሉ፣ ይህ ደግሞ በመማሪያ ክፍላቸውም ላይም ጣልቃ ይገባል።"
ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሏቸው ኪም ሱን ደግሞ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚኖር "ስድብ እና ዘለፋ" ያስጨንቃቸዋል።
"ሕጻናት እርስ በእርሳቸው ሊታሰቡ የማይችሉ ስድቦችን ይመላለሳሉ" ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሕጉን ያቀረበው የተቃዋሚው ፒፕል ፓወር ፓርቲ የፓርላማ አባል ቾ ጁንግ ሁን ሌሎች አገራት ተመሳሳይ እርምጃ ሲወስዱ ፓርቲያቸው መበረታታቱን ይናገራሉ።
የስማርትፎን ሱስ "በተማሪ የአእምሮ እና ስሜታዊ ዕድገት ላይ እጅግ ጎጂ ተጽዕኖ እንዳለው የሚያሳይ ሳይንሳዊ እና የሕክምና ማረጋገጫ" አለ ይላሉ።
ምንም እንኳን ሕጉ በትምህርት ሰዓት ብቻ ስልክ መጠቀምን የሚከለክል ቢሆንም፣ መምህራን ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ስልኮቻቸውን እንዳይጠቀሙ የማስቆም ሥልጣን ይሰጣል።
እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ስለ ስማርት ስልኮች ትክክለኛ አጠቃቀም እንዲያስተምሩ ይጠይቃል።
ሕጉ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ተማሪዎች ስልካቸውን መጠቀም ስለሚችሉበት ሁኔታ ደንግጓል።
አካል ጉዳተኛ ወይም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በስልካቸው አጋዥ መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ፣ እንዲሁም ለትምህርታዊ ዓላማዎች ወይም በድንገተኛ አደጋዎች ወቅት እንዲጠቀሙ ይፈቅዳል።
መምህራን ግን በእገዳው ላይ የተከፋፈለ አቋም ነው ያላቸው።
በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ሁለቱ ዋና ዋና የመምህራን ማኅበራት መካከል ወግ አጥባቂው የኮሪያ መምህራን ማኅበር ብቻ ሕጉን የደገፈ ሲሆን፣ በክፍል ውስጥ ስልኮችን ለመገደብ "በጣም ጠንካራ የሕግ መሠረት" ይሰጣል ብሏል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ 70 በመቶ የሚጠጉ መምህራን በስማርት ስልኮች አጠቃቀም ምክንያት የክፍል ውስጥ መማር ማስተማር መስተጓጎሉን ገልጸው ነበር ይላሉ።
አንዳንድ ተማሪዎች "[መምህራኑ የስልክ አጠቃቀምን በሚገድቡበት ወቅት] ስሜታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም፤ የሚሳደቡ ወይም መምህራኑን የሚያጠቁ ገጥመውናል።"
ሌላኛው ቡድን የኮሪያ መምህራን እና የትምህርት ሠራተኞች ማኅበር ደግሞ በሕጉ ላይ ይፋዊ አቋም የለንም ብሏል።
አንዳንድ አባላት ግን ሕጉ የተማሪዎችን ስማርት ስልኮቻቸውን የመጠቀም መብትን የሚጥስ ነው የሚል ስጋት እንዳደረባቸው አስታውቋል።