ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጆች “ከእሣት ጋር እየተጫወቱ ነው” ሲሉ የኡጋንዳው ፕሬዝደንት አስጠነቀቁ
በጎረቤት አገር ኬንያ ባሉ ወጣቶች ተነሳስተው በኡጋንዳ የተቃውሞ ስልፍ የጠሩ ወጣቶች "በእሳት አትጫወቱ" የሚል ማሳሰቢያ ከፕሬዝዳንቱ ደረሳቸው።
የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፀረ-ሙስና ተቃውሞ እያሰሙ ማክሰኞ ወደ ፓርላማ ለመገስገስ ያሰቡ ወጣቶችን “ከእሣት ጋር ጨዋታ” አቁሙ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኡጋንዳ ወጣቶች በመንግሥት ደረጃ የሚስተዋለውን ሙስና ለማስቆም በማኅበራዊ ሚድያዎች የሰልፍ ጥሪ ሲያስተባብሩ ታይተዋል።
የኡጋንዳው የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪ የጎረቤት ሀገር ኬንያ ተቃውሞን ተከትሎ የመጣ ነው። ኬንያዊያን ላለፉት ሳምንታት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት ፕሬዝደንት ሩቶ ተግባራዊ ሊያደረጉት ያሰቡትን የግብር ጭማሪ እንዲሰርዙ ማስገደዳቸው ይታወቃል።
የኬንያ ተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች ፕሬዝደንቱ ካቢኒያወቸውን በትነው የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ሙከራ ቢያደርጉም ሩቶ ከመንበራቸው መውረድ አለባቸው እያሉ ነው።
ሙሴቬኒ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው ታዲያ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ያሰቡ ሰዎችን እንደማይታገሱ ተናግረዋል።
“እኛ ሐብት በመፍጠር ላይ ስለሆንን ጊዜ የለንም. . . እናንተ ደግሞ ሰላማችንን መበጥበጥ ነው የምትፈልጉት። ከእሣት ጋር እየተጫወታችሁ ነው፤ እንድትረብሹን አንፈቅድላችሁም” ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 1986 ሥልጣን ላይ የወጡት ሙሴቬኒ የሥልጣን ጊዜያቸውን እያራዘሙ ያሉት በጉልበት ነው የሚል ትችት ከተቃዋሚዎቻቸው ይሰነዘርባቸዋል። ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር በተረጋጋ ሁኔታ እየመሩ ነው ሲሉ ያወደሷቸዋል።
ፕሬዝደንቱ ከማስጠንቀቂያቸው በተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጆች “ከውጭ ኃይሎች ጋር እየሠሩ” ኡጋንዳን ሊበጠብጡ ነው ሲሉ ኮንነዋል። ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የሀገሪቱ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጆች ሊያደርጉ ላሰቡት ተቃውሞ ፈቃድ እንደማይሰጥ አሳውቋል።
ከቁንጮ ተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎቹ አንዱ ሰልፉ እንደሚካሄድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ሉዌዝ አሎይኪን “ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የፖሊስን ይሁንታ አንፈልግም። ይህ ሕገ-መንግሥታዊ መብታችን ነው” ማለታቸውን የዜና ወኪል ፅፏል።
የዩናይትድ ስቴትስ እና ዩኬ መንግሥታት የኡጋንዳ ፓርላማ አፈ-ጉባዔ አኒታ አኔት አሞንግ ላይ በሙስና ምክንያት ማዕቀብ መጣላቸው ይታወቃል።
አፈ-ጉባዔዋ ግን የተወቀሱበትን ወንጀል እንዳልፈፀሙ ይናገራሉ።
በማዕቀቡ መሠረቱ አፈ-ጉባዔዋ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ መሄድ አይችሉም። ዩኬ፤ ከጉዞ ማዕቀቡ በተጨማሪ ተቀማጭ ሀብታቸው እንዳይንቀሳቀስ እንደምታደርግ አሳውቃለች።
ከአኒታ በተጨማሪ ሁለት ሌሎች ግለሰቦች ማዕቀብ የተጣለባቸው ሲሆን በሙስና መጠርጠራቸውን ተከትሎ ሙሴቬኒ ከሥልጣን አባረዋቸዋል።
ሁለቱ ባለሥልጣናት በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል አቅም ለሌላቸው ሰዎች እንዲውል የታቀደ የቤት ቆርቆሮን በተመለከተ ሙስና መሥራታቸው ተነግሯል። ሁለቱም ግለሰቦች ይህን ወቀሳ ያስተባብላሉ።
በጎረቤት ሀገር ኬንያ ደግሞ ፕሬዝደንት ሩቶ ለሳምንታት የቀጠለው ተቃውሞን “ይበቃል ማለት ይበቃል ነው” ሲሉ ተቃውሞ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በ2022 ምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙት ሩቶ በፕሬዝደንትነት ዘመናቸው እንዲህ ያለ ተቃውሞ ገጥሟቸው አያውቅም።
የኬንያ አክቲቪስቶች ማክሰኞ ዕለት የሚካሄድ የተቃውሞ ሰልፍ የጠሩ ሲሆን ፕሬዝደንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ይገኛሉ።
በምዕራባዊው የሀገሪቱ ክፍል ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያድረጉት ፕሬዝደንት ሩቶ የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጆች “እንደተደበቁ አይቀሩም” ብለው አዘጋጆቹ “ወደፊት መጥተው ይህ አመፅ ምን ሊያሳካ እንዳሰበ ይንገሩን” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
አዘጋጆቹ ምንም እንኳ በአብዛኛው የተቃውሞ ሰልፎቹ ሰላማዊ ናቸው ቢሉም ፖሊስ እና የሀገሪቱ ወታደራዊ ሠራዊት ኃይል ተጠቅሞ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ገድሏል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ላለፉት ሳምንታት በዘለቀው ተቃውሞ ምክንያት እስካሁን ቢያስን 50 ሰልፈኞች ሲገደሉ 413 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው በመንግሥት የሚደገፈው የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል።