ከ30 ዓመት በላይ ኤችአይቪ በደሙ የነበረበት ግለሰብ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ተነገረ

የኤችአይቪ የደም ምርመራ በላብራቶሪ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአውሮፓውያኑ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በደሙ ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስ የነበረበት ግለሰብ ከበሽታው ነጻ መሆኑን ዶክተሮች ገለጹ።

በዚህም እስካሁን ከኤችአይቪ ቫይረስ ነጻ መሆናቸው ከተነገረላቸው ሰዎች አራተኛው ሆኗል።

ግለሰቡ የነበረበትን የደም ካንሰር ለማከም በተፈጥሮ ቫይረሱን ለመቋቋም ከሚችል አንድ ግለሰብ የአጥንት መቅኔ ዝውውር ሕክምና ተደርጎለታል።

ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ የተነገረለት ግለሰብ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የ66 ዓመት ሰው ሲሆን፣ አሁን የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰድ ማቆሙ ተነግሯል።

ቫይረሱ በደሙ ውስጥ እንደሌለ ባወቀበት ጊዜ ግለሰቡ በሰጠው አስተያየት ከቫይረሱ መፈወሱን “ከአድናቆት በላይ ነው” ሲል ገልጾታል።

ግለሰቡ በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት፣ ዱዋርቴ ውስጥ በሚገኘው ‘ሲቲ ኦፍ ሆፕ’ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምናውን ሲከታተል የቆ ሲሆን ማንነቱ እንዲገለጽ ስላልፈለገ መጠሪያው በሆስፒታሉ ስም እንዲሆን ጠይቋል።

እንደ ግለሰቡ በቫይረሱ ተይዘው የነበሩ አብዛኞቹ ጓደኞቹ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ከመምጣቱ በፊት ለሞት ተዳርገዋል።

እነዚህ መድኃኒቶች በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ በደማቸው ያለ ሰዎች ከጤናማነት ጋር የተቀራረበ ሕይወትን እየመሩ ነው።

ቫይረሱ የሰውን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ ሥርዓት በመጉዳት ወደ ኤድስ በሽታ የሚያመራ ሲሆን በሽታውን ለመቋቋም ጥረት ያደርጋል።

ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ የተገለጸው ግለሰብ እንዳለው “ከ35 ዓመት በፊት ቫይረሱ እንዳለብኝ በምርመራ ሲረጋገጥ፣ እንደሌሎቹ ሁሉ ሞት የተፈረደብኝ ያህል ነበር ያሰብኩት። ፈጽሞ ከቫይረሱ ነጻ የምሆንበት ቀን ይመጣል ብዬ አስቤ አላውቅም” ብሏል።

ግለሰቡ በ63 ዓመቱ የደም ካንሰር ስለተገኘበት በካንሰር የተጠቁትን ህዋሳቱን ለመተካት የአጥንት መቅኔ ዝውውር ሕክምና ተደርጎለታል።

በዚህ ወቅትም የአጥንት መቅኔውን የለገሰው ግለሰብ ኤችኤይቪ የሚቋቋም ተፈጥሮ ስለነበረው ለግለሰቡ መፈወስ ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።

የኤችአይቪ ቫይረስ በሽታን ተከላካይ ነጭ የደም ህዋሳትን በማጥቃት ወደ ኤድስ የሚሸጋገር ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ግን ይህንን የሚከላከል ተፈጥሯዊ ባህሪ እንዳላቸው ተደርሶበታል።

ከኤችአይቪ ነጻ የሆነው ሕመምተኛ የመቅኔ ሽግግር ከተደረገለት በኋላ በሐኪሞች ክትትል ሥር ቆይቶ ቫይረሱ በደሙ ውስጥ ከማይለይበት ደረጃ ላይ መድረሱን አረጋግጠዋል።

በዚህም ከ30 ዓመት በላይ ሲወስደው የነበረው የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒትን እንዲያቆም በሐኪሞቹ ተነግሮታል።

ከ10 ዓመት በፊት ራይ ብራውን የተባለው ግለሰብ ከኤችአይቪ ነጻ መሆኑ የተገለጸ የመጀመሪያ ሰው ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሌሎች ሦስት ሰዎችም ከበሽታው መፈወሳቸው ተዘግቧል።

አሁን አሜሪካ ውስጥ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ የተነገረው ግለሰብ በዕድሜ የገፋ ቫይረሱ በደሙ የነበረበት እና የመጀመሪያው ሰው ሲሆን፣ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ለረዥም ጊዜ የወሰደ እንደሆነም ተነግሯል።