ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሶማሌ ክልል በደረሰ የባቡር አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው
በሶማሌ ክልል ሺንሌ ከተማ ውስጥ በደረሰ የባቡር አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሲሞቱ 27 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገለጹ።
ሰኞ፣ ጥቅምት 11/ 2018 ዓ.ም. ሌሊት ላይ በደረሰው በዚህ አደጋ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎች ከባድ ጉዳት እንዳጋጠማቸው የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ መሐመድ አደም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ለሕክምና ወደ ሺንሌ፣ ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተሞች እንደተወሰዱ ኃላፊው ገልጸዋል።
አደጋው ያጋጠመው ለክስተቱ ምክንያት የሆነው ባቡር ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሰጠ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መሐመድ፣ ነገር ግን በአደጋው መንስኤ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ከአደጋው መከሰት በኋላ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከተለዩ በኋላ ባቡሩ ውስጥ የቀሩ ሰው ይኖራል በሚል ስጋት የሞቱ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ሊጨምረው እንደሚችል ሲገለጽ ነበር።
ሆኖም አቶ መሐመድ በሥፍራው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መሰማራታቸውን እና የቀረ ሰው አለመኖሩን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
የሕዝብ እና የጭነት ማጓጓዣ በሆነው ባቡሩ ላይ አደጋው የደረሰው ከደዋሌ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ እየተጓዘ ባለበት ወቅት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር 29 መድረሱን የሺንሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀብሪል ኡመር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው አደጋው የደረሰው ባቡሩ ባጋጠመው የሞተር ችግር ምክንያት ቁልቁለት ቦታ ላይ ከቆሙ ሁለት የባቡር ፉርጎዎች ጋር በመጋጨቱ መሆኑን አስረድተዋል።
ለአደጋው መንስኤ የሆነው ባቡር ስኳር እና ዱቄት ከጫኑ ሁለት የባቡር ፉርጎዎች ጋር በመጋጨቱ መገልበጡን እና በዚህም ሳቢያ በሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አቶ ጂብሪል ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል የባቡር ሠራተኛ የሆኑ ሴቶች እንደሚገኙበትም አቶ ጂብሪል አክለዋል።
የድሬዳዋ የባቡር መንገድ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ዳባር ካዳንም አደጋው መድረሱን ለክልሉ ቴሌቪዥን አረጋግጠው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ኡማር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በተከሰተው አደጋ ለተጎዱ ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
አደጋው ያጋጠማቸው ባቡር እና ፉርጎዎች በድሬዳዋ ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅት ሥር የሚተዳደሩ መሆናቸው ተዘግቧል።
በኢትዮጵያ አልፎ አልፎም ቢሆን የባቡር አደጋዎች ቢያጋጥሙም የሰኞ ሌሊቱ አደጋ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት ነው።
ከስድስት ዓመታት በፊት ከሰበታ ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ የነበረ የዕቃ ጫኝ ባቡር ግጭት አጋጥሞት እንደነበር ይታወሳል።
ከሰበታ ወደ ጅቡቲ በማቅናት ላይ የነበረ 17 ፉርጎ የሚጎትት የዕቃ መጫኛ ባቡር ግጭት ደርሶበት የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መንገድ እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር።