ኡጋንዳ ሲቪሎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚዳኙበትን ሕግ አፀደቀች

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ጥቅም ደግፈዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ጥቅም ደግፈዋል

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ሲቪሎች በአንዳንድ ሁኔታዎች በድጋሚ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚዳኙበትን የሕግ ማሻሻያ ፈረሙ።

ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት የፍርድ ሂደትን የሚፈቅድ ሕግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በሚል ባለፈው ጥር የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቶበታል።

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፊት ሲቪሎች እንደ ጦር መሳሪያ እና ወታደራዊ የደንብ ልብስ ይዘው ከተገኙ የፍርድ ሂደታቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት ይታይ ነበር።

የመብት ተሟጋቾች ሕጉ የመንግሥትን ተቺዎች ለማሳደድ ጥቅም ላይ ውሏል በሚል ቅሬታ አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባለፈው ወር ሕጉ የአገሪቱን ትልቁን ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚጥስ ነው የሚል ተቃውሞ ቢገጥመውም ማሻሻያውን አፅድቀዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ አሊያም የዳኝነትን ተግባር ለመከወን አቅም የላቸውም ማለታቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ማኅበር በወቅቱ ገልጿል።

ማሻሻያው ግን አንዳንድ ችግሮችን ለመፍታት የሚሞክር ይመስላል።

ፍርድ ቤቱን የሚመሩ ባለሙያዎች አግባብነት ያለው የሕግ ስልጠና እና ማረጋገጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይጠቅሳል። ከዚህ በተጨማሪም ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነፃ እና ገለልተኛ ይሆናሉ ይላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሲቪሎች የውትድርና መገልገያ ቁሳቁሶችን ይዘው ከተገኙ ተላልፈው ይሰጣሉ።

የአገሪቱ ጦር ቃል አቀባይ ሕጉ በምክር ቤት አባላት ከፀደቀ በኋላ "ሕጉ በታጠቁ ነውጠኛ ወንጀለኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል፤ ዲሞክራሲያዊ ሂደቱን ለመናድ የሚመሰረቱ ታጣቂ የፖለቲካ ቡድኖችን ይከላከላል፤ ብሔራዊ ደኅንነት ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ያደርጋል። መጀመሪያም ካልተበላሸ አታስተካክለው" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ቦቢ ዋይን ሕጉ በእርሳቸው እና በሌሎች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።

"በተቃዋሚ ጎራ ያለን ሁላችንም ይህ ሕግ ያነጣጥርብናል" ሲሉ ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግረዋል።

ለበርካታ ዓመታት ተሟጋቾች ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን መንግሥት ተቃዋሚዎችን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው እንዲሁም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የውሸት ማስረጃዎች ይቀርባሉ በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ የሆኑት ጓዋያ ተጉሌ ባለፈው የካቲት ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ፒድካስት "የፖለቲካ ተቀናቃኝ ከሆንክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እንድትቀርብ መንገድ ይፈልጋሉ። እናም እጣ ፈንታህ እንዳበቃለት ታውቃለህ። . . . አንዴ እዚህ ከገባህ የፍትኅን ደጅ አትረግጥም" ሲሉ ጫናውን ተናግረዋል።

ጠበቃው አክለውም ፍርድ ቤቶች ከጦር አለቆች ውሳኔዎችን የሚጠባበቁ በመሆናቸው ሰዎች ካለ ዋስትና በእስር ዓመታትን ሊያሳልፉ እንደሚችሉ እና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ደግሞ ከመደበኛው ፍርድ ቤት በበለጠ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ገልፀዋል።

የቅርብ ጊዜ ጉዳይ የሆነው የታዋቂ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኪዛ ቢሲጂ ጉዳይ ሲሆን ፖለቲከኛው በኬንያ ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ በወታደራዊ ፍርድ ሽጉጥ በመያዝ እና በውጭ አገር መሳሪያ ለመግዛት በመሞከር ክስ ቀርቦባቸዋል።

ፖለቲከኛው ክሱን ውሸት ብለውታል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ ጉዳያቸው ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት ሲተላለፍ የቀረቡባቸው ክሶች ውድቅ ተደርገው አዲስ ክሶች ተመስርተውባቸዋል።

እ.አ.አ ከ1986 ጀምሮ ስልጣን ላይ ያሉት ዩሪ ሙሴቬኒ ፍርዱን "የተሳሳተ ውሳኔ" ያሉት ሲሆን አገራቸው በዳኞች ሳይሆን በሕዝቦች ነው የምትመራው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ ቀደም ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን በመደገፍ "ያለምንም ልዩነት ሰዎችን በመሳሪያ እየገደሉ ያሉ የወንጀለኞችን እና አሸባሪዎችን ከፍተኛ እንቅስቃሴ" አደብ ያስይዛል ብለዋል።