በአሜሪካ ኢሚግሬሽን ለ100 ቀናት የታሰረው ፍልስጤማዊ ተሟጋች የ20 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ክስ መሰረተ

የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ምሩቁ ማህሙድ ካሊል በዩኒቨርስቲው በነበሩ የፍልስጤም ድጋፎች በመሳተፉ ለ100 ቀናት በኢሚግሬሽን መታሰሩን ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ላደረሰበት ጉዳት ካሳ እንዲከፍለው ከሰሰ።

ጠበቆቹ ደንበኛቸው ለሃሰተኛ እስር፣ ተንኮል ለተሞላበት ክስ እንዲሁም ጸረ- ሴማዊ በሚል የትራምፕ አስተዳደር ባለስልጣናት ላደረሱት ጉዳት 20 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ ክሳቸውን ሐሙስ ዕለት አስገብተዋል።

ማህሙድ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ባለሥልጣናት እና የፍልስጤም ደጋፊ በሆኑ ተማሪዎች መካከል የተካሄዱ ድርድሮችን በማሸማገል እንዲሁም ለፍልስጤም ባለው የጸና ድጋፍ ታዋቂ ሆኗል።

የአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ማህሙድ በኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ለእስር የተዳረገው የካቲት 29/ 2017 ዓ.ም ነበር።

የማህሙድ የሰብዓዊ ተሟጋችነት እንቅስቃሴ ከአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የሚጻረር ነው በሚል የአሜሪካ መንግሥት ከአገር ሊያባርረው ይፈልጋል።

ሆኖም ማህሙድ ከአገር ለመውጣት ወይም የህብረተሰቡ ስጋት አይደለም በሚል ከኢሚግሬሽን እስር እንዲለቀቅ እና የኢሚግሬሽን ሂደቱ በውጭ ሆኖ እንዲከታተል የፌደራል ዳኛ በሰኔ ወር ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ማህሙድ በሃሰተኛ ሁኔታ በቁጥጥር ውሎ ለእስር እንደታደረገ፣ ሴራ የተሞላበት ክስ እንደቀረበበት፣ ያለ አግባብ ሂደቱን ማወሳሰብ፣ ሆን ብሎ ስሜቱ እንዲቃወስ የሚያደርጉ ተግባራት በአሜሪካ መንሥት ባለስልጣናት ተፈጽሞበታል ሲሉ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

እነዚሀ ሁሉ የደረሱበት ጉዳቶች መንስዔያቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማህሙድ " በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስጋትን የሚጋርጥ እንዲሁም የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ጥቅምን የሚጎዳ" ነው ሲሉ መፈረጃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ጠበቆቹ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍረጃ "እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ እያደረገችው ያለውን የዘር ፍጅት እንዲሁም አሜሪካ ለዚህ የምታደርገውን ድጋፍ" በሚቃወሙ አሜሪካዊ ባልሆኑ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ የህግ ባለሙያዎቹ ተከራክረዋል።

የፍልስጤም ደጋፊ ተማሪዎች እስራኤል በጋዛ ላይ የምታደርገውን የዘር ጭፍጨፋ በጦር መሳሪያ እና በሌሎች ነገሮች እያገዙ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ጋር የንግድ ሽርክናቸውን ዩኒቨርስቲዎች እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው የሚለውን አትቀበለውም።

የአገር ውስጥ ደህነነት ቢሮ ቃለ አቀባይ ትሪሺያ ማክላውሊን የማህሙድን ክስ "የማይረባ" ሲሉ ያጣጣሉ ሲሆን የአይሁድ ተማሪዎች "ላይ ጥላቻ ያዘለ ትርክቶችን ተናግሯል" በሚል በመግለጫቸው መክሰሳቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ አስነብቧል።

ማህሙድ በበኩሉ የትራምፕ አስተዳደር ለእስሩ ኃላፊነት እንዲወስድ፤ "በተጨማሪም ይህ ሁኔታ በማህበረሰቡ፣ ፍልስጤምን በሚደግፉ፣ በአጠቃላይ በተማሪዎች እና በአሜሪካ ህዝብ ላይ ለፈጠረው ድንጋጤ ተጠያቂ እንዲሆኑ" ክሱ መቅረቡን ገልጿል።

"በእኔ እና በሌሎች ላይ ለፈጸሙት ጥፋት 20 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ወይም የትራምፕ አስተዳደር በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ" ፍላጎቱ መሆኑን ገልጿል።

"በኔ ላይ ይህንን ሞክረው አልተሳካላቸውም። ነገር ግን ጉዳቱ እንዳለ ነው። ለሰሩት ስራ ተጠያቂነት የማይቀርብባቸው ከሆነ በዚህ ተግባራቸው መቀጠላቸው የማይቀር ነው" ብሏል።

የአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ማህሙድ ለእስር የተዳረገው በኒውዮርክ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከነፍሰጡር ባለቤቱ ፊት ለፊት ነው።