ከማዳበሪያ ግዢ ጋር በተያያዘ 11 ባለሥልጣናት መታሰራቸውን ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ

ከአፈር ማዳበሪያ ግዢ ጋር በተያያዘ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የሌሎች የመንግሥት ተቋማት አስራ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
አስራ አንዱ ግለሰቦች ከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ክስ ተመስርቶባቸው "ወደ ማረሚያ ቤት መውረዳቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በዚሁ መሠረትም አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ አቶ ወልደአብ ደምሴ በኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ አቶ ተንሳይ ሜጫ በኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ ወ/ሪት መንበረ ኃ/ማርያም በኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ አቶ ሚሊዮን ገረመው በኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የግዢ ባለሙያ፤ አቶ ሰለሞን ገብሬ ሥራ አስፈጻሚ።
በተጨማሪም አቶ መንግስቱ ተስፋ በግብርና ሚኒስቴር ሥራ አስፈጻሚ፤ አቶ ዘላለም ዳኜ በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብዓት ግዢ እና ትራንዚት ክፍል ሥራ አስኪያጅ፤ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ፤ ፀጋዬ በርሀ በተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዳይሬክተር፤ አንዲሁም አቶ አለባቸው ሞልቶት የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የጂቡቲ ቅርንጫፍ ኃላፊ መሆናቸው ተገልጿል።
በዚህ የከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት አስራ አንዱ ግለሰቦች በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ከሚገባው ከፍተኛ መጠን ካለው ከአፈር ማዳበሪያ ግዢ እና ጥራት ጋር የተያያዘ ኃላፊነት ነበራቸው።
ፌደራል ፖሊስ እንዳለው በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች "በጋራ እና በተናጠል የተሰጣቸውን ሥልጣን ያለ አግባብ በመጠቀም" ፈጸሙት በተባለው ወንጀል ለእስር ተዳርገዋል።
ጨምሮም የክልል መንግሥታት ለኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ እንዲፈፅም የሰጡትን ውክልና እና የኮፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔዎች፣ የግዢ መመሪያዎችን፣ ውሎች እና ድንጋጌዎችን ጥሰዋል ብሏል።
ተከሳሾቹ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ የአፈር ማዳበሪያ ጋር በተያያዘ 204 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ያለአግባብ በመክፈል፣ መቀለ ከተባለችው መርከብ ላይ ወሳኝ የሆነ ክፍል ተነቀለ በማለት ኮርፖሬሽኑ 100 ሺህ ዶላር ተጨማሪ የማጓጓዣ ወጪ ማስወጣታቸው ክስ ቀርቦባቸዋል።
እንዲሁም ጥራት የሌለው የአፈር ማዳበሪያ የተጓጓዘበት ወጪ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላርን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ወይም ከ5 ቢሊየን ብር በላይ "በመመዝበር በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ" ተከሰዋል።
ፌደራል ፖሊስ አስራ አንዱ ግለሰቦቸ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጀል የምርመራ መዝገብ አጣርቶ በፍትሕ ሚኒስቴር ለዐቃቤ ሕግ ከላከ በኋላ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ተመሥርቶ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ መደረጉን ገልጿል።















