የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸመው አፍጋኒስታናዊ ለሳምንታት ጨለማ ክፍል ውስጥ ብቻውን ያሳልፍ እንደነበር መረጃዎች አመለከቱ

ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ከተማ የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ ወታደሮች ላይ ተኩስ በመክፈት የተጠረጠረው አፍጋኒስታናዊ፤ ጨለማ ክፍል ውስጥ ብቻውን ሳምንታትን ሲያሳልፍ እና "በአእምሮ መቃወስ" ሲሰቃይ እንደነበር የኢሜይል ልውውጦች አመለከቱ።

በአውሮፓውያኑ 2024 እነዚህን ማስታወሻዎች የጻፉት ከአፍጋኒስታን ሸሽቶ የመጣው ተጠርጣሪ እና ቤተሰቡ ወደ አሜሪካ በገቡበት ወቅት እገዛ ሲያደርጉላቸው የነበሩ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ እንደሆኑ ተገልጿል።

ራህማኑላህ ላካንዋን፤ "ድንገተኛ" ጥቃት ከፍቶ የ20 ዓመቷን የብሔራዊ ዘብ አባል ሳራ ብክስቶር በመግደል እንዲሁም የ24 ዓመቱን አንድሪው ዎልፊን ክፉኛ በማቁሰል ተከስሷል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንደሚናገሩት የ29 ዓመቱ ላካንዋል በ2021 ወደ አሜሪካ የገባው በአፍጋኒስታን ተሰማርተው ከነበሩ የአሜሪካ ወታደርች ጋር ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ጥገኝነት እንዲያገኙ ባስቻለው ፕሮግራም አማካኝነት ነው።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ያገኛቸው የኤሜይል ልውውጦች እንደሚያሳዩት ላካንዋል በአእምሮው ጤንነት ምክንያት ሲሰቃይ ነበር።

እሑድ ዕለት ከኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም፤ አፍጋኒስታናዊው "ወደ አገሪቱ ከገባ ጊዜ አንስቶ አክራሪ ሆኗል" በማለት ከስሰዋል። ባለሥልጣናት፤ ጥቃቱን የፈጸመውም "ከአገሩ ማኅበረሰብ እና መንግሥት ጋር ባለው ግንኙነት አማካኝነት" የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

የአፍጋኒስታን ዜግነት ያለው ላካንዋል ወደ አሜሪካ የገባበት 'አላይስ ዌልካም ፕሮግራም' የተሰኘው መርሃ ግብር በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሥልጣን ዘመን የተጀመረ ነው። ፕሮግራሙ የተጀመረው በአፍጋኒስታን የነበሩ የአሜሪካ ወታደሮች ቀውስ በተሞላበት መልኩ ከአገሪቱ በወጡበት ወቅት ነው።

ታሊባን አፍጋኒስታንን መልሶ መቆጣጠሩን ተከትሎ እንደ ላካንዋን ያሉ ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር የተባበሩ ሰዎች የበቀል እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል የሚል ስጋት ነበር። በአሜሪካ ጥገኝነት ጥያቄ ያቀረበው በ2024 እንደሆነ እና በዚህ ዓመት ማመልከቻው ተቀባይት እንዳገኘ አንድ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

በዋሽንግተን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ቤሊንግሃም ከተማ ይኖር የነበረው ከባለቤቱ እና አምስት ልጆቹ ጋር ነው። ላካዋን ይህንን ጥቃት እንዲፈጽም ያነሳሳው ምክንያት ምን እንደሆነ አልታወቀም።

ነገር ግን 'ዩኤስ ኮሚቴ ፎር ረፊውጂስ ኤንድ ኤሚግራትስ' የተሰኘው በስደተኞች ላይ የሚሠራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ባለፈው ዓመት የላካቸው የኢሜይል መልዕክቶች የላካዋን ሕይወት በአሜሪካ ምን ዓይነት ገጽታ እንደነበረው ማሳየት ጀምረዋል።

ከአፍጋኒስታን የመጣው ቤተሰብ አሜሪካ ውስጥ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ሲያግዙ የነበሩ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ በ2024 መጀመሪያ ጥር 11 ላይ በጻፉት ኢሜይል፤ ላካንዋን ለአንድ ዓመት ሥራ አጥ ሆኖ መቆየቱን እና ቤተሰቡ ከቤት የመባረረ አደጋ እንደገጠማቸው በመጥቀስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሲቢኤስ የተመለከተው የኢሜይል መልዕክት፤ "የወርልድ ሪሊፍ በጎ ፈቃደኞች ለቤተሰቡ ነገሮችን ለማስተካከል እየሞከሩ ነው። ነገር ግን አባትየው መፍትሔ ያልተሰጠው የአእምሮ ጤና እክል ያለበት ይመስለኛል፤ ከማንም ጋር አይነጋገርም" ይላል። በኤሜይሉ ላይ የተጠቀሰው ወርልድ ሪሊፍ የአፍጋኒስታን ዜጎች የጥገኝነት ዝውውር ላይ እገዛ የሚያደርግ ቡድን ነው።

ከ20 ቀናት በኋላ በጥር 31/2024 በተላከ ሌላ ኢሜይል ላይ ደግሞ የእርዳታ ሠራተኛው፤ ላካንዋን "ለሳምንታት አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ጨለማ በሆነው መኝታ ቤቱ ውስጥ ነው። ማንንም አያነጋገርም፤ ሚስት እና ታላቅ ልጁን ጭምር" በማለት ጽፈዋል።

የአእምሮ ጤና ባለሙያ ያልሆኑት የእርዳታ ሠራተኛ አክለውም፤ ላካንዋን "ለአንድ ወይም ሁለት ሳምንታት የሚቆይ የአእምሮ መቃወስ አጋጣሚዎች" ማሳለፉን እንዲሁም በዚህ ወቅት "የቤተሰቡን መኪና ይዞ" እንደሚጠፋ ገልጸዋል። ሁኔታውን "ለማስተካከል" የሚሞክርባቸው ጊዜያት እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ያነጋገረው የላካንዋን የልጅነት ጓደኛም በተመሳሳይ፤ በአፍጋኒስታን በወታደራዊው ክፍል ከነበረው ሥራ በኋላ የአእምሮ ጤና እክሎች እንደነበሩበት ገልጿል።

ላካንዋን ሲሠራ የነበረው 'ዚሮ ዩኒት' በተሰኘው ከሲአይኤ ጋር የሚሠራ የአፍጋኒስታን የስለላ እና ወታደራዊ ክፍል ውስጥ እንደበር አንድ የቀድሞ አፍጋኒስታን መከላከያ እና ደኅንነት አባል ለሲቢኤስ ተናግሯል። የሲአይኤ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍም ግለሰቡ ከአሜሪካው ስለላ መሥሪያ ቤት ጋር መሥራቱን አረጋግጠዋል።

ከዋሽንግተን ዲሲው ጥቃት ከቀናት በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁሉም "የሦስተኛ ዓለም አገራት" የሚነሳ "ስደትን በቋሚነት ለማቆም" ዝተዋል።

ሁሉም የስደተኝነት ጥያቄ አቅራቢዎች "በመጨረሻ ደረጃ እስከሚመረመሩ" ድረስ ለጥገኝነት ማመልከቻዎች ውሳኔ እንዳይሰጥ ተደርጓል።

አፍጋኒስታናዊው ላካንዋል በክስተቱ በደረሰበት ጉዳት አሁንም ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ላይ ሲሆን የነፍስ ማጥፋስ ክስ ይጠብቀዋል።