ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት በተከታታይ የአየር ጥቃቶች እና በቻይና ድጋፍ ከተሞችን ከታጣቂዎች አስለቀቀ
በቻይና የሚታገዘው የምያንማር ወታደራዊ መንግሥት ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም በታጣቂዎች የተያዙ አከባቢዎችን መልሶ ተቆጣጠረ።
ወታደራዊው መንግሥት መልሶ ከተቆጣጠራቸው አካበቢዎች መካከል ኬያክሜ የተሰኘው ከተማ ይገኝበታል። ባለፈው ዓመት ታጣቂዎች በምያንማርን እና ቻይና ድንበር ዋና የንግድ መስመር የሆነችውን ኬያክሜን የተቆጣጠሩት ወራትን ከፈጀ ከባድ ውጊያ በኋላ ነበር።
'ታንግ ናሽናል ሊብሬሽን አርሚ' የተባለው አማጺ ከተማዋን መቆጣጠሩ በተቃዋሚዎች ዘንድ እንደ ወሳኝ ድል ተቆጥሮ ነበር።
ይህ ድል በአውሮፓውያኑ 2021 በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው ወታደራዊ ኃይል አቅም እየተዳከመ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዶ ነበር።
ወታደራዊው መንግሥት በዚህ ወር ከተማውን መልሶ ለመቆጣጠር የፈጀበትን የሦስት ሳምንታትን ጊዜ ብቻ ነው።
ኬያክሜ ከተማ ከታጣቂዎች እጅ መውጣቱ፤ በአገሪቱ በሚካሄደው ግጭት የኃይል ሚዛኑ ወደ ወታደራዊው መንግሥት ማጋደሉን የሚያሳይ ሆኗል።
ወታደራዊው መንግሥት በታጣቂዎች ተይዞ በነበረው ክያክሜ ላይ በየዕለቱ ሲፈጽማቸው የነበሩ የአየር ድብደባዎች ከተማውን ሜዳ አድርጎታል።
የአገሪቱ አየር ኃይል ጄቶች ከ220 ኪሎ ግራም በላይ የሚሆን ቦንብ የጣለ ሲሆን ከባድ መሣሪያዎች እና ድሮኖችም ከከተማው ውጪ ያሉ የታጣቂዎች ይዞታዎችን ደብድበዋል።
አብዛኛው ነዋሪ ከተማውን ለቅቀው ወጥተው የነበረ ቢሆንም ሠራዊቱ መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ ተመልሰዋል።
የአማጺው 'ታንግ ናሽናል ሊብሬሽን አርሚ' ቃል አቀባይ የሆኑት ታር ፓርን ላ፤ በኬያክሜ እና ሲፓው ከተሞች "በየቀኑ ከባድ ውጊያ" እየተካሄደ መሆኑን በዚህ ወር መጀመሪያ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። "ጦሩ በዚህ ዓመት በርካታ ወታደሮች፣ በርካታ ከባድ መሣሪያዎች እና በርካታ የአየር ኃይል አለው። ሲፓውን ለመከላከል የተቻለንን እየሞከረን ነው" ብለው ነበር።
ቃለ አቀባዩ ይህንን ከተናገሩ በኋላ ግን የአገሪቱ ጦር ባለፈው ዓመት በታጣቂው እጅ የገባውን ሲፓውን በመያዝ ወደ ቻይና ድንበር የሚያመራውን መቆጣጠር ችሏል።
ወታደራዊው መንግሥት ይህንን ድል ለመቀናጀቱ በዋነኛነት ሚጠቀሰው የቻይና ድጋፍ ነው። ቻይና ይህንን እገዛ ያደረገችው ወታደራዊው መንግሥት በመጪው ታኅሣሥ ወር ምርጫ ለማካሄድ የያዘውን ዕቅድ በመደገፍ ነው።
ለማካሄድ የታሰበው ምርጫ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት አንግ ሳን ሱ ቺ ፓርቲ የሆነውን 'ናሽናል ሊግ ፎር ዴሞክራሲ' ን በማግለሉ የተነሳ እንዲሁም አገሪቱ እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በመሆኗ ሰፊ ተቃውሞ ተሰንዝሮበታል።
አገሪቱ ጦር በበኩሉ ከእጁ ከወጡት ግዛቶች ውስጥ የተቻለውን ያህል በማስመለስ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ምርጫ የመካሄዱን ጉዳይ ለማረጋገጥ እየሞከረ ነው።
ወታደራዊ መንግሥት በዚህ ዓመት ባደረጋቸው ውጊያዎች ስኬታማ መሆን የቻለው ከዚህ ቀደም ከነበሩ ውድቀቶቹ በመማሩ እንዲሁም አዲስ እና ገዳይ ቴክሎኖጂዎችን በመታጠቁ ነው።
በተለይም ከቻይና የገዛቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ውድ ያልሆኑ ድሮኖች በአማጺው ኃይል ላይ የበላይነት እንዲወስድ አስችለውታል። ቻይና የድሮኖቹን አጠቃቀም በተመለከተም ለጦሩ ሥልጠና ሰጥታለች።
በተጨማሪም ጦሩ ለማብረር ቀላል የሆኑ በሞተር የሚሰሩ ፓራግላይደሮችን በትክልል ዒላማዎች ላይ ቦንብ ለመጣል ተጠቅሞባቸዋል። ከቻይና እና ሩሲያ የቀረቡለትን የጦር አውሮፕላኖች በመጠቀምም ተከታታይ ድብደባዎችን ፈጽሟል።
ይህም በዚህ ዓመቱ ውጊያ ንጹኃን ላይ የደረሰው ጉዳት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጓል። በዚህ ዓመት ቢያንስ አንድ ሺህ ሰዎች እንደተገደሉ የሚገመት ቢሆንም ትክክለኛው ቁጥር ከዚህም ሊጨምር ይችላል።
አራተኛ ዓመቱን በያዘው የምያንማር የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፤ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።