በቀይ ባህር የቱሪስት ሰርጓጅ መርከብ በመስጠሟ የስድስት ሩሲያውያን ህይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, David McArthur MBE/Reuters
በግብጿ ከተማ ሁርጋዳ አቅራቢያ በቀይ ባህር አንድ የቱሪስት ሰርጓጅ መርከብ ሰጥሞ የስድስት ሩሲያውያን ቱሪስቶች ህይወት አለፈ።
ሐሙስ፣ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 4 ሰዓት ላይ ከሰጠመችው ሲንድባድ ከተሰኘችው መርከብ 39 ሰዎችን በህይወት መታደግ እንደተቻለ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ዘጠኝ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን ከነዚህ ደግሞ የአራቱ የከፋ ጉዳት ነው ተብሏል።
ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ህጻናት መሆናቸውን የሩሲያን ባለስልጣን ዋቢ አድርጎ የሩሲያ የዜና አገልግሎት ታስ ዘግቧል።
ባለስልጣናቱ አሁንም ምርመራ እያደረጉ ሲሆን መርከቧ የሰጠመችበት መንስዔ እስካሁን ድረስ አልታወቀም።
በቀይ ባህር ላይ የቱሪስት መርከብ ስትሰጥም ከቅርብ ወራት ወዲህ ይህ ሁለተኛው ነው።
በህዳር ወር ማርሳ አላም በተሰኘችው ስፍራ አቅራቢያ አንድ ጀልባ የመገልበጥ አደጋ የገጠማት ሲሆን በዚህም 11 ሰዎች ደብዛቸው እንደጠፋ ቀርቷል። ግለሰቦቹም እንደሞቱ ይታመናል።
ሲንድባድ ለተወሰኑ ዓመታት የቱሪስት ሰርጓጅ መርከብ ሆኖ አገልግሏል።
በሁርጋዳ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ያሉ የውሃ ስነ ምህዳሮችን (ኮራል ሪፍ) ማየት የሚፈልጉ ጎብኝዎችን እንደሚወስድ የሲንድባድ ሰርጓጅ መርከቦች አስታውቋል።
የቀይ ባህር አስተዳዳሪ አምር ሃናፊ በሰርጓጅ መርከቧ ተሳፍረው የነበሩ 45 መንገደኞች ከሩሲያ፣ ከኖርዌይ እና ከስዊድን አገራት የተውጣጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመርከቧ ውስጥ አምስት የግብጽ ሰራተኞችም ነበሩ። ሃናፊ እንደተናገሩት ስድስቱ ሟቾች ሁሉም ሩሲያውያን ቢሆኑም የተጎጂዎች ሙሉ ዝርዝር መረጃ እስካሁን አልተገለጸም።
ከሟቾቹ መካከል ሁለት ባለትዳር ዶክተሮች የሚገኙበት ሲሆን ሴት ልጆቻቸውም በሆስፒታል እንደሚገኙ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
በክስተቱ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ቢሆንም የሩሲያ አስጎብኚዎች ማህበር የባህር ሰርጓጅ መርከቡ በ20 ሜትር ጥልቀት ላይ እያለ በውሃ አካል በሚገኝ ቁጥቋጦ እና ድንጋይ ተመትቶ ግፊቱን ማጣቱ ተገልጿል። የሁርጋዳ ከተማ ከደቡብ ምስራቅ ካይሮ አጠገብ የምትገኝ ሲሆን ባሏት ውብ የባህር ዳርቻዎች እና የውሃ ላይ ስነ ምህዳር የቱሪስት መስህብ ናት።
የሲንድባድ ሰርጓጅ መርከብ በነዚህ ጉብኝቶች ተሳፋሪዎች በውሃ ውስጥ 25 ሜትር ጥልቀት እንዲገቡ እንደሚያስችላቸው ከድረገጹ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።
የዩናይትድ ኪንግደሟ ብሪስቶል ነዋሪ የሆኑት ዶ/ር ጀምስ አልድሪጅ ባለፈው የካቲት በባህር ሰርጓጅ መርከብ ተመሳሳይ ጉዞ አድርገዋል።
"ሰርጓጅ መርከቧ በጥሩ ሁኔታ የተያዘ እና በማስታወቂያ ፎቶዎቹ ላይ እንደሚታየው ነው" ብለዋል።
ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙላት፣ ወደ ውሃው ውስጥ አብሮዎት የሚገቡ ሁለት ጠላቂዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለሙያዎች አሉ ብለዋል።
የውሃውን ስነ ምህዳር ለ40 ደቂቃ ያህል የጎበኙት ዶክተሩ ስጋት እንዳልተሰማቸውም ለቢበሲ ተናግረዋል።












