የሱዳን ጦርነት ለእስላማዊ ታጣቂዎች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር የአሜሪካው ባለሥልጣን ተናገሩ

በሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የጽንፈኛ እስላማዊ እንቅስቃሴ ወደ አካባቢው የሚመለስበትን ሁኔታን ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አዲሱ በሱዳን የአሜሪካ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ ለቢቢሲ ተናገሩ።
መልዕክተኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደተለያዩ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በመጓዝ በሱዳን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሚያበቃበትን እና አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብበትን መንገድ ለመፈለግ በጉብኝት ላይ ናቸው።
ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁ የሚባል የመፈናቀል ቀውስ እና ረሃብን መጋረጡን የእርዳታ ሠራተኞች እያስጠነቀቁ ነው።
በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የሚካሄደው ጦርነት አገሪቱን በአንጃዎች መካከል በሚደረግ ግጭት መንግሥት አልባ ከማድረግ ባሻገር ለእስላማዊ ታጣቂዎች መፈልፈያ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል ቶም ፔሪዬሎ።
መልዕክተኛው ጨምረውም ለዚህ እንደማሳያ በሱዳን ሠራዊት ውስጥ እስላማዊ ጽንፈኞች ቦታ እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በሱዳን ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ከተስፋፉ የሚያስከትሉት ስጋት የአጭር ጊዜ አለመሆኑንም ተናግረዋል።
“የሱዳን መንግሥት ከተንኮታኮተ እና የአንጃዎች ግጭት ከቀጠለ እስላማዊ ቡድኖች ወደ አካባቢው የመመለስ ዕድል ያገኛሉ” ያሉት ቶም ፔሪዬሎ “እያወራን ያለነው ለ10 እና 20 ዓመታት ስለሚቆይ ችግር ነው” በማለት ሁኔታው ዘላቂ ስጋትን የሚደቅን ነው ብለዋል።
በሱዳን ውስጥ የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ጥረት እያደረጉ ያሉት የአሜሪካው መልዕክተኛ አክለውም፣ ግጭቱን ለማስቆም ተፋላሚ ወገኖችን የሚደግፉ አገራትን ጨምሮ በአካባቢው አገራት በኩል ከፍተኛ ፖለቲካዊ ፍላጎት መመልከታቸውን ገልጸዋል።
“በገንቢ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ መልኩ በአፍራሽ ጎኑ በአካባቢው ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች እንዲጫር ድጋፍ ያደረጉለት እሳት እራሳቸውንም ጭምር እንደሚያቃጥል እየተገነዘቡ ነው” ብለዋል ቶም ፔሪዬሎ።
የአሜሪካው መልዕክተኛ አካባቢውን የሚጎበኙት ባላንጣቸው ኢራን በጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ለሚመራው የሱዳን ሠራዊት የጦር መሳሪያዎችን እያቀረበች መሆኑን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ባለበት ጊዜ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሐሰት ነው ብላ ብታስተባብልም የተቀነቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት መሪ የጄኔራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ኃይሎችን እያስታጠቀች መሆኗ በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል።
በሚመጣው ሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ አንድ ዓመት የሚሆነው የሱዳን የእስር በርስ ጦርነትን ለማስቆም ዓላማ ይዘው በበርካታ አገራት ጉብኝት ለማድረግ የተነሱት የአሜሪካው መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ፣ ወደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጂቡቲ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ በማቅናት ውይይት እንደሚያደርጉ ተነግሯል።












