ሩሲያ “ዓለምን የመጨረሻው ጦርነት ውስጥ ከመክተቷ በፊት” ልትገታ ይገባል ሲሉ ዜሌንስኪ ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock
የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ “ዓለምን የመጨረሻው ጦርነት ውስጥ ከመክተቷ በፊት” ልትገታ ይገባል ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተናገሩ።
ኒው ዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ስሜት የተሞለበት ንግግር ያሰሙት ዜሌንስኪ ኒውክሌር የታጠቀችው ሞስኮው ዓለምን ወደ መጨረሻው ጦርነት ከመዝፈቋ በፊት ልትገታ ይገባል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሞስኮ “ክፋት ሊታመን አይችልም” ያሉ ሲሆን አገራት ተባብረው ሩሲያ ሃገራቸው ላይ እየፈፀመች ያለችውን ወረራ እንዲገቱም ጥሪ አቅርበዋል።
ሩሲያ ከምግብ እስከ የኃይል ምንጭ ድረስ ለጦርነት እየተጠቀመች ነው ሲሉም ወቅሰዋል።
ሩሲያ ዓለም ላይ ልታመጣ የምትችለው አደጋ ላይ ባተኮረው ንግግራቸው ሌሎች እንደ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ጉዳዮች ሊገቱ የሚችሉት ሞስኮ አደብ ስትገዛ ነው ብለዋል።
“ሩሲያ ዓለምን ወደ መጨረሻው ጦርነት እየወሰደች ነው፤ ዩክሬን ግን ከዚህ በኋላ ማንኛውም ሃገር ከየትኛው ወገን ወረራ እንዳይፈፀምበት ለማድረግ ትጥራለች” ሲሉ ለሃገራት መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
አክለው ሩሲያ “የኒውክሌር መሣሪያ የመታጠቅ ምንም ዓይነት መብት የላትም” ብለዋል።
“መሣሪያ የመታጠቅ አቅም ሊገደብ ይገባል፤ የጦርነት ወንጀሎች ቅጣት ሊያስከትሉ ይገባል፤ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው ሊመለሱ ይገባል፤ ወራሪዎች ደግሞ ወደመጡበት መሄድ አለባቸው።
“ይህ ለማድረግ መተባበር አለብን። ደግሞም እናደርገዋለን!” ብለዋል ዜሌንስኪ።
ፕሬዝደንቱ ሩሲያ ዩክራናዊያን ሕፃናት አፍና በመውሰድ “ዘር ማጠፋት” ፈፅማለች የሚል ወቀሳም አሰምተዋል።
ባለፈው መጋቢት ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት [አይሲሲ] የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናዊያን ሕፃናትን ወደ ሩሲያ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወስደዋል ሲል የእሥር ትዕዛዝ ማውጣቱ ይታወሳል።
ሞስኮው የዩክሬንን ወቀሳ በተደጋጋሚ አስተባብላለች። ነገር ግን በርካታ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ሩሲያ በዩክሬን የጦር ወንጀል ፈፅማለች ይላሉ።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ጨምረው ጦርነቱ እንዲቆም የሚደረጉና ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ “ድብስብስ ስምምነቶች” ሊቆሙ ይገባል ብለዋል።
ዜሌንስኪ የንግግራቸው አንኳር መልዕክት የነበረው የዩክሬን ጦርነት ጣጣ ለመላው ዓለም ሕዝብ ይተርፋል የሚል ነው።
ለወራት ሲብላላ የቆየው የሰላም ስምምነት ጥቅሙ ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለምም ጭምር ነው ይላሉ።
ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ከጦርነቱ በኋላ ከክሬምሊን ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክረዋል።
ምዕራባዊያን ሃገራት የተባበሩት መንግሥታት የእነዚህ ሃገራትን የዕድገት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጥያቄ እንዲመልስም እየወተወቱ ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ከሳቸው በፊት ንግግር ያሰሙት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ንግግር በጭብጨባ ሲያጅቡ ታይተዋል።
ባይደን በንግግራቸው የሩሲያ ወረራ ትሩፋት አሁንም ሊገታ አልቻለም የሚል ንግግር አስምተዋል።
“ሩሲያ፤ ዓለም ሁሉን ረስቶት ዩክሬን ላይ የምትፈፅመውን ግፍ ያለምንም እርምጃ ይተወዋል ብላ ታምናለች። ዩክሬን እንዲህ እንድትሆን ከፈቀድን የሌሎች ነፃ ሃገራት ዕጣ ፈንታስ የተጠበቀ ነውን?” ሲሉ ጠይቀዋል ባይደን።
በሌላ በኩል ለሩሲያ የጦር ድሮኖች በማቅረብ የምትወቀሰው የሞስኮ አጋር የሆነችው ኢራን ፕሬዝደንት ኢብራሒም ራይሲ ዋሺንግተን በዩክሬን ያለውን ጦርነት እያጋጋለች ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
“ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬን ያለውን ግጭት በማቀጣጠል የአውሮፓ ሃገራትን ማዳከም ትሻለች። የሚያሳዝነው ይህ የረዥም ጊዜ ዕቅዷ ነው” ሲሉ ኒው ዮርክ ለተሰበሰቡ መሪዎች ተናግረዋል።












