ባሎች በትምህርታቸው ለላቁ ሚስቶች ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለዘመናት በትምህርት፣ በሃብት የላቁ ወንዶች ካላቸው ደረጃ ዝቅ ካሉ ሴቶች በትዳር የሚጣመሩበት ባህል የዓለማችን ሥነ-ጽሑፎችን ወይም ፊልሞችን እሳቤ ቀርጾት ቆይቷል።
ለዚህም እንደ ሲንዴሬላ ያሉ ጥንታዊ ተረቶች ወይም የጄን ኦስቲን ድርሰት የሆነውን የ'ፕራይድ ኤንድ ፕሪጁዲስ' ሴቶችን መጥቀስ ይቻላል።
ሴቶች ከእነሱ በትምህርት፣ በዕወቀት፣ በገንዘብ የላቁ ወንዶችን መመኘትም ሆነ ማግባት ዋነኛው የአጋርነት ወይም የትዳር መስፈርት እንዲሆን አድርጎታል።
በተለያዩ ባህሎችም፣ እምነቶች እና እሳቤዎች ዘንድ ወንድ በትዳር ውስጥ የቤት መሪ፣ ራስ፣ ወይም አስተዳዳሪ እንዲሁም ሴቶች በቤት ሥራዎች ላይ ተወስነው እንደ ደጋፊ ሲታዩም ቆይተዋል።
ነገር ግን በርካታ ሴቶች በትምህርት የላቀ ደረጃ ላይ መድረሳቸው እንዲሁም የገንዘብ ነጻነት ሲያገኙ ይህ ባህላዊ የትዳር ግንኙነቶችን መቀየሩ አልቀረም።
"በአሁኑ ወቅት ከወንዶች በበለጠ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ሴቶች አሉ። በአሁኑ ጊዜ በወጣቶች መካከል አለመመጣጠን እያደገ መጥቷል" ይላሉ በኦስትሪያ የቪየና ዩኒቨርስቲ የሶሺዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ናዲያ ስቴይበር።
በዚህም ምክንያ ምንም እንኳን ሴቶች በትምህርት ደረጃ ወይም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ተመጣጣኝ ሁኔታ ላይ ያሉ አጋሮችን ቢፈልጉም ይህም አብዛኛውን ጊዜ ስለማይሳካ ከእነሱ በደረጃ ዝቅ ካሉ አጋሮች ጋር ሕይወት እንደሚመሠርቱ ምሁሯ ይገልጻሉ።
ይህም በትምህርት፣ በገንዘብ ከደረጃቸው ዝቅ ብለው የሚጣመሩበት ክስተት በማኅበራዊ ሳይንስ ዘንድ 'ሃይፖጋሚ' ተብሎ ይጠራል።

የፎቶው ባለመብት, Historical Picture Archive
'ሃይፖጋሚ' ምንድን ነው?
ሃይፖጋሚ የሚባለው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የትምህርት ደረጃ ዝቅ ካለ ሰው ጋር መጋባት ወይም የፍቅር ግንኙነትን መመሥረት የሚለውን ይገልጻል።
በተለምዶ ሴቶች በገንዘብ የሚያስተዳድሯቸው፣ በዕድሜ የሚበልጧቻው፣ በትምህርት የላቁ አጋሮችን እንዲፈልጉ ሲበረታቱ የቆዩ ሲሆን ይህም 'ሃይፐርጋሚ' ይሰኛል።
"ለዘመናት ሥራ እንዲይዙ በሚል ወንዶች የተሻለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ሲደረግ ሴቶች ደግሞ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከእናቶቻቸው ሲማሩ ቆይተዋል" ይላሉ በለንደን የሚገኘው ሲቪታስ የተሰኘው የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ካትሪን ሃኪም።
"በትዳር አጋሮች መካከል ያለው የዕድሜ እና የትምህርት ልዩነት አባታዊ ሥርዓት (ፓትሪያርኪ) እንዲያብብ አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለ የትምህርት እኩልነት የዘመናዊ ማኅበረሰብ መገለጫ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ሴቶች በትምህርት ደረጃቸው መላቅ
ሴቶች በትምህርት ደረጃ እየላቁ እንደሆነ እና ዓለማችን እየተቀየረች እንደሆነ እየወጡ ያሉ አሃዞች ያሳያሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት ፒው የተሰኘ የምርምር ማዕከል የሠራው ጥናት በአሜሪካ ውስጥ 24 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ከባለቤቶቻቸው በላቀ የትምህርት ደረጃ መማራቸውን ያሳያል።
ይኸው ጥናት 29 በመቶ የሚሆኑት ባለትዳሮች ተመሳሳይ ደመወዝ እንደሚከፈላቸው አሳይቷል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወንዶች አስተዳዳሪ ሲሆኑ፣ አስተዳዳሪ የሆኑ ሴቶች 16 በመቶ ብቻ ናቸው።
ሆኖም በተለይም ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ከባሎቻቸው እኩል ወይም ከዚያ በላይ የሚከፈላቸው የሴቶች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል።
እነዚህ ለውጦች ለረጅም ዘመናት የቆዩ የሥርዓተ ፆታ ባህሎችን እና ደንቦችን የሚገዳደሩ ሆነዋል። በበርካታ ሁኔታዎች የትዳር ሚናዎችን የቀየሩ በመሆናቸው አለመግባባቶችን የሚፈጥሩ እና የግጭቶችም መነሻ መሆናቸው እየታየ ነው።
"አንዳንድ ሴቶች ከእነሱ በማኅበራዊ -ኢኮኖሚያዊ ተመሳሳይ ደረጃ ያሉ አጋሮች በመፈለግ ቢቀጥሉበትም በርካታ ሴቶች ግን በስሜት መጣጣምን፣ የጋራ እሴቶችን እና መከባበርን በማስቀደም" ከተለመዱት ባህላዊ ሁኔታዎች እያፈነገጡ መሆናቸውን ኢግናይት ዴቲንግ የተሰኘ የትዳር አገናኝ ሚሼል ቤጊ ይናገራሉ።
በአውሮፓ እና በሰሜን አሜሪካ በትምህርት ደረጃ የትዳር አጋሮች እኩል መሆን በጣም የተለመደ መሆኑን ካትሪን ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዓለም አቀፍ ሁነቶች
በትምህርትም ሆነ በክፍያ የላቁ ሴቶች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው በፍቅር መጣመር በምዕራባውያን ማኅበረሰቦች ዘንድ የበለጠ የተለመደ ቢሆንም፤ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች አሁንም ወንዶች በትዳር አስተዳዳሪነታቸው እንደቀጠሉ ነው።
"የሂንዱ ቅዱሳን መጻሕፍት ጋብቻን በተመሳሳይ መደብ (ካስት) መካከል እንዲሆን ያዝዛል። ሆኖም ወንድ ከእሱ ዝቅ ካለ መደብ (ካስት) ቢያገባ የሚፈቅድ ቢሆንም፤ አንድ ወንድ ከእሱ ከፍ ካለች መደብ ጋር መጋባትን ይከለክላል" ይላሉ በአሜሪካ የሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ሶናልዴ ዴሳይ።
በሕንድ አሁንም ቢሆን ወላጆች በሚመርጡት እና "ልጅህን ለልጄ" በሚል በመልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ጋብቻ የበላይነቱን እንደያዘ ነው።
ዘመናዊ መልክ ይዘው በጋዜጣ በሚወጡ የጋብቻ ማስታወቂያዎች ላይ ሙሽራው በዕድሜ ተለቅ ያለ፣ ረጅም እና ቢያንስ እንደ ሙሽሪት የተማረ ወይም ከዚያ በላይ እንዲሆን የሚጠይቁ ናቸው።
ይሁን እንጂ "ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሴቶች ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ወንዶች የሚያገቡበት ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል" ይላሉ።
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉ አገራት ከፍተኛ ሴት የዩኒቨርስቲ ምሩቃን አሏት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሆኖም በርካታ በርካታ ወላጆች ወንዶች አስተዳዳሪ እንዲሆኑ በመፈለጋቸው እነዚህ አባታዊ (ፓትሪያርካል) እሴቶች እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል።
በዚህም የተነሳ በትምህርታቸው የላቁ ሴቶች "ተቀባይነት" ያለው የትዳር አጋር ለማግኘት እየታገሉ ይገኛሉ።
ሆኖም አዲሱ የሴቶች ትውልድ እነዚህን ባህላዊ ሚናዎች በመገዳደር ራስን መቻል እና ለትምህርት ቅድሚያ በመስጠት በዘመናዊ ኢራን ውስጥ ለትዳር አጋርነት አዲስ ትርጓሜ ለመስጠት እየጣሩ ይገኛሉ።
በቻይና "ሸንግ ኑ" (ትራፊ ሴቶች) የሚለው አጸያፊ ቃል በ20ዎቹ መጨረሻ እና በ30ዎቹ ላሉ በትምህርት ለላቁ እና ላላገቡ ሴቶች የሚሰጥ ስያሜ ነው።
በጃፓን ባህል በሴቶች ላይ በሚጫነው የሥርዓተ ፆታ ሚና እንዲሁም በኢኮኖሚ ራሳቸውን የቻሉ በመሆናቸው ምክንያት በዕድሜ ዘግይተው ያገባሉ ወይም ማግባት እያቆሙ ነው።
በሌላ በኩል እንደ ኖርዌይ እና ስዊድን ያሉ አገራት የተለየ ምሥልን ይሰጣሉ።
ጠንካራ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ፖሊሲዎች፣ ረዘም ያለ የወላጅ ፈቃድ፣ በሥራ ኃይል ላይ ከፍተኛ የሴቶች ቁጥር ተሳትፎ መኖሩ በእኩልነት ላይ የተመሠረቱ የትዳር አጋርነት በዋናነት እንዲኖር ምክንያት ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ
ምንም እንኳን ወንዶች የበላይ የሚሆኑበት ትዳር እየቀረ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ሃብታም ወይም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የትዳር አጋርን ማግኘት ይቻላል በሚል ለሴቶች ምክር የሚሰጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
በተጨማሪም ባህላዊ የትዳር ሚናን የሚቀበሉ ሴቶችን ለማግኘት ምዕራባውያን ወንዶች ወደ ተለያዩ አገሮች እየተጓዙ ይገኛሉ።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ታዋቂነትን ያገኙ ሲሆን፣ እነዚህም 'ፓስፖርት ብሮስ' ተብለው ይጠራሉ። በተጨማሪ ሴቶች ባህላዊ ሚናዎችን እንዲቀበሉ የሚያበረታቱ ተጽእኖ ፈጣሪዎችም እንደገና እያንሰራሩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, PeopleImages
ከፍተኛ ገንዘብ የሚያገኙ ሚስቶች
ሴቶች ከደረጃቸው ዝቅ ብለው በፍቅርም ሆነ በትዳር አጋርነት በሚጣመሩበት ወቅት በወንዶች ላይ ውጥረት እንደሚፈጥር ናዲያ ስቴይበር ያስረዳሉ።
ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚያነሱት "ወንድነት የሚለውን የተለመደውን ጽንሰ ሃሳብ ስለሚገዳደር ነው" ይላሉ።
"ጉዳዩ ሴቶች ከደረጃቸው ዝቅ ያሉ የትዳር አጋሮችን መቀበል ላይ አይደለም። ከዚህ ባለፈ ወንዶች ከእነሱ በበለጠ የተማረች ወይም የተሳካላት የትዳር ጓደኛን በአጋርነት ለመቀበል ይችላሉ" የሚለው ነው ይላሉ።
ሴቶች በትምህርት ደረጃቸው በላቁ ቁጥር የማኅበረሰባዊ መዋቅሮች ባህላዊ የሥርዓተ ፆታ ሚናዎችን ለማስጠበቅ ዘዴዎችን እንደሚቀይሱ አንዳንድ ሶሺዮሎጂስቶች ይናገራሉ።
ለምሳሌም የሚያነሷቸው ያህል ለተመሳሳይ ሥራ ለሴቶች ያነሰ ክፍያ መስጠት፣ ወይም ሥራ እና እናትነትን ለማስኬድ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመፍጠር የወንዶችን ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ማስጠበቅ የሚጠቅሷቸው ናቸው።















