የአዶለሰንስ ተከታታይ ድራማ ተዋናይ ኦውን ኩፐር በእድሜ ትንሹ የኤሚ አሸናፊ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብሪታንያዊው ተዋናይ ኦውን ኩፐር የኤሚን ሽልማት በ15 ዓመቱ በማሸነፍ የመጀመርያው በዕድሜ ትንሹ ወንድ ተዋናይ ሆኗል።
በኔትፍሊክስ ላይ የሚታየው እና ውስን ክፍሎች ያሉት አዶለሰንስ ተከታታይ ድራማ ላይ ረዳት ተዋናይ በመሆን የተሳተፈው የ15 ዓመቱ ኩፐር የክፍል ጓደኛውን በመግደል የተወነጀለ ታዳጊን ወክሎ ነው የተወነው።
አራት ተከታታይ ክፍሎች ብቻ ያሉት ድራማው በምርጥ ተከታታይ ድራማ፣ በዝግጅት፣ በድርሰት ጽሑፍ፣ እንዲሁም በድራማው ላይ በትወና የተሳተፉት ስቴፈን ግራሃም እና ኢሪን ዶሄርቲ አሸናፊ ሆነዋል።
ኩፐር ሽልማቱን ሲቀበል ባደረገው ንግግር "እዚህ መቆም በራሱ አስደናቂ ነገር ነው፤ የድራማ ትምህርት ከሁለት ዓመት በፊት ስጀምር፣ አይደለም እዚህ መድረክ ላይ መቆም አሜሪካ እመጣለሁ ብዬ እንኳን አላሰብኩም" ብሏል።
ኩፐር "ዛሬ ምሽት ያረጋገጥኩት ካዳመጥን እና ትኩረታችንን ከሰበሰብን እና ከምቾታችን ቅጥር መውጣት ከቻልን ማንኛውም ነገር በሕይወት ማሳካት እንደሚቻል ነው፤ ኃፍረት ቢሰማህ ማን ግድ ይሰጠዋል? የማይቻል ነገር የለም። ከሦስት ዓመት በፊት ማንም ነበርኩ። አሁን ግን እዚህ ነኝ።"
ቤተሰቦቹን፣ አብረውት የተወኑትን፥ እንዲሁም የድራማውን ፕሮዳክሽን አባላት ያመሰገነው ኩፐር፣ አክሎም "ስሜ በዚህ ሽልማት ላይ ተጽፎ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ይህ በትክክል የሚገባው ከካሜራ ጀርባ ላሉ ሰዎች ነው" ብሏል።
ኩፐር እአአ በ1973 'ዛት ሰርቴን ሰመር' ላይ በመተወን ያሸነፈውን የ16 ዓመቱን ስኮት ጃኮቢ ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
በሴቶች ዘርፍ አሁንም ክብረወሰኑ የተያዘው በሮክሳና ዛል ሲሆን 'ሳምቲንግ አባውት አሚሊያ' የተሰኘው ድረማ ላይ በመተወን ስታሸንፍ 14 ዓመቷ ነበር።
አዶለሰንስ በተመልካቾች፣ በባለሙያዎች እና በሂስ አቅራቢዎች ዘንድ በታዳጊዎች ላይ ስማርት ስልኮች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ያላቸውን ተጽዕኖ ማሳየት በመቻሉ አድናቆትን አግኝቷል።
ግርሃም በመሪ ተዋናይነት ሽልማቱን ሲቀበል "በሌላ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር ለእንደኔ ዓይነት ልጅ አይሆንም ነበር። ኪርቢ በምትባል አካባቢ የምኖር ከሁለት ዝርያዎች የተገኘሁ ልጅ ነኝ" ብሏል።
"ስለዚህ ዛሬ ከእኩዮቼ ፊት እዚህ መገኘቴ እና በእናንተ እውቅና ማግኘቴ በሕይወቴ ከማስበው ምርጥ ጊዜዎች መካከል አንዱ ነው። እናም ለእናንተ ደግሞ ማንኛውም ሕልም እንደሚቻል ያሳያችኋል።"
የታዳጊዎች የሥነ ልቡና ባለሙያ በመሆን የተወነችው ዶሃርቲ ደግሞ በረዳት ተዋናይ ዘርፍ አሸናፊ ሆናለች።
ብሪታንያዊቷ ተዋናይ "ኦውን ኩፐርን እና አዶለሰንስን በቀሪው ሕይወቴ ሁሉ ስዘክር እኖራለሁ" ስትል ቀልዳለች።
"ይህንን ድራማ በመስራት ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ መጥራት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የቡድን ጥረት ማሳያ ነው" ብላለች።
ግርሃም በምርጥ የድራማ ጽሑፍ ሽልማቱን ሲቀበል "ይህች የሠራናት ትንሽ ሥራ ይህንን ያህል ተጽዕኖ ይኖራታል ብለን አላሰብንም ነበር፤ ነገር ግን ያንን በመፍጠሩ በጣም ደስተኞች ነን" ብሏል።
አብሮት ድራማውን የጻፈው ጃክ ትሮን ሽልማቱን በድራማው ላይ ለተሳተፉ ታዳጊ ተዋንያን መታሰቢያ እንዲሆን አድርጎ "እናንተ ወጣቶች ጥሩ መሆን እንደሚችሉ ያሳያችሁ ነበልባል ናችሁ" ብሏቸዋል።















