ፈረንሳይ በሳህል ቀጠና ስታካሂድ የቆየችው ወታደራዊ ዘመቻ ማብቃቱን በይፋ ልታውጅ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸው ላለፉት ስምንት ዓመታት በሳህል አገራት ስታካሂደው የቆየችው የፀረ-ጂሃዲስቶች ዘመቻ ማብቃቱን በይፋ ይናገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንቱ ዛሬ የፈረንሳይ የወደብ ከተማ በሆነችው ቶውሎን በሚያደርጉት ንግግር ላይ ላለፉት ዘጠኝ ወራት እንቅስቃሴው የተገታው የ'ባርክሄን ኦፕሬሸን' ይፋዊ መቋጫው እንደሚሆን ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመጨረሻዎቹ የፈረንሳይ ወታደሮች ከወራት በፊት ከማሊ ጋዎ ከተማ ከሦስት ወራት በፊት ወጥተዋል።
የማክሮን ኤሊዚዜ ቤተ-መንግሥት እንዳለው ከሆነ ፈረንሳይ በአፍሪካ የሚኖራትን ወታደራዊ ኦፕሬሽን የምታስተዳድርበት አዲስ ዕቅድ ይፋ ማድረግ ይፈልጋሉ።
በ'ኦፕሬሽን ባርክሄን' እስከ 5500 የፈረንሳይ ወታደሮች ተሳትፈው ነበር። እአአ 2013 ይፋ የተደረገው ይህ ዘመቻ በዋናነት በማሊ ጂሃዲስቶችን ለመዋጋት በሚል የተመሠረተ ሲሆን፣ በጥምረቱ ውስጥ ደግሞ ኒጀር፣ ቻድ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ሞሪታኒያ ተካተውበታል።
በቀጠናው ከአል ቃይዳ እና ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገሩ ቡድኖች መስፋፋት እና የሟች የፈረንሳይ ወታደሮች ቁጥር ማሻቀብ በፓሪስ ያሉ ወታደራዊ አመራሮች ዘመቻው ውጤታማነት ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗል።
በስምንት ዓመታት ውስጥ 58 ወታደሮች መሞታቸው እንደ ትልቅ ጉዳት ተቆጥሯል በፈረንሳይ ዘንድ።
ከዚህ በተጨማሪም የፈረንሳይ ጦር የተሰማራባቸው አገራት ዜጎች በጦሩ አባላት ላይ ያላቸው ጥላቻ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጦሩን በተመለከተ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች በቀጠናው የሚደረግ ኦፕሬሽንን አደገኛ አድርጎታል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በማሊ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ አዲሶቹ የማሊ የጦር አበጋዞች፣ ፈረሳይን በጣልቃ ገብነት ወንጅለው ፊታቸውን ዋግነር ወደ ተሰኘው የሩሲያ ቅጠረኛ ቡድን አዙረዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ዛሬ በሚያደርጉት ንግግራቸው ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከአካባቢው ታስወጣ እንጂ በቀጠናው ያለውን የአክራሪ እስላማዊ ቡድን በተለየ ቅርጽ መዋጋቷን ትቀጥላለች እንደሚሉ ይጠበቃል።
ቁጥራቸው ወደ 3ሺህ የሚጠጉ የፈረንሳይ ወታደሮች በኒጀር፣ በቻድ እና በቡርኪና ፋሶ ይቆያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን ወታደሮቹ ለብቻቸው እንቅስቃሴያቸውን ማደረግ በማቆም ከየአገራቱ ብሔራዊ ሠራዊት ጋር በመጣመር ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ፈረንሳይ የ'ባርክሄን ኦፕሬሽን' ያለመሳካት ከማመን ውጪ አማራጭ እንደሌላት ይናገራሉ።
ይህ በተለይም በማሊ የወታደራዊ ጁንታው መፈንቅለ መንግሥት ካካሄደ እና ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ግንኙነት ካቋረጠ በኋላ ግልጽ መሆኑን ይናገራሉ።












