በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደው ተቃውሞ እና መንገድ መዝጋት ቀጥሏል

የፎቶው ባለመብት, SM
የትግራይ ኃይሎች ተብለው የሚታወቁት የሠራዊት አባላት በክልሉ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚያሰሙት ተቃውሞ እና መንገድ መዝጋት መቀጠሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሰኞ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም. በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ የጀመረው ተቃውሞ ወደ ተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ማክሰኞ፣ ረቡዕ እና ሐሙስ መቀጠሉን ተገልጿል።
ዛሬ [ሐሙስ] በአዲግራት እና በአካባቢው ተቃውሞ መቀስቀሱን እና ከአዲግራት ወደ መቀለ የሚወስደው ዋና መንገድ በተቃዋሚዎች መዘጋቱን ቢቢሲ አረጋግጧል።
በተጨማሪም በአሁላ እና በመኾኒ ምሥራቃዊ እና ደቡባዊ ዞኖችን ከመቀለ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች እንዲሁም ከእንዳአባጉና ወደ እነዳ ሽረ እንዳሥላሴ የሚወስደው መንገድም ዛሬም ተዘግተው እንደሚገኙ የተለያዩ ምንጮች አመልክተዋል።
የትግራይ ኃይሎች አካል የሆነው የአርሚ 22 አባላት ከአራት ቀናት በፊት በመቀለ ከተማ ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት መንገድ በመዝጋት እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉለው ነበር።
በመቀለ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎበት ቢቆምም በተከታታይ በነበሩት ቀናት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የቀጠለ ሲሆን፣ ሐሙስም [ዛሬ] መቀጠሉ እየተነገረ ነው።
ማክሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2018 ዓ.ም. በማዕከላዊ ዞን ነበለት በተባለው አካባቢ ተቃውሞ የነበረ ሲሆን በዚህም ወደ ሐውዜን እና አድዋ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተው ነበር።
ከአካባቢው ለቢቢሲ ትግርኛ የተላኩት ምሥሎች እንደሚያሳዩት በነብለት የሚገኘው የአውቶቡስ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ሳይችል ቀርቷል።
በተመሳሳይ ከውቅሮ ወደ መቀለ በሚወስደው መንገድ በአጉላዕ ከተማ መንገድ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፡ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች ማለፍ ሳይችሉ መቅረታቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የትግራይ ኃይል አባላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል።
በደቡብ ትግራይ ዞን መኾኒ እና ዓዲሽሁ ወደ መቀለ የሚወስዱ መንገዶችም ተዘግተዋል።
የእንዳባጉና፣ ሽረ፣ ማይፀብሪ መንገድ ተዘግቶ የነበረ ቢሆንም የተከፈተው የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
የወታደራዊ ኃይሉ አባላት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ደሞዛቸው በወቅቱ እየተከፈላቸው እንዳልሆነ፣ ጥቅማ ጥቅም እየተሰጣቸው ባለመሆኑ፣ ወደ የአካባቢው አስተዳደር ሲሄዱም ጉዳያቸው ሰሚ አለማግኘቱ እንዲሁም እንደ ታጋይ እንደማይከበሩ በመግለፅ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
እንዲሁም ደግሞ ከደሞዝ እና ከጥቅማ ጥቅም ውጪ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ድምፃቸውን አሰምተዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ለተቃውሞ የወጡት የፀጥታ ኃይል አባላት 'የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጠባቂ አይደልንም'፡ 'ጦርነት አንፈልግም' እና 'ሰላም እንሻለን' የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ታይተዋል።
ሰኞ ዕለት በመቀለ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የትግራይ ኃይሎች አባላት፣ ወደ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽ/ቤት በመሄድ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ለማነጋገር ጠይቀው ነበር።
ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ በወቅቱ በቢሯቸው ስላልነበሩ ወደ ሰማዕታት ሃውልት አዳራሽ ገብተው የሚመለከታቸው ኃላፊዎች እስኪመጡ እንዲጠብቁ ቢነገራቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ይህን ተከትሎም ከመቀለ የሚወጡ ሦስት ወሳኝ መንገዶችን በመዝጋታቸው ወደ ከተማዋ አውሮፕላን ማረፊያው እና ወደ ሌሎች የክልሉ ክፍል የሚያቀኑ ተሽከርካሪዎች እና መንገደኞች ተስተጓጉለው ውለዋል።
ሰኞ ዕለት ማምሻውን ከትግራይ ጊዜዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት፣ ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከወታደራዊ አመራሮች ጋር በሰማዕታት አዳራሽ የተነጋገሩ ሲሆን ጥያቄያቸውን በዝርዝር አቅርበዋል።

የፎቶው ባለመብት, SM
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተቃዋሚዎች የሁለት ዓመት ደሞዝ አለመከፈሉን እንዲሁም ቃል የተገባላቸው ጥቅማ ጥቅም አለመከበሩን በመግለጽ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ ባለፈም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ ጥያቄዎቹ በመላው ትግራይ ያሉ የትግራይ ኃይሎች አባላት ቅሬታ መሆኑን ይናገራሉ።
ተቃውሟቸውን ያሰሙት የትግራይ ኃይል አባላት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የቀድሞው የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት የነበሩ እና የትግራይ ኃይልን የተቀላቀሉ ናቸው።
እነዚህ የትግራይ ኃይል አባላት በቀድሞው የደመወዝ ክፍያ ዝርዝር ውስጥ ስለነበሩ ደመወዛቸው እየተቆራረጠም ቢሆን መቀጠሉን ይናገራሉ።
ነገር ግን በጦርነቱ ወቅት ኃይሉን የተቀላቀሉ አዳዲስ አባላት የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም እያገኙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ለዚህም "ልክ እንደሌሎቹ አባላት ድጎማ ይሰጠን፤ አድልዎ አይፈጠር፤ የ2013 እና 2014 ዓ.ም. ክፍያ ይሰጠን" በማለት ጠይቀዋል።
አባላቱ ያነሷቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሁለት ዓመቱ ክፍያ ተጣርቶ እልባት እንደሚያገኝ ቃል ገብተውላቸው ነበር።
መቀለ ውስጥ ሰኞ ዕለት ከሰልፈኞቹ ተወካዮች ጋር በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ ከዚህ በፊት ጸድቆ የነበረው ለሠራዊቱ አባላት የሚሰጠው የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ ነው።
በዚህም ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚሆን ቦታ መስጠት ተጀምሮ በአንደኛው ዙር ለሰማዕታት ቤተሰቦች በመመደብ ላይ እንደሚገኝ እና ቀጥሎም በጦርነት ለተጎዱ ሰዎች ከዚያ በማስከተልም ለአርበኞች እንደሚሰጥ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል።
ለታጋዮች የሚሰጠው መሬት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተቃውሟቸውን ላሰሙት አባላት ተገልጿል።
ሌሎች ጥያቄዎቻቸው ደረጃ በደረጃ እንደሚመለሱም ተነግሯቸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በረቡዕ ዕለት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ፣ የአስተዳደሩ ካቢኔ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቀደም ሲል ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሊተገበር በዕቅድ ላይ የነበረው እና የትግራይ ኃይል አባላትን አስመልከቶ የወጣ መመሪያ ተገቢ ደሞዝ፣ ጥቅማ ጥቅም እና ለቤት መሥሪያ የሚሆን ቦታ እንዲሰጥ የሚያስችል ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ ውሳኔ መሠረት መመሪያው ለተለያዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቢሮዎች እንዲሠራጭ እና እንዲተገበር መታዘዙን መግለጫው ያመለክታል።
ደም አፋሳሽ የነበረውን የትግራይ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የትግራይ ኃይል አባላት ትጥቀቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲቀላቀሉ ይጠበቃል።















