ፖሊስ በሞስኮ በሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ የምሽት ክበቦች ላይ ዘመቻ አካሄደ

የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በቅርቡ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንቀስቃሴን ሕገወጥ በማለት የፈረጀችው ሩሲያ በሞስኮ በሚገኙ የተመሳሳይ ጾታ የምሽት ክበቦች (ክለቦች) ላይ ዘመቻ ማካሄዷ ተዘግቧል።

ፖሊስ በርካታ የተመሳሳይ ጾታ ክለቦችን ጥሶ በመግባት የተወሰኑትን ታዳሚዎች አጠር ላለ ጊዜ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስቶሮዥኖ ኖቮስቲ የተሰኘው የቴሌግራም ገጽ ዘግቧል።

በተጨማሪም የአንዳንዶች ፖስፖርት ተወስዶ ፎቶ እንዲነሳ ተደርጓል ተብሏል።

በክለቡ ተገኝቶ የነበረ አንድ ግለሰብ ረዘም ላለ ጊዜ እታሰራለሁ የሚል ፍራቻ እንዳደረበትም ለኖቮስቲ ተናግሯል።

ፖሊስ በበኩሉ በእነዚህ የምሽት ክበቦች ላይ ዘመቻ ያካሄደው አደንዛዥ እፅ ለመፈለግ መሆኑንም ኖቮስቲ ነግረውኛል ብሏል።የከተማዋ ባለስልጣናት እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም።

“ድንገት መሐል ላይ ሙዚቃው ቆመ እና ፖሊሶች ወደ ክለቦቹ መግባት ጀመሩ” ሲልም አንድ የዓይን እማኝ ተናግሯል።

ሶታ የተሰኘው ሌላ የቴሌግራም ቻናል አርብ አመሻሽ ላይ ሦስት የምሽት ክበቦች በፖሊስ ወረራ እንደተፈጸመባቸው ገልጿል።

ፖሊሶች እና የፖሊስ መኪኖች ከአንድ የምሽት ክበብ ውጭ ተሰባስበው የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ተጋርተዋል።

የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የአደባባይ እንቅስቃሴ ጽንፈኛ ድርጅት ነው በማለት በቅርቡ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች አግዷል።

ይህ እግድ የተላለፈው የፍትህ ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ቢሆንም በሩሲያ በሕጋዊነት የተመዘገበ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ድርጅት የለም።

በሩሲያ የተመሳሳይ ጾታ ጥምረት እውቅና የለውም። በሩሲያ ትዳር ማለት የወንድ እና የሴት ጥምረት ማለት ስለመሆኑ ትርጉም ለመስጠት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከሦስት ዓመታት በፊት ተቀይሮ ነበር።

በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2013 ላይ ሩሲያ “ከተለመደው ውጪ ያለ ጾታዊ ግንኙነት ላይ የሚደረግ ፕሮፖጋንዳን” የሚከለክል ሕግ አውጥታለች።

የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን የሚያመለክቱ ይዘቶች ከመጽሓፍት፣ ከፊልሞች፣ ከማስታወቂያዎች እና ከቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲሰረዙ ተደርገዋል።

በቅርቡም አንድ የሩሲያ የቴሌቪዥን ጣቢያ የፕሮፓጋንዳውን ሕግ ጥሷል ተብሎ እንዳይከሰስ በደቡብ ኮሪያ የፖፕ ሙዚቃ ቪዲዮ ላይ የነበረውን የቀስተ ደመና ቀለም እንዲለውጥ መገደዱ ተነግሯል።