"ባለቤቴን አጣሁ፤ ተዋረድኩ"፡ በ8 ዶላር ጉቦ ለ39 ዓመታት ፍርድ ቤት የተመላለሱት አዛውንት

ጃግሽዋር ፕራስድ

የፎቶው ባለመብት, Alok Putul/BBC

የምስሉ መግለጫ, ጃግሽዋር ፕራስድ

በሕንዷ ከተማ ራይፑር አንድ ያረጀ ቤት ይታያል። የ84 ዓመቱ ጃግሽዋር ፕራስድ አቫድያ መኖሪያ ነው።

ስምንት ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል በሚል ለ39 ዓመታት በዘለቀ የፍርድ ሒደት ውስጥ አልፈዋል።

ግለሰቡ በሕንድ የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይሠሩ ነበር። በአውሮፓውያኑ 1986 አንድ መቶ ሩፒ የሕንድ ገንዘብ (8 ዶላር ገደማ) ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው ተከሰሱ።

ስምንት ዶላር ትንሽ ገንዘብ ይመስላል። ለጃግሽዋር ግን ትልቅ ነው። ለዓመታት እታሰራለሁ ብለው ሲሰጉ ኖረዋል።

ከክሱ ነጻ የተባሉት ከ39 ዓመታት በኋላ ነበር። ነጻ መባላቸው የሚያስደስታቸው አይደለም።

"ውሳኔው ለእኔ ትርጉም አልባ ነው። ሥራዬን አጥቻለሁ። ማኅበረሰቡ ፊቱን አዙሮብኛል። ልጆቼን ማስተማር አልቻልኩም። ልጆቼን አልዳርኩም። ዘመዶቼ ተጣልተውኛል። ባለቤቴ ሕክምና ማግኘት ስላልቻለች ሞተችብኝ። በሕይወቴ ያጣሁትን ማን ይመልስልኛል?"

የሕንድ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን በማጓተት ይታማሉ። የፍትሕ ሚኒስትሩ እንዳሉት ወደ 52 ሚሊዮን የሚጠጉ ክሶች በፍርድ ቤቶች እየታዩ ነው።

ጃግሽዋር ፕራስድ የክፍያ ክፍል ተባባሪ ሠራተኛ እንደነበሩ በፍርድ ቤት ቢገለጽም በአገሪቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ታስረዋል።

"በትራንስፖርት ድርጅቱ ውስጥ አንድ ሠራተኛ ላልፈጸመው ክፍያ ሰነድ እንዳዘጋጅ ጠየቀኝ። ከበላይ አመራሮች ትዕዛዝ ሲደርሰኝ መረጃ እንደማገኝ እና ሰነዱን የማዘጋጀው መረጃው ከደረሰኝ በኋላ መሆኑን ነገርኩት። ሠራተኛው በ20 ሩፒ ሊደልለኝ ሞከረ። በዚህ ደስተኛ አለመሆኔን ገለጽኩለት። ወደ ቢሮዬ ዳግመኛ እንዳይመጣም ነገርኩት።"

ጉቦውን አልቀበልም በማለታቸው ሠራተኛው መቆጣቱን ያስታውሳሉ። ከቀናት በኋላ ተመልሶ ቢሯቸው ሄደ።

"ከቢሮ ስወጣ ከኋላዬ መጥቶ የሆነ ነገር በኪሴ ከተተ" ይላሉ።

ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ጊዜ ሳያገኙ መለያ ልብስ ያላደረጉ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው። ጎቦ በመቀበል እንደሚከሰሱ ተነገራቸው።

ጃግሽዋር ፕራስድ

የፎቶው ባለመብት, Alok Putul/BBC

የምስሉ መግለጫ, ጃግሽዋር ፕራስድ

ረዥሙ የፍትሕ ጉዞ

የታሰሩበት ቀን ረዥሙን የፍትሕ ትግል የጀመሩበት እንደሆነ ይናገራሉ። ቅጣቱ ከእሳቸው አልፎ ለቤተሰባቸው ተርፏል።

ታስረው ክስ የተመሠረተባቸው ከሁለት ዓመት በኋላ በ1988 ነው። ከ1988 እስከ 1994 ከሥራ ተባረዋል።

ከራይፑር ግዛት ወደ ሬዋ ተዛወሩ። ከባለቤታቸው እና ከልጆቻቸው ጋርም ተራራቁ። ደሞዛቸው በግማሽ ተቆርጦ ነበር።

የሥራ ዕድገት ሳይሰጣቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። ልጆቻቸው አንድ በአንድ ትምህርት አቋረጡ።

ያኔ 13 ዓመቱ የነበረው ትንሹ ልጃቸው ነራጅ አሁን 52 ዓመት ሞልቶታል። ልጅነቱን እንደተሰረቀ ይናገራል።

"ያኔ የጉቦን ትርጉም ራሱ አላውቅም ነበር። ሰዎች ግን 'ጉቦ የበላው ሰውዬ ልጅ' ይሉኛል" ይላል።

"ልጆች ይቀልዱብኝ ነበር። ጓደኛ ማፍራት አልቻልኩም። ጎረቤቶቻችን እና ዘመዶቻችን ፊታቸውን አዞሩብን። የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል ባለመቻሌ በተደጋጋሚ ተባርሬያለሁ" ይላል እምባውን እየጠረገ።

የመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት ጉቦ መስጠት በሕንድ የተለመደ ነው።

ጃግሽዋር ፕራስድ

የፎቶው ባለመብት, Alok Putul/BBC

የምስሉ መግለጫ, ጃግሽዋር ፕራስድ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መብራት ለማስገባት፣ የልደት ምስክር ወረቀት ለማውጣት ወይም የመንግሥት ሥራ ለማግኘት ጉቦ መስጠት ግድ ይሆናል።

ሆኖም ግን የሚታሰሩት እና የሚከሰሱት በጣም ጥቂት ባለሥልጣናት ናቸው።

የጃግሽዋር ባለቤት ኢንዱ በ1977 በልብ ድካም ሞታለች። በማኅበረሰቡ የደረሰባት ጫና ቀላል አልነበረም።

"ባለቤቴ በጭንቀት ሞተች። በጉቦ ስከሰስ ለረዥም ጊዜ በድባቴ ስትሰቃይ ነበር። የእኔ ከሥራ መባረር እና ሐዘኑ ተደራረበባት። ማሳከሚያ ገንዘብ አልነበረኝም። የሞተችበትን ቀን አልረሳውም። ለቀብር እንኳን ገንዘብ አልነበረኝም። ጓደኛዬ 3,000 ሩፒ ሰጥቶኝ ቀበርኳት።"

በአውሮፓውያኑ 2004 በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የአንድ ዓመት እስራት እና የ1,000 ሩፒ ቅጣት ተፈረደባቸው።

ምስክሮች የሰጡት ቃል ትክክለኛ እንዳልነበረ በይፋ ቢገልጹም ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አሳለፈ።

ጉዳያቸውን ወደ ቻቲስግራህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስደው ይግባኝ ካሉ በኋላ ከክሱ ነጻ መሆናቸው ተገለጸ።

ሳይታሰሩ ቢቀሩም የፍርድ ቤቱ ፋይል ሳይዘጋ ዓመታት ቆይተዋል።

የጉዞ ወኪል እና ሹፌር በመሆን ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሞክረዋል። ዕድሜያቸው ቢገፋም በቀን እስከ 10 ሰዓት ለመሥራት ይገደዳሉ።

የስምንት ዶላር ክስ ሕይወታቸውን አመሰቃቅሎታል። ማረሚያ ቤት ባይገቡም ለ14,000 ቀናት በማይታይ እስር ቤት ኖረዋል።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በ2004 የተመለከተውን ጉዳይ በ2025 በድጋሚ አይቷል። ማስረጃ መርምሮ፣ ምስክሮች እና ግራ ቀኙን ሰምቶ ነጻ ብሏቸዋል።

"ፍትሕ ሰፍኗል። ግን የጠፋውን ጊዜ አይመልስልኝም። ባለቤቴን መልሶ አያመጣትም። ለልጆቼ ልጅነታቸውን አይመልስላቸውም።"

ጠበቆቻቸው ከመንግሥት ካሳ ለማግኘት እየሞከሩ ነው።

ጃግሽዋር ፕራስድ መንግሥት ጡረታቸውን እና ያጡትን ገንዘብ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ሌላ እሰጣ ገባ ውስጥ መግባት ግን አይሹም።

"ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከክሱ ነጻ ነህ ብሎኛል" ይላሉ ሐዘን በሰበረው ድምጽ እና ፊት።

"ከሚሰማኝ ጫና አንጻር የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዋጋ ያጣል። እኔም ቤተሰቤም 39 ዓመታትን ተነጥቀናል።"