የዩክሬን የአውሮፓ አጋሮች የሰላም ድርድሩ ኪየቭን ማካተት አለበት አሉ

የአውሮፓ አጋሮች ከሩሲያ ጋር የሚደረጉ ማናቸውም የሰላም ንግግሮች ኪየቭን ማካተት እንዳለባቸው በማሳሰብ ድጋሚ ለዩክሬን ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ።

የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የጀርመን፣ የፖላንድ፣ የፊንላንድ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ "በዩክሬን ውስጥ ያለውን የሰላም መንገድ ያለ ዩክሬን ተሳትፎ መወሰን አይቻልም" ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ዳግም በሚያደርጉት ጥረት የፊታችን አርብ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በአላስካ እንደሚገናኙ ማሳወቃቸው ይታወሳል።

ዩክሬን ወደ ሰላም ድርድሩ ላትጋበዝ ትችላለች ብለው የሰጉት ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከኪየቭ ውጭ የሚደረጉ ስምምነቶች ሁሉ "የከሸፉ ውሳኔዎች" ይሆናሉ ብለዋል።

ቅዳሜ አመሻሽ ላይ የዋይት ሐውስ ባለስልጣን ትራምፕ ከፑቲን እና ከዜሌንስኪ ጋር የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስ ግን መጀመርያ ላይ ሩሲያ በጠየቀችው መሠረት ሁለቱ መሪዎች ብቻ ናቸው እንደሚገናኙ ይፋ የተደረገው።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከፑቲን ጋር ብቻ በመገናኘት መጀመር እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ለጋዜጠኞች "ከሩሲያ ለመጀመር" እንዳቀዱ ተናግረው ነበር።

ነገር ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከፑቲን እና ከዜሌንስኪ ጋር የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማድረግ "ዕድሉ አለ" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ፑቲን በዚህ ሀሳብ ስለመስማማታቸውም ሆነ አለመስማማታቸው የታወቀ ነገር የለም።

በተደጋጋሚ ከዜሌንስኪ ጋር በቀጥታ ውይይት ለማድረግ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ፑቲን ከሦስት ዓመታት በፊት በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከፈፀሙ በኋላ ሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው አያውቁም።

ትራምፕ አርብ ዕለት ሞስኮ እና ኪየቭ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ "የግዛቶች መለዋወጥ እንደሚደረግ" ጠቁመዋል።

ዜለንስኪ ግን ለዚህ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ምላሽ ሰጥተዋል።

ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ "ሩሲያ ላጠፋችው ጥፋት አንሸልማትም" ብለዋል። "በእኛ ላይ የሚወሰኑ ማናቸውም ውሳኔዎች፣ ማንኛውም ዩክሬንን ያላካተተ ውሳኔ፣ ሰላምን የሚፃረሩ ውሳኔዎች ናቸው" ብለዋል።

አክለውም "ሩሲያውያን... አሁንም የዩክሬንን ግዛት በዩክሬን ግዛት 'ለመለዋወጥ' የሚለውን ሀሳባቸውን ለመጫን ይሞክራሉ። ውጤቱም ምንም ዋስትና የማይሰጥ ሩሲያውያን ጦርነቱን ለመቀጠል የበለጠ አመቺ የሚያደርግላቸው ነው" ሲሉ በቆራጥነት ተናግረዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ ሚዲያ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ዋይት ሐውስ ሩሲያ በምሥራቅ ዩክሬን የሚገኘውን የዶንባስ ግዛትን እና የክራይሚያን ባህር ሰርጥ በሙሉ ለመውሰድ ያቀረበችውን ሃሳብ ዩክሬን እንድትቀበል ለማድረግ የአውሮፓ አጋሮቿን ለማሳመን እየተሞከረ ነው።

የአውሮፓ መሪዎች ቅዳሜ ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ "ዓለም አቀፍ ድንበሮች በኃይል መለወጥ የለባቸውም" ሲሉ አሳስበዋል ።

"ዩክሬን የራሷን እጣ ፈንታ የመምረጥ ነፃነት አላት" ሲሉ አገሮቻቸው ለዩክሬን በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ እና በገንዘብ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

መሪዎቹ ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን ደህንነትም ለመከላከል ጭምር "ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ" ወሳኝ ነው ብለዋል።

በአላስካው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የምትጠይቀው ዩክሬን ብቻ አይደለም።

የአውሮፓ አጋሮቿ ትራምፕ ከፑቲን ጋር ሊደርሱበት በሚችሉት ማንኛውም ስምምነት ላይ ተጽዕኗቸው አለመኖሩ ያሳስባቸዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቅዳሜ እለት በኤክስ ገጻቸው ላይ ሩሲያ እና አሜሪካ የአውሮፓን ተሳትፎ አለማካተታቸው የፈጠረባቸውን ስጋት አንፀባርቀዋል።

"አውሮፓውያን የራሳቸው ደህንነት አደጋ ላይ ስለሆነ የመፍትሄው አካል መሆን አለባቸው" ሲሉ ጽፈዋል።

አውሮፓ ሞስኮ ላይ ማዕቀብ በመጣል እነዲሁም ለዩክሬን የጦር መሳርያ ድጋፍ በማድረግ ሩሲያ ላይ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ወስዳለች።

ዜለንስኪ ቅዳሜ ዕለት ከማክሮን ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ላይ ዋናው ነገር "ሩሲያውያን እንደገና ማንንም እንዳያታልሉ" ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የዩክሬኑ መሪ "ሁላችንም ጦርነቱ እንዲቆም እና ለዩክሬን እና ለሌሎች የአውሮፓ አገራት አስተማማኝ የደህንነት መሰረት እንፈልጋለን" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ከአውሮፓ እና ከዩክሬን ጋር ያላት ዲፕሎማሲ የወደቀው በምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ ላይ ነው።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ቅዳሜ ዕለት ዩናይትድ ኪንግደምን በጎበኙበት ወቅት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ እና ከዜሌንስኪ ከፍተኛ ረዳቶች ጋር ተወያይተዋል።

ስለ ውይይቶቹ ቫንስን በማመስገን የዜሌንስኪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አንድሪይ ያርማክ ዩክሬን መካተት አለባት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

"አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በድርድር ጠረጴዛ ላይ ዩክሬን ስትኖር ብቻ ነው" ብለዋል።

"ተኩስ ማቆም አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የጦር ግንባሩ ድንበር አይደለም።"

እአአ በ1867 ሩሲያ ለአሜሪካ በሸጠችው አላስካ የሚካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ፣ ጆ ባይደን ከፑቲን ጋር በ2021 በጄኔቫ ከተገናኙ በኋላ በሥልጣን ላይ ያሉ የአሜሪካ እና የሩሲያ ፕሬዚዳንቶች ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

ጆ ባይደን ፑቲንን ጄኔቫ ካገኙ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ሞስኮ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን ልካለች።

እአአ በ 2022 ክሬምሊን አራት የዩክሬን ግዛቶችን ዶኔትስክ፣ሉጋንስክ፣ዛፖሪዝህዝሂያ እና ኬርሰን ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ባይኖራትም መገንጠላቸውን አስታውቃለች።

ሞስኮ በሙሉ ወረራዋ ወሳኝ ለውጥ ማምጣት ቢሳናትም፣ ነገር ግን የዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛት ሰፊ ቦታዎች ይዛለች። የዩክሬን ጥቃት በበኩሉ የሩስያን ኃይሎችን ወደ ኋላ መመከት አልቻለም።