ዩናይትድ ከዎልቭስ ሲጫወት ፍጹም ቅጣት ምት በመከልከሉ የዳኞች ማሕበር ይቅርታ አለ

ሰኞ ምሽት በነበረ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዎልቭስ ፍጹም ቅጣት ምት በመከልከላቸው ይቅርታ ተጠየቁ።

ዎልቭስ ከሜዳቸው ውጭ ከዩናይትድ ሲፋለሙ በጨዋታው መገባደጃ የተከለከሉትን ፍጽም ቅጣት ምት ቢያገኙ ኖሮ ከዩናይትድ ጋር አቻ መለያየት ይችሉ ነበር።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ በእንግሊዝ የሚከናወኑ ፕሮፌሽናል ጨዋታዎችን የሚዳኘው ማኅበር አለቃ ሆዋርድ ዌብ ሰኞ ምሽት በነበረው ጨዋታ ዎልቭስ ፍጹም ቅጣት ምት ማግኘት ይገባቸው እንደነበረ ለክለቡ ተናግረዋል።

የማኅበሩ አለቃ ዩናይትድ ዎልቭስን 1 ለ 0 እየመራ በተጨማሪ ሰዓት የዩናይትዱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና በዎልቭሱ አጥቂ ሳሳ ካላይጂች ላይ ፍጹም ቅጣት ምት የሚያሰጥ ጥፋት ቢሰራም ዎልቭስ ፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለዋል የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

ይህን ተከትሎም ጨዋታውን የዳኙት ሦስት ዳኞች ለሁለተኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሳይመረጡ ቀርተዋል።

የመሃል ዳኛው ሳይመን ሁፐር፣ የቫር ዳኛ ማይክል ሳሊስበሪ እና ምክትል የቫር ዳኛ ሪቻርድ ዌስት ቀጣይ ጨዋታዎችን እንዲዳኙ እስካሁን አልተመረጡም።

ኦልትራፎርድ ላይ በነበረው ጨዋታ የዩናይትዱ ተከላካይ ራፋኤል ቫራን በ73ኛ ደቂቃ ባስቆጠራት የጭንቅላት ጎል ባለሜዳው ቡድን ሦስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል።

ባለፈው የውድድር ዘመን በሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎቹ ሽንፈት አስተናግዶ የነበረው የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ውጤቱ እንዴት መጣ ሳይሆነው ዋናው ነገር ለቡድኑ ሙሉ ነጥብ ማግኘቱ ነው ይላል ሳይመን።

በጨዋታው ዎልቭስ 23 ግዜ የጎል ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በአንጻሩ ባለሜዳው ዩናይትድ ያደረገው ሙከራ 15 ነበር።

የዎልቭስ አዲሱ አሰልጣኝ ጌሪ ኦኒል ቡድናቸው ካሳየው ብቃት እና ካደረጋቸው ሙከራዎች አንጻር ቢያንስ ከተጋጣሚያችን ጋር ነጥብ ተጋርተውን መውጣት ነበረብን ብለዋል።

አሰልጣኙ ውድድሩ እንደተጠናቀቀ የዳኞች ስብስብ ኃላፊ የሆኑት ጆን ሞስ ቀርበዋቸው የተሰራው ጥፋት በግልጽ ፍጹም ቅጣት ምት እንደሚያሰጥ ሲነግሩኝ ፍጹም ቅጣት ምት መከልከላችን ይበለጠ አበሳጭቶኛል ብለዋል።

ቴን ሃግ ከጨዋታው በኋላ ዎልቭስ የጠየቁት ፍጹም ቅጣት ምት በቫር ታይቶ ሳይጸድቅ መቅረቱ እፎይታ ሰጥቶኛል ካሉ በኋላ ቡድናቸው እንደጠበቁት አለመጫወቱ ቅር እንዳሰኛቸው በግልጽ ተናግረዋል።

ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና በበኩሉ ፍጹም ቅጣት ምቱ እንደማይሰጥ “እርግጠኛ ነበርኩ” ብሏል።

ኦናና “ግብ ጠባቂዎች ውሳኔዎችን ይወስናሉ፤ አንዳንዴ ውሳኔዎቹ ትክክል ናቸው አንዳዴ ደግሞ ትክክል አይሆኑም። . . . ለእኔ ሁለት በአካል ግዙፍ የሆኑ ሰዎች መጋጨት (ለኳስ ሲሻሙ) እንጂ ሌላ አይደለም። ለኛ ዋናው ማሸነፋችን ነው። በድሉ ደስተኛ ነኝ” ብሏል ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት።