ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኩዌት የውጭ አገር ሠራተኞች መኖሪያ ሕንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ40 በላይ ሰዎች ሞቱ
የኩዌት ከተማ በሆነችው ማንጋፍ ውስጥ በሚገኝ አንድ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ቢያንስ 41 ሰዎች መሞታቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች የሕንጻው የታችኛ ክፍሎች በእሳት ነበልባል ሲቃጠሉ፣ ከላይኛው ክፍሎች ደግሞ ጥቁር ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 15 ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። በእሳት ቃጠሎው ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በሕንጻው ውስጥ የሚኖሩ ከውጭ አገራት የመጡ ሠራተኞች ናቸው።
የኩዌት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እሳቱ በቁጥጥር ስር ውሎ በሕንጻው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሕይወት የማዳን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ሜጀር ጄኔራል ኢድ አል-ኦዌይሃን ለአገሪቱ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፣ የእሳት አደጋው የደረሰው ዛሬ ረቡዕ ማለዳ 12 ሰዓት ላይ ነው።
የኩዌት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ፋሃድ ዩሱፍ አል-ሳባህ የአደጋውን ስፍራ በጎበኙበት ጊዜ የሕንጻው ባለቤቶችን የደኅንነት መመሪያዎችን በመጣስ እና “በገንዘብ ወዳድነት” መክሰሳቸውን ሮይተርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት አደጋው የደረሰበት ሕንጻ ከሚገባው በላይ በርካታ ሰዎች ተጨናንቀው የሚኖሩበት ነው።
አንድ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ለአገሪቱ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃል፣ አደጋው በደረሰበት ጊዜ “ከፍተኛ ቁጥር” ያላቸው ሰዎች በሕንጻው ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ ይኖሩ ነበሩ።
“የበርካቶችን ሕይወት ለማዳን ተችሏል፣ ነገር ግን በጭስ በመታፈን ምክንያት የሞቱ ሰዎች አሉ” በማለት በእንደዚህ ዓይነት ለተጨናነቁ የመኖሪያ ሕንጻዎች ተደጋጋሚ የአደጋ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
አደጋው በደረሰበት ሕንጻ ውስጥ የነበሩት የውጭ አገር ሠራተኞችን ዜግነት እና የቅጥር ሁኔታቸውን በተመለከተ አስካሁን ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
ነገር ግን ያልተረጋገጡ ዘገባዎች በአደጋው ከሞቱት የተወሰኑት የሕንድ ዜግነት ያላቸው ሠራተኞች መሆናቸውን ያመለክታሉ።
ከኩዌት ሕዝብ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የውጭ አገር ሠራተኞች ሲሆኑ፣ አገሪቱ በተለይ በግንባታ ዘርፍ እና በቤት ውስጥ ሥራ ከውጭ አገራት በሚመጡ ሠራተኞች ላይ ጥገኛ ናት።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በተደጋጋሚ በአገሪቱ ያሉ የውጭ አገር ሠራተኞች የአኗኗር ሁኔታን በተመለከተ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።