"በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራት ጤናማ ያደርጋል"- በ141 ተቋማት የተሠራ ጥናት

በተለመደው አካሄድ በሳምንት አምስት ቀን ሠርተን ሁለት ቀን እናርፋለን። ሰኞ ሲመጣ ወደ ሥራ እንመለሳለን። ይሄ አሠራር ምን ያህል ውጤታማ ይሆን?

'ኔቸር ሂውማን ቢሄቪየር' በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ የታተመው ጥናት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

እስካሁን በዘርፉ ከተሠሩ ጥናቶች ሰፊው ነው። በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራት የሰዎችን ጤና እንደሚያሻሽል ጥናቱ ያትታል።

ጥናቱን የሠሩት የቦስተን ኮሌጅ ባለሙያዎች ናቸው። ከሥራ ጋር በተያያዘ መታከት፣ በሥራ ደስተኛ መሆን እንዲሁም አካላዊ እና አእምሯዊ ጤናን መዝነዋል።

በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ፣ በአየርላንድ እና በኒው ዚላንድ በሚገኙ 141 ተቋማት ውስጥ ነው ምርምሩ የተካሄደው።

የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ዌን ፋን "በሠራተኞች ጤና ላይ ትልቅ ለውጥ አይተናል" ብለዋል።

እንዲሁም አራት ቀናት ብቻ በመሥራት የተቋማት ውጤታማነት እና ትርፋማነትም ጨምሯል።

በተቋሙ ውስጥ አጥኚዎቹ ያደረጉት ሙከራ ከተጠናቀቀ በኋላ 90 በመቶ የሚሆኑት በሳምንት አራት ቀናት ብቻ ለመሥራት ወስነዋል።

በሳምንት አራት ቀን መሥራት የጤና ጥቅም እንዳለው ከተረጋገጠ ለምን ይሄንን አሠራር መተግበር አልተቻለም?

ብዙ የመሥራት ልማድ

ቻይናውያን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ በሳምንት ስድስት ቀናት በመሥራት ይታወቃሉ።

በሕንድ እያደረገ በመጣው የቴክኖሎጂ እና የፋይናንስ ዘርፍ ሠራተኞች ረዥም ሰዓት እንዲያገለግሉ ጫና ይደረግባቸዋል። ከሥራ ሰዓት ውጪ በመሥራት የዓለም አቀፍ ገበያውን ፍላጎት ለማሟላት ይሞከራል።

ፕሮፌሰር ዌን እንደሚሉት እንደ ቻይና፣ ሕንድ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ባሉት አገራት ረዥም ሰዓት መሥራት የሚያስከብር ነው።

በጃፓን ከሥራ ሰዓት ውጪ አብዝቶ መሥራት የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ በሥራ ብዛት የሚከሰት ሞት 'ካሮሺ' የሚል ስም ተሰጥቶታል።

በጃፓን የሥራ ገበያ ባለሙያ ሂሮሺ ኦኖ "በጃፓን ሥራ ከሥራነትም በላይ ነው። እንደ ማኅበራዊ ክንውን ነው የሚታየው" ይላሉ።

ሥራ ባይኖርም እንኳን ማልዶ መግባት እና ዘግይቶ መውጣት የተለመደ ነው።

"ይህም የሚደረገው ቁርጠኛነትን ለማሳየት ነው። እንደ ማርሻል አርትስ ለዕይታ የሚደረግ ነው" ይላሉ ባለሙያው።

ሳይሠሩ የሚበሉ ሰዎች በጣም ስለሚጠሉ ሁሉም ሰው ታታሪነቱን ለማሳየት ይሞክራል። አንድ ሰው አርብ እረፍት ቢወጣ 'እንዴት የሥራ ቀን ይዘላል?' ተብሎ ይታማል።

በጃፓን የአባቶች የእረፍት ፈቃድ ሳይቀር ይታጠፋል።

"አንድ ዓመት ያህል የአባትነት እረፍት መውጣት ቢቻልም የሚጠቀሙበት ጥቂት ወንዶች ናቸው። በርካቶች እረፍት በመውሰድ የሥራ ባልደረቦቻቸውን ማስቸገር አይፈልጉም" ሲሉ ሂሮሺ ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ዌን እንደሚገልጹት ቡድናቸው የሠራው ጥናት ስለ ሥራ ባህል ያለውን አመለካከለት ሊቀይር ይችላል።

በአይስላንድ 90 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች የሥራ ሰዓታቸውን አሳጥረዋል። የሥራ ሰዓትን ማሳጠርም በሕግ ይፈቀዳል።

የሥራ ሰዓት ወይም ቀናት ለማሳጠር በሚል በደቡብ አፍሪካ፣ በብራዚል፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ እና በቦትስዋና ሙከራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

ቶኪዮ ለመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ቀናትን አራት ለማድረግ ጅማሮ ላይ ናት። ዱባይም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች።

ደቡብ ኮሪያ በ67 ተቋማት ውስጥ አራት ቀን ከግማሽ መሥራትን በቅርቡ ትተገብራለች።

ሕይወትን የሚያሰናክል ሥራ

'4 ዴይ ግሎባል' የተባለው ተቋም ኃላፊ ካረን ሎዌ "ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ ሕይወት እና ሥራ ተጣጥመው እየሄዱ አለመሆኑ ታውቋል" ይላሉ።

በብራዚል፣ በናሚቢያ፣ በጀርመን እና በሌሎችም አገራት ተቋማቸው አራት ቀን እንዴት መሥራት እንደሚቻል መንገድ ያመላክታል።

ኮሎራዶ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በ250 ሠራተኞች በሳምንት አራት ቀን ብቻ መሥራትን ተግብረዋል። ትልቁ ስኬታችን የሚሉት ተሞክሮም ይሄ ነው።

ፖሊስ ጣቢያው ለተጨማሪ ሰዓት ክፍያ የሚያወጣውን ወጪ በ80 በመቶ ቀንሷል።

"ድንገተኛ ጥሪ በሚያስተናግድ ፖሊስ ጣቢያ አሠራሩ ውጤታማ ከሆነ በየትኛውም ተቋም ሊተገበር ይችላል ማለት ነው" ይላሉ።

በአውሮፓውያኑ 2019 ሥራውን ሲጀምሩ በጣት የሚቆጠሩ ተቋማት ብቻ ነበሩ ሐሳቡን የተቀበሉት። አሁን ግን በሺዎች የሚቆጠሩ መሥሪያ ቤቶች አሠራራቸውን ለመለወጥ ቆርጠው ተነስተዋል።

"አሠራሩ ውጤታማ እንደሆነ ማስረጃዎች አሉ። ነገሩን መረዳት ብቻ ነው የሚጠይቀው" በማለት ያስረዳሉ።

ውስን የሥራ ቀናት ሲባል ውጤታማነት የሚቀንስ የሚመስላቸው ብዙ ቢሆኑም እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው።

በ2019 የማይክሮሶፍት የጃፓን ቅርንጫፍ በሳምንት አራት ቀናት በመሥራት ውጤታማነቱ በእያንዳንዱ ሠራተኛ 40 በመቶ ጨምሯል።

ሆኖም አሠራሩን አልዘለቀበትም።

ካረን እንደሚገልጹት፣ ግዙፍ ተቋማት በተለያዩ አገራት ቅርንጫፍ ስላላቸው እና የሥራ ሰዓት ልዩነት ስለሚገጥማቸው አሠራሩን ለመተግበር ሊቸገሩ ይችላሉ።

ፕሮፌሰር ዌን እንደሚሉት፣ የሥራ ቀናት ሲቀነሱ አላስፈላጊ ስብሰባዎች ወደ ስልክ ጥሪ ወይም አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተለውጠዋል።

የሥራ ቀናት ሲቀነሱ ሥራን ለማካካስ ሠራተኞች በበለጠ ይሠራሉ የሚለው አመለካከት የተዛባ መሆኑን ያስረዳሉ።

"አምስት የሥራ ቀናትን ወደ አራት ለማውረድ መጨነቅ አይደለም ነጥቡ። ብክነትን መቀነስ ነው ግቡ" ይላሉ።

ጤናማው አሠራር

በኬፕ ታውን በስቴልቦሽ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ሼሪል ዴቪስ እንደሚሉት፣ አራት ቀናት ብቻ መሥራት ጤናማ ሕይወትን ለመምራት ይረዳል።

ሼሪል የሚመሩት ቡድን ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የሥራ ቀናት ወደ አራት ከመቀነሳቸው በፊት በከፍተኛ ድካም ይንገላቱ ለነበሩ 30 ሺሀ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ድጋፍ ይሰጡ ነበር።

"ብዙዎቹ ሠራተኞች እየታመሙ ይቀሩ ነበር። ሰነፍ ሁነው ሳይሆን ከፍተኛ ሥራ ስለሚያደክማቸው ነበር። ሥራው እንጥፍጣፊ አቅም እንዳይቀራቸው ነበር የሚያደርጋቸው" ይላሉ።

ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት ከሚስተዋልባቸው አገራት መካከል ትጠቀሳለች።

ሼሪል ከበላይ ያሉ አለቆች ፈቃደኛ ባይሆኑም አራት ቀን ብቻ መሥራትን ተግባራዊ ለማድረግ ታግለዋል።

"ስኬታማ አይሆንም ብለው ነበር። ግን ውጤታማ ሆንን" ይላሉ።

አሠራሩ ከመተግበሩ በፊት በስድስት ወራት ውስጥ 51 ጊዜ በሕመም ምክንያት ፈቃድ ተጠይቋል። አራት ቀናት ብቻ መሥራት ሲጀምር ግን ወደ አራት ቀን ፈቃድ ብቻ ወርዷል።

የተሻለ እንቅልፍ እንደሚተኙ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ እና አዳዲስ ጊዜ ማሳለፊያዎች መጀመራቸውን የተናገሩ ብዙዎች ናቸው።

በትርፍ ቀናቸው በመሥራት ገንዘብ ለማግኘት ይሞክራሉ ተብሎ ቢታሰብም ከአንድ ሰው በስተቀር የተቀሩት እረፍታቸውን በአግባቡ መጠቀም ነው የመረጡት።

"ትኩረታቸው ጨምሯል። የሥነ ልቦና ድጋፍ ለሚሰጧቸው ተማሪዎች የበለጠ ሐዘኔታም ያሳያሉ" ሲሉ ለውጡን ይገልጻሉ።

ለውጥ የሚሹ ወጣቶች

የሥራ ቀናትን የመቀነስ አሠራር ሁሉንም ተቋም ውጤታማ ያደርጋል ማለት አይደለም።

ፕሮፌሰር ዌን እንደሚሉት፣ የአንድ አገር የምጣኔ ሃብት አወቃቀር ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።

"አብዛኞቹ አፍሪካውያን በግብርና ወይም በማዕድን ማውጣት ሥራ የተሰማሩ ናቸው። ሥራዎቹ ኢ-መደበኛ ስለሆኑ በቀላሉ የሥራ ቀንን መቀነስ አይቻልም" ይላሉ።

አነስተኛ ገቢ በሚያስገኙ የጉልበት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሥራ ቀናቸውን ከመቀነስ ይልቅ ጨምረው ደመወዛቸውን ማሳደግ ነው የሚመርጡት።

ፕሮፌሰር ዌን የግንባታ፣ አገልግሎት ሰጪ እና የፋብሪካ አምራች ተቋማትን በጥናታቸው አካትተዋል።

"በየትኛውም ዘርፍ አራት ቀን በሳምንት መሥራት ሊተገር ይችላል። ሆኖም ለሁሉም በውጤታማነት ይሠራል ማለት አልፈልግም" ይላሉ።

የሥራ ባህል እየተለወጠ የመጣው ወጣቶች በሚያሳድሩት ጫና መሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

በቅርቡ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው ወጣቶች ከደመወዝ ይልቅ በሥራ እና በግል ሕይወታቸው መካከል ያለውን ሚዛን ማመጣጠንን ይመርጣሉ።

በደቡብ ኮሪያ ደመወዛቸው ተቀንሶ የሥራ ቀናትም ቢቀነሱላቸው የሚመርጡ ወጣቶች ተበራክተዋል።

"ወጣቶች የተለመደውን አሠራር አይፈልጉትም። የሥራ ዓላማ እና ሕይወት ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ የተለየ ዕይታ አላቸው" ይላሉ ፕ/ር ዌን።

ከኮሮና ወረርሽኝ ወዲህ በርካቶች ከሥራ መልቀቃቸው (ግሬት ሬዚግኔሽን በመባል የሚታወቀው) እንዲሁም አዳዲስ የሥራ ማቆም ልማዶች መምጣታቸውን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ።

በሥራ ቦታ ላይ አስፈላጊ የሆነውን ብቻ ማከናወን (ኳየት ኩዊቲንግ) የሚባለው እና በቻይና የሥራ ጫናን አለመቀበት (ላይንግ ፍላት የሚባለው) ከዚህ ጋር በተያያዥ ይጠቀሳሉ።

በጃፓንም ለውጦች እየታዩ ነው።

ሂሮሺ "አሁን 30 በመቶ የጃፓን ወንዶች የአባትነት እረፍት ይወጣሉ። እነዚህ በአብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። ኮቪድ ለውጥ አምጥቷል። አራት ቀናት ብቻ በሳምንት መሥራት ይለመዳል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ" ይላሉ።